በሌማት ቱርፋት ከሌማታቸው የተሻገሩ ብርቱዎች

የሌማት ቱርፋት ንቅናቄ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት ወደ ሥራ ከገባ በኋላ ብዙዎችን የሀብት ባለቤት አድርጓል:: ትኩረት ተነፍጓቸው የቆዩ የየአካባቢው ጸጋዎች እንዲታዩና አዲስ የሥራ ባህል እንዲፈጠርም አስችሏል:: ሥራ ፈላጊዎች ሥራ ፈጣሪ፤ ከእጅ ወደ አፍ ሲኖሩ የነበሩትም ትርፍ አምራች ሆነዋል:: በዚህም የጎደለ ሌማታቸውን ከመሙላት አልፈውም ለገበያ በማቅረብ የሌሎችን ጫና እያቀለሉ ይገኛሉ::

ማዕከላዊ ኢትዮጵያ በሌማት ቱርፋት ጥሩ ውጤት ከተመዘገበባቸው ክልሎች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው:: ወጣቶች፣ አርሶ አደሮችና የመንግሥት ሠራተኞችም ሳይቀር በሥራው ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ:: ወጣት አቤል ሙሉጌታ በምሥራቅ ጉራጌ ዞን የቡታጅራ ከተማ ነዋሪ ነው:: ከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸላቸው ቦታ ከአራት ጓደኞቹ ጋር በመሆን ቀሽት የንብ ማነብ ማህበርን መሥርተው ወደ ሥራ ገብተዋል:: እሱም ማህበሩን በሥራ አስኪያጅነት ይመራል::

በ2015 ዓ.ም ከእያንዳንቸው ኪስ በተዋጣ 110 ሺህ ብር 20 ቀፎዎችን በመግዛት ሥራውን እንደጀመሩ የሚያስታውሰው ወጣት አቤል፤ አሁን ላይ ሥራው ሰፍቶ የ450 ዘመናዊና የ300 ባህላዊ ቀፎዎች ባለቤት መሆን ችለዋል:: ከማር ባለፈ ሰም እንዲሁም ሕብረ ንብ እያባዙ ለገበያ ያቀርባሉ:: አካባቢው ለማር ምርት ምቹ በመሆኑ ከአንድ ቀፎ በዓመት በአማካይ ከ50 ኪሎ ግራም በላይ ምርት እናገኛለን፤ ይህም ሕይወታችን ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቶልናል ይላል::

ለውጤታማነታቸው የሥራ ቦታ ማመቻቸትን ጨምሮ በየደረጃው ባሉ የመንግሥት አካላት የተደረገላቸው ድጋፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የሚጠቅሰው ሥራ አስኪያጁ፤ ሌሎች ወጣቶች የእነሱን ፈለግ ተከትለው ወደ ሥራ እንዲገቡና ሕይወታቸውን እንዲለውጡ ልምዳቸውን እንደሚያካፍሉ፤ ሥልጠናን ጨምሮ ሌሎችንም አስፈላጊ ቁሳቁሶች ድጋፍ እንደሚያደርጉም ይገልጻል::

ባለፉት ዓመታት ያካበቱትን ልምድ ተጠቅመው ሥራቸውን ወደ 20 ሺህ ቀፎ በማድረስ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጠቃሽ የሆነ ግዙፍ የንብ ማነቢያ ማዕከል መገንባትን ራዕይ አድርገው እንደሚሠሩ የሚጠቁመው ወጣቱ፤ ምርቱ ላይ እሴት ጨምረው ወደ ውጭ ለመላክም እቅድ አላቸው:: እቅዳችንን ከዳር ለማድረስ ጥረት እናደርጋለን፤ መንግሥትም እስካሁን ሲያደርግልን የነበረውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥል ሲል መልዕክቱን ያስተላልፋል::

አርሶ አደር በላይነህ መንቴ በከምባታ ዞን ቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ የዛቶ ሾደራ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው:: በሚያከናውኑት የጥምር ግብርና ሥራ አስር ቤተሰባቸውን ያስተዳድራሉ:: በሌማት ቱርፋት ንቅናቄ በተፈጠረላቸው ግንዛቤ ውጤታማ ያልነበሩ የላም ዝርያዎችን ወደ ተሻሻሉ ዝርያዎች በመለወጥ በወተት ልማት ውጤታማ መሆን ችለዋል::

