“ከጠለምት ወረዳዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን በመመለስ ሂደት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተልዕኮውን በብቃት ተወጥቷል”- የታዛቢ ቡድኑ አባላት

አዲስ አበባ፡- ከጠለምት ወረዳዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን በመመለስ ሂደት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተልዕኮውን በብቃት መወጣቱን የአማራ እና ትግራይ ክልሎች የታዛቢ ቡድን አባላት ተናገሩ።

ከሦስቱም የጠለምት ወረዳዎች ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ወደ ቀያቸው ሲመለሱ ማኅበረሰቡ በደስታ ተቀብሎ ሰላማዊ ኑሮ እንዲቀጥል መደረጉንም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል የጠለምት ወረዳዎች ተልዕኮ አፈፃፀም ታዛቢና ቅሬታ ሰሚ ዓባይ መንግሥቴ፤ ከፌዴራል መንግሥት እንዲሁም ከሁለቱ ክልሎች የተውጣጣ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቋሞ የተፈናቀሉ ዜጎችን የመመለስ ሥራ መሥራቱን ገልፀዋል።

የሁለቱ ክልሎች ታዛቢዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት በሕዝባዊ ውይይት በቀጥታ የስም ዝርዝር አስተችቶ በማረጋገጥ ተፈናቃዮችን የመመለስ ሥራው በተሳካ መልኩ ተከናውኗል ብለዋል።

በተፈናቃይና በተቀባይ ማኅበረሰብ መካከል የተናበበና የመረጃ ትክክለኛነት ተረጋግጦ ከሦስቱም የጠለምት ወረዳዎች ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል።

የተፈናቀሉ ዜጎችን በመመለስ ሂደት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተልዕኮውን በብቃት መወጣቱን አንስተው፤ በአካባቢው የሚነሱ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ በመመለስ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የተቀናጀ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ትዝብታቸውን አጋርተዋል።

በአካባቢው የነበሩ ታጣቂዎችን በማስወጣት መከላከያ ሠራዊት የአካባቢውን ሠላምና ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን መታዘባቸውንም አረጋግጠዋል።

በትግራይ ክልል የጠለምት ወረዳዎች ተልዕኮ አፈፃፀም ታዛቢ ታዘዘ ገብረስላሴ፤ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመመለስ መከላከያ ሠራዊት፣ የሁለቱ ክልሎች ተወካዮች፣ ከተፈናቃይና ተቀባዩ ማኅበረሰብ የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት የጋራ መድረክ መካሄዱን አስታውሰዋል።

በመድረኩ ላይ በተደረሰ የጋራ ስምምነት መሠረትም የመመለሱ ሂደት በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል ብለዋል።

በዚህም ነጋዴው ወደ ንግዱ አርሶ አደሩ ወደእርሻ ሥራው እንዲገባ መደረጉን መታዘብ እንደቻሉ አስረድተዋል።

የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተጠናከረ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግና ለዘላቂ ሰላም በጋራ በመሥራት ልማትን ማስቀጠል እንደሚገባ የታዛቢ ቡድኑ አባላት አስገንዝበዋል።

መንግሥትም በአካባቢው የሕክምና፣ የግብርና ግብዓትን ጨምሮ ሌሎችም መሠረታዊ አገልግሎቶችን የማሟላት ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በየአካባቢው ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥም ከኅብረተሰቡ የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በቅርበት እየሠሩ መሆኑን አንስተዋል።

የተፈናቀሉ ወገኖችን በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ በመመለስ ሂደት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላደረገው የላቀ አስተዋጽኦ ታዛቢዎቹ አድናቆትና ምስጋናቸውን አቅርበዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You