አካል ጉዳተኞች በምክክሩ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል

አዳማ፦ አካል ጉዳተኞች ያላቸውን አጀንዳ በማቅረብ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ገለጹ።

“አጀንዳችን ለነገዋ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ በሀገራዊ ምክክሩ ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገ ሀገር አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ኮንፈረንስ የመክፈቻ መርሃግብር በአዳማ ከተማ ትናንት ተካሂዷል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በዕለቱ እንደገለጹት፤ አካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ምክክሩ አጀንዳቸውን አቅርበው በሚገባ መሳተፍ ካልቻሉ ምክክሩ ሙሉ ሊሆን ሊሆን አይችልም፡፡ እናም አካል ጉዳተኞች ያላቸውን አጀንዳ በማቅረብ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክሩ ከተቋቋመ ጀምሮ ሁሉን አካታች በሆነ መልኩ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ዜጎች ለችግሮች ነፍጥን መፍትሔ ከማድረግ ይልቅ ለሀገራዊ ምክክሩ ቅድሚያ በመስጠት በግጭት ይበልጥ ተጎጂ የሆኑትን አካል ጉዳተኞችን ሊታደጉ ይገባል ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ የሰላም እጦት አካልንና አእምሮን በማሳጣት ሀገርን ወደ ውስብስብ ችግር የሚያስገባ መሆኑን አመላክተዋል።

በሀገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች የሚፈጠሩ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች የአካል ጉዳቶች ቁጥር ከፍ እያደረገው ይገኛል ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ የቀደሙና አሁናዊ ችግሮች በውይይትና በምክክር መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው፤ መድረኩ የአካል ጉዳተኞች በምክክሩ እንዲሳተፉ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አካል ጉዳተኞች በሀገሪቱ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የሀገሪቱ ሁለንተናዊ የልማት ግብ እንዲረጋገጥ አካል ጉዳተኞች በምክክሩ ተሰሚነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከ23 ሚሊዮን በላይ የአካል ጉዳተኞች በመኖራቸው ምክክሩ አካታች በሆነ መልኩ በማድረግ ልማትን ማረጋገጥ ያስፈልጋልም ብለዋል።

አካል ጉዳተኞችን አካታች ለማድረግ የፖሊሲ ማዕቀፎችና የፖለቲካ አደረጃጀቶች ላይ ተጨማሪ ሥራዎች መሥራት እንደሚጠይቅም አብራርተዋል።

መድረኩ አካል ጉዳተኛው የቀጥታ ውክልና እንዳያጣ የሚያስችለው ነው ብለዋል።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 20 /2016 ዓ.ም

 

Recommended For You