የትምህርት ስብራቱ ወጌሻ

ዜና ትንታኔ

ትምህርት ዓለም አሁን ለደረሰበት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ እድገት መሠረት ብቻ ሳይሆን የቀጣዩ የሰው ልጅ ህልውና ዕጣ ፈንታንም የሚወስን ነው። በኢትዮጵያ በየዘመኑ የነበሩ መንግሥታት ዘመናዊ ትምህርት ለእድገትና ብልጽግና ወሳኝ መሆኑን በመረዳት የየራሳቸውን የትምህርት ፖሊሲ በመቅረጽ ትምህርትን ሲተገብሩ ቆይተዋል።

በየዘመናቱ የነበሩ የዘርፉ ተግዳሮቶችን ለመፍታትም የትምህርት ሚኒስቴር ባለፉት ስድስት ዓመታት የለውጥ (ሪፎርም) አጀንዳዎችን ቀርጾ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል። ሪፎርም በአንድ ወቅት ተጀምሮ የሚያልቅ ሥራ ሳይሆን ቀጣይነት ያለውና በየጊዜው እየተገመገመ ማስተካከያ የሚያስፈልገው ተግባር መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡

በተለይም የትምህርት ተደራሽነትን፣ ፍትሃዊነትን ፣ተገቢነትን እና የጥራት ችግሮችን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ እንዲሁም ሥርዓተ ትምህርት በመቅረጽና የተለያዩ ሪፎርሞችን በመተግበር በትምህርት ሥርዓቱ ያጋጠሙ ስብራቶችን ለመጠገን ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በተሠራው ሥራ ተስፋ ሰጪ ምልክቶች እየታዩ ቢሆንም የአጠቃላይ ትምህርትን ተደራሽነት፣ ፍትሐዊነትና ጥራት ማረጋገጥ አሁንም ፈተና መሆኑ ይገለጻል።

ባለፉት ዓመታት በትምህርት ዘርፉ የተከናወኑ የሪፎርም ተግባራትና የተወሰዱ ርምጃዎችን በተመለከተ የዘርፉን ባለሙያዎችን ጠይቀን ሃሳባቸውን ሰጥተውናል፡፡

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ሥነ ባህሪ ኮሌጅ ዲን የሆኑት ሳሙኤል አሰፋ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት የትምህርት ጥራት ሳይሆን ለትምህርት ቤቶችና ለተማሪ ብዛት ትኩረት በመሰጠቱ የትምህርት ጥራትን ጎድቶታል፡፡

የትምህርት ዘርፍ ብዙ ሪፎርም የሚያስፈልገው ዘርፍ መሆኑን የሚናገሩት ሳሙኤል (ዶ/ር)፤ ከፈተና ጋር በተገናኘ ከዚህ ቀደም በነበረው የፈተና አሰጣጥ ተማሪዎች በቂ ዝግጅት ሳያደርጉ ፈተናውን አልፈው ዩኒቨርሲቲ የሚገቡበትና የሚመረቁበት ሁኔታ እንደነበር ያወሳሉ፡፡

አሁን ላይ ትምህርት ሚኒስቴር በፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱ እንዲሁም በአጠቃላይ በትምህርት ዘርፉ ላይ እየወሰደ ያለው የሪፎርም ሥራ ጥሩ መሆኑን ገልጸው፤ ሪፎርሙ ውጤታማ እንዲሆንና የትምህት ጥራት እንዲረጋገጥ ባለድርሻ አካላት በኃላፊነት መስራት እንደሚገባቸው ይገልጻሉ፡፡

‹‹ኩረጃን ለመከላከል የፈተና አሰጣጡን ማጠናከር ጥሩ ቢሆንም ብቻውን ግን የትምህርት ሥርዓቱን መጠገን አያስችልም›› የሚሉት ሳሙኤል(ዶ/ር)፤ ከታች ጀምሮ ትምህርት ቤቶችና የመምህራን አቅም ግንባታ ላይ ጠንካራ የሪፎርም ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ፡፡

መንግሥት በትምህርት ዘርፉ እያደረገ ባለው ሪፎርም ከፍተኛ ወጪ ቢያስወጣውም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መንገድ እስከመጨረሻው መሄድ ከተቻለ ወደፊት ውጤት እንደሚመጣ ይገልጻሉ፡፡

የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ ላይ የተደረገው የሪፎርም ትግበራ አስፈላጊ መሆኑን አውስተው፤ በዚህም በሚዘጋጁ መጽሐፍት ሀገር በቀል እውቀቶች እንዲካተቱ፣ ከተማሪው አቅም እና ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት እንዲኖር አስችሏል ነው ያሉት፡፡ የተጀመረው ሪፎርሙ ሙሉ ለሙሉ ውጤታማ እንዲሆንም ከፖለቲካዊ ጫናዎች ነጻ መሆን ይኖርበታልም ይላሉ፡፡

የዩኒቨርሲቲዎች ራስገዝነትን በተመለከተ በሌሎች ሀገራት የሚገኙ የዩኒቨርሲቲዎች ራስገዝ መሆናቸውን አውስተው፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ራስ ገዝ እንዲሆኑ መደረጉ የኢኮኖሚያዊ ነጻነት ብቻ ሳይሆን አካዳሚያዊ ነጻነት እንዲኖራቸው ስለሚረዳ የሚበረታታ ተግባር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስገዝ መሆኑን አውስተው፤ ነገር ግን ነጻነትቱን ተከትሎ ገቢ ለማመንጨት ሲባል ክፍያ ላይ ጭማሬ ሊኖር ስለሚችል በተማሪዎች ወይም በተማሪ ቤተሰብ ላይ ጫና እንዳይፈጥር ስጋት እንዳላቸውም ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ኮሚቴ ተዋቅሮ የጥድፊያ ነገር መመልከታቸውን ጠቁመው ፤መሰል አካሄዶች ታርመው በጥንቃቄና በጊዜ ሂደት ወደ ራስ ገዝ አሠራር መግባት እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆናቸው ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከልም ተቋማዊ ነጻነት፤ የሀብት ነጻነትና አካዳሚያዊ ነጻነት እንደሚገኙበት ይጠቅሳሉ፡፡

