ባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት አቅዷል

አዲስ አበባ፡- በ2017 በጀት ዓመት 70 ነጥብ 64 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ማቀዱን የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) ትላንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ በ2017 በጀት ዓመት 70 ነጥብ 64 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል ብለዋል፡፡

በዓመቱ የድርጅቱን ያልተጣራ የትርፍ መጠን 9 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለማድረስ መታቀዱን ጠቅሰው፤ የደንበኞች አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ የተቋሙን ገቢ ለማሳደግ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡

የተቋሙን ተሽከርካሪዎች የመጫን አቅም 34 ሺህ 619 ቶን፣ የኮንቴነሮችን ብዛት 28 ሺህ 184 ቲኢዩ ለማድረስ እና የወደቦች ኮንቴነር ተርሚናል 66 ነጥብ 13 ሄክታር ለማሳደግ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

የኦፕሬሽን አገልግሎትን መጠን 7 ነጥብ 9 ሚሊዮን ቶን እና በባህር የሚጓጓዙ ገቢ ዕቃዎችን 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን ለማድረስ ማቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በባህር የሚጓጓዝ ወጪ ዕቃዎች 16 ነጥብ 1 ሚሊዮን ቶንና በውጭ ወደቦች ከ810 ሺህ ቶን በላይ እቃዎችን ለማጓጓዝ ታቅዷል ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ በድርጅቱ መርከቦች ከ639 ሺህ ቶን በላይ የገቢ እቃ ለማጓጓዝ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

በመልቲሞዳል ሥርዓት ከ126 ሺህ ቲዩ በላይ ኮንቴነር ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚጓጓዝ ጠቅሰው፤ በድርጅቱ ተሽከርካሪዎች ከ705 ሺህ ቶን በላይ ጭነት እንደሚጓጓዝም ጠቁመዋል፡፡

የዩኒሞዳል ሥርዓት የገቢ ጭነትን ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን በላይ ለማድረስና የወጪ እቃ ጭነትን ከ392 ሺህ ቶን በላይ ለማድረስ እንደታቀደ ገልጸው፤ በደረቅ ወደቦች 2 ነጥብ 19 ሚሊዮን ቶን ጭነት ለማስተናገድ መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡

በሀገር ውስጥ የውሃ አካላት ላይ የሚጓጓዙ መንገደኞችን ቁጥር ከ126 ሺህ በላይ ለማድረስ እንደሚሠራ ገልጸው፤ ከ15 ሺህ ቶን በላይ በጭነት አገልግሎት ለመስጠት ማቀዳቸውን አስረድተዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተቋሙን ገቢ ለማሳደግ በተሠራው ሥራ 57 ነጥብ 14 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን ጠቅሰው፤ ከታክስ በፊት ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

የተቋሙን የገቢ መጠን ማሳደግ፣ የመርከቦችንና የጭነት ተሽከርካሪዎችን የመጫን አቅም መጨመር ላይ መሠራቱንም ጠቅሰዋል፡፡

ፈጣንና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት መስጠትና በቴክኖሎጂ የታገዙ አሠራሮችን ማጎልበት በበጀት ዓመቱ በትኩረት የተከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ማርቆስ በላይ

 አዲስ ዘመን ሐምሌ 20 /2016 ዓ.ም

 

Recommended For You