የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች መፍትሄ እየሰጠ ነው

አዲስ አበባ ፦ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ለተለያዩ ማህበራዊና ሀገራዊ ችግሮች መፍትሄ እየሰጠ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የሴቶች ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በ2016 ዓ.ም የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሀ-ግብር ለተሳተፉ ወጣቶች ሰሞኑን የምስጋናና የእውቅና መርሀ ግብር አካሂዷል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፤ የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ለሶስት ሳምንታት በሁሉም ክልሎችና መስተዳድር ከተሞች በመገኘት የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን ሲሠሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ከፍ የምትለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ልምድ ከፍ ሲል ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ባለፉት ዓመታት ሰፊ ትኩረት የተሰጠው የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም የተለያዩ ችግሮችን ለመፍታት ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን አንስተዋል።

በዘንድሮው የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሳተፉ ወጣቶች 80 መሆናቸውን ጠቁመው፤ ማህበረሰቡን በተለያዩ ዘርፎች በማገልገል፣ ወጣቱን በተለያዩ ጉዳዮች በማንቃት፣ ክልሎች ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተባባሪ እንዲሆኑና መንግሥትና ሕዝብን በማቀራረብ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል።

ዶክተር ኤርጎጌ እንዳመላከቱት፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከማገዙም በተጨማሪ የሀገር ፍቅር በተግባር የሚገለጽበትና ወጣቶች ማህበረሰባቸውን ለማገልገል እድል የሚያገኙበት ተግባር ሆኗል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ በበኩላቸው፤ የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አንዱ አካል መሆኑን አስረድተዋል።

የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ መካሄድ መጀመሩን አስታውሰው፤ በየአመቱ የተሳታፊዎች ቁጥር እያደገ መጥቷል ብለዋል።

የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶች የተለያዩ የሀገራቸውን ክፍል እንዲያውቁና አንዱ የአንዱን ባህልና ወግ እንዲረዳ በማድረግ አንድነትን ለመፍጠር የሚረዳ መሆኑን አንስተዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በወጣቶች የሥብዕና ግንባታ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ወጣቶች በተለይም በክረምት ወራት የሚኖራቸውን ሰፊ ጊዜ በአልባሌ ቦታ ከማዋል ይልቅ ህብረተሰቡን በማገልገል ማሳለፍ ይገባቸዋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሚኒስቴር ዴኤታዋ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ጥሩ የሚባል ጅምር ላይ የሚገኘው የበጎ ፈቃድ ሥራ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በታቀደው መልኩ እየተከናወነ ይገኛል።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 20 /2016 ዓ.ም

 

Recommended For You