”ኢትዮጵያ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ሆና የሌሎችን እጅ መጠበቅ የለባትም” -ነገሰ ነገዎ የገዳ ቱለማ ሐዩ

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ሆና የሌሎች ሀገራትን እጅ መጠበቅ የለባትም ሲሉ የገዳ ቱለማ ሐዩ ነገሰ ነገዎ አስታወቁ፡፡ በተፈጥሮ ጸጋው ለመጠቀም ትውልዱ ለሥራ መትጋት እንደሚጠበቅበትም አመለከቱ፡፡

የገዳ ቱለማ ሐዩ ነገሰ፣ ከኢፕድ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ናት፡፡ በአብዛኛው ሊታረስ የሚችል መሬትም አላት፡፡ ይህን በተፈጥሮ የተቸረችውን ጸጋ ይዛ የሌሎች ሀገራትን ርዳታ መጠበቅ የለባትም፡፡

አሁን ጊዜው እንደድሮ አይደለም ያሉት ሐዩ ነገሰ፣ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ትከተለው የነበረ የአስተራረስ ዘዴ ምናልባት የሌሎችን ርዳታ እንድትጠብቅና አልፋም እንድትለምን ያስደረጋት ነበር ብለዋል፡፡

ምክንያቱም ድሮ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል ይታረስ የነበረው በበሬ ያውም በዓመት አንዴ የሚዘንበው ዝናብ እየተጠበቀ መሆኑን አስታውሰው፤ አሁን ግን እንደሱ አይነት አካሔድ እየተቀየረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

እርሳቸው እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት ብዙ ቦታ በሚባል ደረጃ እየታረሰ ያለው በትራክተር ነው፤ እርሻዎቹም ኩታ ገጠም እንዲሆኑ በመደረግ ላይ በመሆናቸው ለዚህ የአስተራረስ ዘዴ ምቹ እየሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ የኦሮሚያ ክልል ብዙ ለውጦች አሉ፡፡ አርሲ እና ባሌን ብንወስድ በአሁኑ ወቅት በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ኢንቨስተሮችም ሆኑ አርሶ አደሮች እርሻቸውን የሚያርሱት በትራክተር ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለግብርና ሥራ ምቹ የሆነ የአየር ጸባያ ያላት ከመሆኑም በተጨማሪ መሬቱም ውሃው ባልጠፋበት ሁኔታ ከሌላው ሀገር ድጋፍ መጠበቅ ኢትዮጵያን ክብር የሚያሳጣ መሆኑን ሐዩ ነገሰ አመልክተዋል፡፡

በተሰጠን የተፈጥሮ ጸጋ ለመጠቀም ትውልዱ አሁንም ለሥራ መትጋት ይጠበቅበታል ሲሉ ጠቅሰው፤ በተመቻቸው የተፈጥሮ ጸጋ ወጣቱ ሥራን ሳይንቅ የተለያዩ አትክልቶች እና ፍራፍሬዎችን ማምረት ቢችል ከፍተኛ ተጠቃሚ ይሆናል ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ መንግሥት ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ መሆኑን ገልጸው፤ መሥራት የሚችል ሁሉ ሠርቶ መለወጥ ይችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ሥራ ሠርቶ መለወጥ ለተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍል ብቻ የተሰጠ ስጦታ አለመሆኑንም አመልክተው፤ ኢትዮጵያ ከርዳታ ጠባቂነትና ከልመና መውጣት የምትችለው በዜጎቿ ጥረትና ትጋት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሐዩ ነገሰ፣ “ይህ እንደሚቻል ደግሞ በዓይናችን አይተናል፤ በጆሯችንም ሰምተናል፡፡ ኢትዮጵያ በመስኖ የስንዴ ምርት በማምረት ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ያመረተችውንም ወደ ውጭ ሀገር መላክ ጀምራለች ነው ያሉት፡፡

ይህም በሥራ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አረጋግጧል። ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻልም በተግባር ተመልክቷልና ከገባንበት ሰመመን መንቃት ችሏል፡፡ ይህ ተግባር ተጠናክሮ ቢቀጥልና ትውልዱም የሥራ ባህሉን እያዳበረ ቢመጣ ኢትዮጵያ አትለምንም፤ ርዳታ ጠባቂም አትሆንም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በሀገራችን በየትኛውም አካባቢ ባለ በባህሉ ሆነ በኃይማኖቱ ረገድ አትስራ የሚልም ሆነ እርስ በእርስ አትከባበር የሚል አስተምህሮም የለም ያሉት ሐዩ ነገሰ፣ ይሁንና እንደተባለው ትውልዱ ያንን ልማዳዊ ሕግ ላለማክበር ገሸሽ ሲል ይስተዋላል ብለዋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የራሱን ነገር ቸል ብሎ ወደ ውጭው ባህል በማዘንበሉ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን በባህላችንም ሆነ መልካም በሆኑ እሴቶቻችን ውስጥ የሌላውን አመለካከት እንዳይቀጥሉበት በመምከር ከሀገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች የሚጠበቅ ነው፡፡ የሃይማኖት አባቶች እና አባ ገዳዎች የየራሳቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው። ሥራ ፈትቶ የሚለምነውን አካል ልመና የሚያስጸይፍ ተግባር መሆኑን አስረግጠን ማስገንዘብ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

በተለይ ከሰዎች እጅ መጠበቅ አዋራጅም በራስ አለመተማመንንም የሚፈጥር መሆኑን ማስረዳት አለብን የሚመክር ካለ የሚመለስ ትውልድ አለ ሲሉም አመልክተዋል፡፡

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 20 /2016 ዓ.ም

 

Recommended For You