በአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ላይ ወጣቱን ማሳተፍ ይገባል

አዲስ አበባ፡- በአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ላይ ወጣቱን በማሳተፍ በርካታ ለውጦች ማምጣት እንደሚገባ ተጠቆመ።

የአካባቢ ጥበቃና የውሃ ብክለትን መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ሥልጠና በሰርቪ ግሎባል አዘጋጅነት ለወጣቶች ተሰጥቷል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ውሃ ሀብት ኢንስቲትዩት መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ታዬ አለማየሁ፤ የአካባቢ ጥበቃና የውሃ ብክለትን መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ፅሁፍ አቅርበዋል።

በዚሁ ወቅት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ የዜጎች የኑሮ ደረጃና ቁጥር እያደገ በሚሄድበት ወቅት የውሃ ፍላጎት ይጨምራል ብለዋል።

በቆላማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከውሃና ከከብት ግጦሽ ጋር ተያይዞ በአርብቶ አደሮች መካከል የእርስ በእርስ ግጭቶች እየተቀሰቀሰ መሆኑን ለአብነት ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ጥቂት ኢንዱስትሪዎች ቢኖሩም እንኳን እነኝህ ፋብሪካዎች ወንዞችን ለፍሳሽ ማስወገጃነት እየተገለገሉባቸው መሆኑን የጠቀሱት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ይህ ተግባርም በዜጎችና በእንስሳት ላይ አደጋ እያደረሰ ነው ብለዋል።

አክለውም በዚህ ረገድ በሀይቆች አካባቢ በሚገኙ ፋብሪካዎችና ሆቴሎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ላይ ወጣቱ ከራሱ በመጀመር በርካታ ተግባራትን ሊያከናውን ይገባል ያሉት መምህሩ፤ ከጥቂት አስርት ዓመታት በፊት በተሰሩ ሃላፊነት የጎደላቸው ተግባራት በርካታ የውሃ አካላት በደለል በመሞላታቸው እየጠፉ መሆናቸውን አውስተዋል።

ኢትዮጵያ በቂ የውሃ ሀብት ያላት ሀገር ብትሆንም ዜጎቿ በውሃ እጦት እየተቸገሩ ሲሆን ካላት አጠቃላይ የውሃ ሀብት 97 በመቶው ከሀገር እንደሚወጣ ጠቅሰው፤ በአካባቢ ጥበቃ ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ጅምር ተግባራትን በይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማከናወን አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።

የሰርቪ ግሎባል ምክትል ካንትሪ ዳይሬክተር ታሪኩ ነጋሽ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ቁጥር ከ45 በመቶ በላዩ የወጣት ሃይል ነው። ይህ የወጣት ሃይል ለሀገርም ሆነ ለዓለም እድገት የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት ነው ያሉት።

በዚህም ሰርቪ ግሎባል በአየር ንብረት ለውጥ፣ በትምህርት፣ በወጣቶች አዕምሮአዊ ጤንነትና ሌሎችም ዘርፎች ላይ ከ2ሺህ በላይ ወጣቶችን እንደየፍላጎታቸው በማደራጀት ስለተለያዩ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ግንዛቤ እንዲያገኙ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ታሪኩ ገለጻ፤ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀግብር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ሌሎች የዓለም ሀገራትም ተሞክሮ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው። በዚህ ረገድ ጉዳዩን ወጣቱ ከወቅታዊነትና መዝናኛነት ከማየት ይልቅ የአየር ንብረት ለውጥ በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ተጽእኖ እንዲረዳው ማድረግ ያስፈልጋል።

የኢኮ-ጀስቲስ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር እስከዳር አውግቾ፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን ከውጭ ከመጠበቅ ይልቅ ሀገር በቀል እውቀቶችን በመጠቀም የማይበገር የአኗኗር ሁኔታን መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ተቋማት በተገቢው መንገድ የአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ ሳይዙ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣት የሚሄዱበት ርቀት ሀገርን እየጎዳ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ሁሉም ዜጋ ስለአካባቢ ጥበቃ የወጡ ሕጎችን በመገንዘብ መብቱን ሊጠይቅ እንደሚገባ አንስተዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You