ምርምሮችን ወደተግባር የመለወጥ ባህል ማዳበር ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፡- ምርምሮችን ወደተግባር የመለወጥ ባህል መዳበር ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ለዘርፉ ትብብር ሊደረግ እንደሚገባ በቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ የሪሰርችና የኖውሌጅ ማኔጅመንት ቢሮ ሃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ማትያስ ሽመልስ ገለጹ።

ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ የሚያዘጋጀው 18ኛው ሀገር አቀፍ የተማሪዎች ጥናትና ምርምር መድረክ ትናንት በተካሄደበት ወቅት ረዳት ፕሮፌሰር ማትያስ፤ ምርምሮችን ወደተግባር የመለወጥ ባህል መዳበር ለሀገር እድገት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

መድረኩ ዩኒቨርሲቲው “በተማሪዎች፣ ለተማሪዎች” ተነሳሽነት የተለያዩ ተቋማት ተመራቂዎች ጥናታዊ ጽሑፎቻቸውን እንዲያቀርቡ የሚጋብዝበት ሲሆን፤ በትናንቱ መርሃ ግብር ስምንት ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል።

በምርምር ማመን ያስፈልጋል፤ ውሳኔዎች ምርምርን ማዕከል ያደረጉ መሆን ይገባቸዋል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ማቲያስ፤ በማንኛውም ዘርፍ የተሰማሩ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ውሳኔ ሰጪዎች መረጃን መሠረት ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል።

ባህሉ ባለመዳበሩ በርካታ ምርምርና ጥናቶች ወደተግባር ሊለወጡ እንዳልቻሉ ጠቁመው፤ ተበጣጥሰው የሚገኙ ጥናቶችም የየራሳቸው ግኝቶች ስላላቸው ለውሳኔዎች፣ ለፖሊሲ ዝግጅቶ፣ ስትራቴጂ ለመንደፍ ለሚደረግ ተግባር አካል ሊሆኑ ይገባል ነው ያሉት።

ምርምሮች ሰፊ ልምድና እውቀት ባላቸው ፕሮፌሰሮች ጭምር ይሠራሉ፤ ጠቃሚ ምክረ ሃሳቦችንም ያስቀምጣሉ ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ነገር ግን የሚሠሩ ጥናቶችን ወስዶ ጥቅም ላይ በማዋል በኩል ክፍተቶች አሉ ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀው መድረክ ተማሪዎች ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን በንድፈሃሳብ የሚማሩትን የምርምር ክህሎት በተግባር እንዲተገብሩና የሠሯቸውን ምርምሮች በማቅረብ ብቃታቸውን እንዲያሳድጉ የሚረዳቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

መድረኩ ተመራቂዎች ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመመረቂያ ጽሁፋቸውን እንዲያቀርቡ የሚጋበዙበት፤ አዳዲስ ሃሳቦች የሚፈልቁበት፤ ተሳታፊዎቹ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂዎች እንደመሆናቸው አዳዲስ ጉዳዮችን የምርምራቸው አካል የሚያደርጉበት ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

አያይዘውም ስለ ካፒታል ገበያ፣ የባንክ አሠራርና የበይነመረብ ገበያን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮች ይዳሰሱበታል።ምርምር አቅራቢዎቹ ጉዳዮችን የሚመለከቱበት መንገድ ጠቃሚ ነው፤ እውቀትን ከማዳበር ባሻገርም ማህበረሰቡ በአዳዲስ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ እንዲኖረውና የእውቀት ሽግግር እንዲያደርጉ ያስችላል ብለዋል።

ተሳታፊዎች የሚያቀርቧቸው ምክረ ሃሳቦች ለፖሊሲ አውጪዎችና በቀጣይ በዘርፉ ምርምር ለሚያካሂዱ አካላት እንደግብአት እንዲያገለግሉ ታትመው ለሚመለከታቸው አካላት እንዲዳረሱ ይደረጋሉ ነው ያሉት።

ሃሳባቸውን ለመግለጽ፣ የመግባባት ብቃታቸውን ለማሳደግ እና በምርምር ያገኟቸውን እውቀትና ክህሎት ለሌሎች ለማስተላለፍ አጋጣሚን እንደሚፈጥርላቸውም ተናግረዋል።

በካፒታል ገበያ ዙሪያ የጥናት ጽሁፉን ያቀረበው ተማሪ አቤኔዘር ኪዳኔ፤ ባንኮች እርስ በእርስ ብድር እንዲወስዱ የሚፈቅደውና በቅርቡ የወጣው የብሄራዊ ባንክ ፖሊሲ መንግሥት በባንኮች መካከል ያለውን ግብይት እንዲመራ ያስችለዋል።ኢኮኖሚው ዝቅ የሚል ከሆነም ቀድሞ መገመት እንደሚስችል ነው የጠቆሙው።

የበይነመረብ ገበያን የሚመለከት ጥናት ያቀረበችው የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪ ኤልዳና አዳነ፤ ህብረተሰቡ የበይነ መረብ ገበያን እየለመደው መምጣቱን በጥናቷ መመልከቷን፤ ነገር ግን ማህበራዊ ሚዲያ ላይ እንደሚያተኩሩ ማስተዋሏን ጠቁማለች።የበይነ መረብ ገበያ እንዲለመድ ድርጅቶች ሊያስተዋውቁ እንደሚገባም መክራለች።

18ኛው ሀገር አቀፍ የተማሪዎች ኮንፍረንስ ዩኒቨርሲቲው በዓመት አራት ጊዜ ከሚያዘጋጃቸው ኮንፍረንሶች መካከል አንዱ ነው።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You