እንደ ሳሙኤል (ዶ/ር) ገለጻ፤ ዩኒቨርሲቲዎች ራስገዝ ሲሆኑ ሙሉ በሙሉ በራሳቸው ሀብት እንደሚተዳደሩና ለዚህም ሁሉም ተማሪዎች ለትምህርት የሚያስፈልገውን ወጪ ከፍለው የሚማሩ ስለሆነ የኢኮኖሚ አቅም የሌላቸው ተማሪዎች በእነዚህ ራስገዝ ዩኒቨርሲቲዎች አይማሩም በሚል የሚነሳ ሃሳብ ስህተት ነው ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች ራስገዝ ይሆናሉ ማለት ሥርዓት አልበኛ ይሆናሉ ማለት አይደለም ያሉት ሳሙኤል (ዶ/ር)፤ ሕግና ሥርዓትን ተከትለው በነጻነት ይሠራሉ ማለት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲዎች ገቢን በተመለከተ ከላይ እንደተገለጸው ራሳቸው በሚያመነጩትና ከመንግሥት በብሉግራንት (በድጎማ መልክ) በሚያገኙት ሀብት የሚተዳደሩ ይሆናሉ፡፡ መንግሥት በአዋጁ ውስጥ በግልጽ እንዳስቀመጠው ከፍለው መማር ለማይችሉ ብቃትና አቅም ላላቸው ተማሪዎች መንግሥት ይከፍላል ነው ያሉት።

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) 33ኛውን ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባዔ አስመልክተው እንደተናገሩት፤ የትምህርት ሥርዓቱን በአዲስና በጠንካራ መሠረት ላይ ለመገንባት ባለፉት ዓመታት የሪፎርም ሥራዎች መሬት እንዲይዙ በማድረግ ጉልህ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡

በዋነኝነት ትኩረት ተሰጥቶ የተተገበረው የመምህራን እና የርዕሰ-መምህራንን የሙያ ብቃት ማረጋገጥ ሲሆን ለ52 ሺህ 300 የሁለተኛ ደረጃ መምህራንና ለ8070 ርዕሰ-መምህራን በ28 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥልጠና መሰጠቱን ያነሳሉ፡፡

የሪፎርሙ አካል የሆነው ሀገር-አቀፍ በ12ኛ ክፍል ፈተና በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በወረቀትና በበይነ-መረብ ፈተናን ጎን ለጎን መስጠት ተችሏል፡፡ የመሠረተ ልማት ሥራን እና የኮምፒዩተሮች አቅርቦትን አጠናክሮ በማስቀጠል በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ በበይነመረብ ለመስጠት እየተሠራ እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡

በተጨማሪም በትምህርት ለትውልድ እንቅስቃሴ ከ27 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በማሰባሰብ የትምህርት ቤት መሠረተ ልማቶች እንዲሻሻሉ ተደርጓል፡፡ ከደረጃ በታች የሆኑ ትምህርት ቤቶችን ለማሻሻል የተጀመረውን የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡

ሌላኛው የሪፎርም አካል ከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሲሆን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቋማዊ ነፃነት ደንብ ጸድቆ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ተቋማዊ ነፃነትን ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ለማስፋት የሚያስችል ሥራ በቀጣይነት እንደሚተገበር አመላክተዋል፡፡ የትምህርት ፕሮግራሞች ዩኒቨርሲቲዎች ከተሰጣቸው ተልዕኮ እና ልየታ መስክ መሠረት የሚከለሱ ይሆናል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ በሰፊው የሚታዩትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዎቻችን ከአካባቢያዊነት የወጡ፣ በእውነት ሀገራዊ የዕውቀት ተቋማት እንዲሆኑ፣ የማስቻል ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር አስተዳደራዊ ሥራዎች ላይ ማሻሻያን ማድረግ ሌላው የለውጡ ተግባር ነው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴርን እንደተቋም ለሠራተኞች እና ለተገልጋዮች ውብ፣ ማራኪ፣ ምቹና ደህንነቱ የተረጋገጠ እንዲሆን የተጀመሩ ዓበይት ተግባራት መኖራቸውን አውስተዋል፡፡

የተጀመረው የሪፎርም ሥራ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የበለጸገች፣ ፍትሃዊና ሰላም የሰፈነባት፣ ለልማትና እድገት የምትተጋ ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚችል ትውልድ ማፍራትን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ ይህን ዓላማ የትምህርት ማህበረሰቡና አጋር ድርጅቶችን በጋራ ሆነን ልናሳካው ይገባል ነው ያሉት፡፡

በሥነ ምግባሩ የታነፀ ብቁና ተመራማሪ ትውልድ ለማፍራት የአጠቃላይ ትምህርትን ተደራሽነት፣ ፍትሐዊነት፣ ጥራትና ተገቢነት ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል። በተለይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ለሁሉም ደረጃዎች መሠረት በመሆኑ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሕፃናትን ሀገር ገንቢ ትውልድ አድርጎ መቅረጽ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን ጳጉሜን 2 /2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You