ጉባዔው ትክክለኛ የኢትዮጵያን ገጽታ በተግባር ለዓለም ያሳየ ነው

አዲስ አበባ፡- 4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ትክክለኛ የኢትዮጵያን ገጽታ በተግባር ለዓለም ያሳየ መሆኑን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ አስታወቁ፡፡

እ.አ.አ ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 3 ቀን 2025 በስፔን ለሚካሄደው 4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ቅድመ ጉባዔ በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ መጠናቀቁን አስመልክቶ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ እንደገለጹት፤ እ.ኤ.አ በ2015 3ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባዔ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡ በዚህም የአዲስ አበባ የድርጊት መርሃ ግብር አጀንዳ እየተባለ የሚጠራውን ሰነድ ጸድቋል፡፡ ሰነዱ ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር የተያያዘ ነው፡፡

4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ከመካሄዱ በፊት የአዲስ አበባ የድርጊት መርሃግብር አፈጻጸምን በአዲስ አበባ መገምገም አስፈላጊ ነው በሚል ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሃሳብ ተቀባይነት አግኝቶ በአዲስ አበባ መካሄዱ የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ ለዓለም ለማሳየት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የጉባዔው ተሳታፊዎች በተደረገላቸው መስተንግዶ ምስጋና አቅርበዋል ያሉት አምባሳደሩ፤ በቆይታቸው ደስተኞች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በልማት ጎዳና መሆኗንም ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በነበራት ችግር የተነሳ በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ ክሶች ነበሩባት፡፡ ነገር ግን ትክክለኛ የኢትዮጵያን ገጽታ በተግባር የሚታየው በልማት ሥራ ነው፡፡ ይህን አይነት ጉባዔ የኢትጵያን አቅምና ገጽታ በትክክል ያሳየ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

እንደ አምባሳደር ተስፋዬ ገለጻ፤ በጉባዔው ከ40 በላይ ሚኒስትሮችና አንድ ሺህ በላይ የተቋማትና የሀገራት ተወካዮች በመታደማቸው ለኢኮኖሚ መነቃቃት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ተሳታፊዎች በሙሉ ኢትዮጵያ ለጎብኚዎች ጥሩና ምቹ መዳረሻ መሆኗን እንዲያስረዱ የሚያደርግ ቆይታ አሳልፈዋል፡፡

ተሳታፊዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በመሆኑ ከገጽታ መቀየር ጀምሮ ለቱሪዝም ገቢ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ ኢትዮጵያ የሚነገር የልማት ታሪክ አላት፤ ይህንንም በሚገባ እንደተገነዘቡም አስረድተዋል፡፡

እንደ አምባሳደሩ ማብራሪያ፤ በጉባዔው ከታዳጊ ሀገሮች የልማት ፍላጎት አጀንዳ ጋር ተጣጥሞ የሚሄድት አሠራር ሊሰፍን እንደሚገባ ተጠይቋል፤ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓቱም እንዲስተካከል ጥያቄም እየቀረበ ነው፡፡

በአፍሪካ ውስጥ ልማት እንዳይኖር እዳ ትልቅ ፈተና በመሆኑ ታዳጊ ሀገራት ያለባቸው እዳ ለልማት በሚጠቅሙ መልኩ መቃለል እንዳለበት በጉባዔው መነሳቱን ጠቁመው፤ እ.ኤ.አ በ2025 ስፔን በሚካሄደው 4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በመሆን የአፍሪካን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ጉዳዮችን ይዛ እንደምትቀርብም ጠቁመዋል፡፡

ሞገስ ጸጋዬ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 20 /2016 ዓ.ም

 

Recommended For You