ላሞቹ ከወለዱበት ጊዜ ጀምሮ አራት ወራት ድረስ በቀን ሦስት ጊዜ ወተት ይሰጣሉ የሚሉት አርሶ አደሩ፤ ከአራት ወር በኋላም በቀን ሁለት ጊዜ ይታለባሉ:: ጠዋትና ቀን የሚታለበው ወተት ለገበያ የሚቀርብ ሲሆን፣ የማታው ደግሞ ለቤተሰቡ ፍጆታ ይውላል:: ይህም ለቤተሰቡ የተመጣጠነ ምግብ ማቅረብ፣ ለገበያ ከሚቀርበውም ተጨማሪ ገቢ ማግኘት አስችሏቸዋል::

ባለሙያዎች በሚያደርጉላቸው ድጋፍ የላሞችን ጤንነት በመጠበቅና አመጋገባቸውን በማስተካከል ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እንደሚሰሩ የሚገልጹት አርሶ አደሩ፤ በቀጣይነትም ሥራውን አስፍተው ወደ እንስሳት እርባታ ማዕከል የማሳደግ እቅድ ይዘዋል:: የሌማት ቱርፋት ንቅናቄ አካባቢያችንን ጸጋ እንድናውቅና እንድንጠቀም በማድረግ የብዙ ሰዎችን ሕይወት እየቀየረ ነው ይላሉ::

ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ በየደረጃው ያለው አመራር ለሚያደርጉት ጠንካራ ድጋፍና ክትትልም ምስጋና አቅርበዋል:: አቶ ተመስገን ሶደኖ እና ወይዘሮ የተመኝ አሰፋ በሀላባ ዞን የሀላባ ቁሊቶ ከተማ ነዋሪ ጥንዶች ናቸው:: አቶ ተመስገን የዞኑ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ባልደረባ ሲሆኑ፤ ባለቤታቸው ደግሞ በሀላባ ቁሊቶ ከተማ ውሃ አገልግሎት ውስጥ ይሠራሉ::

እንደሀገር የተፈጠረው የኑሮ ውድነት ቤታቸውን ሲያንኳኳ እንደነበር የሚያስታውሱት ጥንዶቹ፤ በተለይ ለልጆች ምግብ በዋና ግብዓትነት የሚጠቀሙት እንቁላል 15 ብር መግባት አሳስቧቸው ነበር:: በዚህም ምክንያት እንደማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ችግሩ እንዲቀረፍ ደጋግመው ሲጠይቁ ቆይተዋል::

የሌማት ቱርፋት ንቅናቄ ዞኑ ላይ ተግባራዊ ሲደረግ ግን ከጠያቂነት ይልቅ የመፍትሔው አካል መሆን ፈልጉና በጓሯቸው ዘመናዊ የዶሮ ርባታ ጀመሩ:: አሁን ላይ አርባ ዶሮዎችን እያረቡ ሲሆን፤ በየቀኑ ከ37 ያላነሰ እንቁላል ያገኛሉ:: ይህም የቤተሰቡን ፍላጎት ከማሟላት አልፎ ለገበያ ማቅረብ አስችሏቸዋል::

የዶሮ ልማት ጥቂት ቦታ ላይ መሠራት የሚችልና ብዙም ጊዜ የማይፈልግ ነው የሚሉት ጥንዶቹ፤ ጠዋት ላይ ማደሪያቸውን አጽድተውና ምግባቸውን አቅርበው ይሄዳሉ:: ለምሳ ወደ ቤት ሲመለሱም ቅድሚያ ዶሮዎችን የመንከባከብና የጣሉትን እንቁላል የማንሣት ሥራን ይሠራሉ:: በየጊዜው ክትባት እንዲያገኙና ተገቢው የባለሙያ ክትትል እንዲኖራቸውም ይሠራሉ::

የሌማት ቱርፋት ንቅናቄ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ በማድረግ ብዙዎችን ባለሀብት እያደረገ መሆኑን የሚያስታውሱት እነዚህ ብርቱ ጥንዶች፤ ገበያውን በማረጋጋት በኩልም ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል::

በቀጣይነት ሥራቸውን አስፍተው የመሥራት እቅድ እንዳላቸው የሚገልጹት ጥንዶቹ፤ አካባቢያቸው ላይ እምቅ ሀብት እያለ ሥራ የለም በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ጊዜያቸውን በከንቱ የሚያሳልፉ ወጣቶች መኖር የለባቸውም:: ሁሉም አካባቢውን መመልከትና ዝቅ ብሎ ሠርቶ ቀና ብሎ ለመሄድ ቁርጠኛ መሆን አለበት ሲሉም መልእክታቸውን ያስተላልፋሉ::

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 25  /2016 ዓ.ም

Recommended For You