በአዲሱ በጀት ዓመት ለዜጎች ቀልጣፋ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትን ለመስጠት ታቅዷል

አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ በ2017 በጀት ዓመት የተጠናከረ ቅንጅታዊ አሠራርን በመዘርጋት ለዜጎች ቀልጣፋ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን ለመስጠት ማቀዱን የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቆንጂት ደበላ የጽህፈት ቤቱን የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም ከተጠሪ ተቋማት ጋር ትናንት ሲገመገም እንደገለጹት፤ በ2016 በበጀት ዓመት ለዜጎች የተቀላጠፈ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን በመስጠት ረገድ አበረታች ውጤቶች ታይተዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ያጋጠሙ ክፍተቶችን በማረምና ቅንጅታዊ አሠራሮችን በመዘርጋት በ2017 በጀት ዓመት ለዜጎች ቀልጣፋ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ለመስጠት በልዩ ትኩረት ለመሥራት ታቅዷል፡፡

በአዲሱ በጀት ዓመትም ተቋማትን በሰው ኃይል፣ በአሠራር፣ በአደረጃጀት እንዲሁም በቴክኖሎጂ በማጠናከር ዘመኑን የሚመጥን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ በትኩረት የሚሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ ወይዘሮ ቆንጂት ገለጻ፤ ባለፈው በጀት ዓመት በቴክኖሎጂ ተደግፈው የሚሰጡ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች በመጨመራቸውና ቅንጅታዊ አሠራሮች በመሳለጣቸው ምክንያት ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ተችሏል፡፡

በበጀት ዓመቱ ለፕሮጀክቶች ክንውን ልዩ ትኩረት መሠጠቱን ገልጸው፤ በዚህም አግልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል ውጤታማ ሥራዎች ተከናውኗል ብለዋል።

የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የነዋሪነት መታወቂያን ሙሉ ለሙሉ በዲጂታል ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፤ በከተማዋ የሚከሰቱ አደጋዎችን አስቀድሞ መከላከል እንዲቻል በተሠራው ሥራ የተሻለ ውጤት መገኘቱንም ገልጸዋል።

በኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት በበጀት ዓመቱ ውጤታማ ሥራ የተከናወነበትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት ጥረት የተደረገበት መሆኑን ምክትል ሥራ አስኪያጇ አብራርተዋል።

በዚህም የከተማዋን ገጽታ መቀየር መቻሉን ገልጸው፤ በቀጣይ ቀሪ ሥራዎች ለማከናወን በቅንጅት ይሠራል ብለዋል።

የከተማውን ነዋሪና ባለድርሻ አካል በማሳተፍ ጽዱና ማራኪ ከተማ ለመፍጠር በተከናወነ ተግባር አበረታች ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በጀት ዓመቱ ከተማዋ ውብ፣ ጽዱና ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን ለነዋሪው ምቹ በማድረግ ረገድ በተከናወነው ተግባራት ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን እና በህብረተሰቡም ዘንድ ጽዳት ባህል እየሆነ እንደሚገኝ ወይዘሮ ቆንጂት ተናግረዋል።

አዲስ አበባ ከተማን ከተለያዩ አደጋዎች መከላከል ላይ በተሠራው ሥራ ከ37 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ማዳን መቻሉን ጠቁመዋል።

በከተማዋ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የእሳት አደጋዎችን በተመለከተም ጠንካራ የቅድመ መከላከል ሥራ በመሠራቱ ጉዳቶችን መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል።

ጽህፈት ቤቱ ወላጆቻቸውን ላጡ ህጻናት ድጋፍ በማድረግ ለአቅመ ደካማ ዜጎች የቤት እድሳት በማከናወን ማህበራዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ መቆየቱን ተናግረዋል።

የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የመፍታትና ብልሹ አሠራሮችን መከላከል የቀጣይ ዓመት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አስረድተዋል።

መርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይም በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You