የራስን ፀጋ ማየት ያስቻለው የእሳቤ ለውጥ

መሐመድ ሲራጅ ይባላል። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን የምሥራቅ ስልጤ ወረዳ ነዋሪ ነው። ገና በለጋ ዕድሜው ራሱን ለመለወጥ በነበረው ፍላጎት ምክንያት ብዙ ነገሮችን ሞክሯል።

ራሱን ለመለወጥ በነበረው የሕይወት ትግል ድንበርን ተሻግሮ ሳዑዲ አረቢያ ዓመታትን እስከመከተም ደርሶ ነበር። በሰው ሀገር ሕይወት አልጋ በአልጋ አልሆነችለትም፤ እንዳሰበው ብልጽግናን በቀላሉ ማሳካት የሚቻልም አልነበረምና ወደ ትውልድ ቀዬው ተመለሰ።

ሥራ ጠባቂ ሳይሆን ሥራ ፈጣሪ መሆንን አልሟልና አካባቢው ላይ መማተር ጀመረ። በዚህም በክልሉ እየተተገበረ በሚገኘው የ30፣ 40፣ 30 የአትክልትና ፍራፍሬ ንቅናቄን መነሻ በማድረግ በሕዝብ ይዞታ በሆነ መሬት ላይ ሥራ አጥ ወጣቶችን አሰባስቦ አቮካዶ ወደ ማልማት ሥራ ገባ።

መሐመድ ያደራጃቸው ወጣቶች ንቅናቄውን መነሻ አደረጉት እንጂ በመጀመሪያው ዓመት 30፣ በሁለተኛው ዓመት 40 እንዲሁም በሦስተኛው ዓመት 30 የፍራፍሬ ችግኝ መትከል ይበቃናል አላሉም። ሥራውን አስፍተውት በአስር ሄክታር መሬት ላይ የሚያከናውኑ ሲሆን፣ ከጀመሩት ሦስት ዓመታትን አስቆጥረዋል።

አቮካዶ ተክሎ ወራትን አለፍ ሲልም ዓመታትን መጠበቅም አስፈላጊ ሆኖ አላገኙትም። በዚህም ክልሉ ላይ በሰፊው እየሠራበት ያለውን የተቀናጀ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ተግባራዊ እያደረጉ ነው። ይህም ከአቮካዶ ልማቱ ጎን ለጎን ጎመን፣ ቦሎቄና ቀይ ስርን ጨምሮ የተለያዩ አትክልቶችን ማምረት አስቻላቸው። ምርታቸውንም ከአካባቢያቸው አልፈው ለአጎራባች ወረዳዎችም ማቅረብ ጀምረዋል።

ዝቅ ብሎ ሰርቶ ከመለወጥ ይልቅ በአቋራጭ ለመበልጸግ ባለ የተሳሳተ ፍላጎት ምክንያት ብዙዎች በረሃ ቀርተዋል፤ የአውሬ ሲሳይም ሆነዋል የሚለው መሐመድ፤ አካባቢው ላይ እምቅ የመልማትና ሠርቶ የመለወጥ ጸጋ እያለ በአስተሳሰብ እና ዕይታ ችግር ምክንያት ለዓመታት በሰው ሀገር ያሳለፈውን ጊዜ በቁጭት ያስታውሰዋል።

ሳውዲ አረቢያ ነበርኩ፤ ይህን አይነት አፈር ማግኘት አይታሰብም። የሚታየው ጠጠር ብቻ ነው። ለወጣቶች ያለኝ መልእክት ሀገራችን ሁሉም ነገር ያላትና አንድ ነገር ያልጎደላት ነች። እዚህ ሀገር ላይ ዝቅ ብለን ከሠራን የማናሳካው ነገር የለም ይላል።

ውጪ በነበርኩበት ጊዜ አንድ አረብ ስለኢትዮጵያ ሲጠይቀኝ ስድስት ወር ዝናብ ስድስት ወር ደግሞ በጋ ነው የሚል ምላሽ ሰጠሁት የሚለው መሐመድ፤ እንዲህ አይነት ሀገር እያለህ ስደትን ለምን ምርጫህ ታደርጋለህ አለኝ። ይህም ቆም ብሎ እንዲያስብና ወደሀገሩ ተመልሶ ለመሥራት እንዲወስን እንዳደረገው ይገልጻል።

በህብረት መሥራታችን ትልቅ ጥቅም ፈጥሮልናል የሚለው መሐመድ፤ ከቀዬው ርቆ ክፉ ደጉን ማየቱ ከራሱ አልፎ ለብዙ ሥራ አጥ ወጣቶች ወደ ሥራ መግባት ምክንያት ሆኗል። የተቀናጀ አትክልትና ፍራፍሬ ልማቱም አንደኛውን ተክል በሽታ ቢያጠቃው እንኳን በሌሎች ተጠቃሚ እንድንሆን ያስችለናል ይላል።

በተጨማሪም በባለሙያዎች ለሚደረግ ክትትልና በዛ ያለ ምርት ለገበያ ለማቅረብም ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል ሲል ይገልጻል።

ዛሬም ድረስ ሥራ የለም በሚል ጊዜያቸውን በከንቱ የሚያባክኑ ወጣቶች መኖራቸውን የሚጠቅሰው መሐመድ፤ ልፋትና ትጋት ሳይኖር ውጤታማ መሆን አይቻል። ስለሆነም ወጣቶች አካባቢያቸው ላይ ያለውን ጸጋ መለስ ብለው መመልከትና ራሳቸውን ለመለወጥ መትጋት ይጠበቅባቸዋል ሲል ይመክራል።

አባቶቻችን ለዘመናት እዚህ ቦታ ነበሩ፤ ሆኖም የእውቀት፣ የአስተሳሰብና ያለንን ጸጋ ተረድቶ የመጠቀም ችግር ስለነበር አካባቢው ባለው ጸጋ ልክ አልበለጸጉም። ተጠቃሚም አልሆኑም። አሁን ላይ ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ በሚደረገው የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እንዲሁም በተፈጠረው የዕይታ ለውጥ ፀጋችንን መጠቀም ጀምረናል ይላል።

በቀጣይነትም ሥራውን ከዚህ በላይ አስፍተው የመሥራትና የመለወጥ ራዕይ አንግበው እየሠሩ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታን ጨምሮ የሚደረጉ ድጋፍና ክትትሎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

ሐምሌ 19 / 2016 ዓ.ም

Recommended For You