ሁለንተናዊ ስብዕናን ያሟላ ትውልድ ለመፍጠር የትምህርት አመራሩ ርብርብ ማድረግ አለበት

አዲስ አባባ፡- ሁለንተናዊ ስብዕናን ያሟላ ትውልድ ለመፍጠር የትምህርት አመራሩ ርብርብ ማድረግ እንዳለበት ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የ2016 የትምህርት ዘመን እቅድ አፈጻጸምና የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ከትምህርት ቤት አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር የማጠቃለያ ምክክር በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም አካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በመድረኩ እንደገለጹት፣ የተማሪ ውጤት ቢስተካከልም ሥነ ምግባር ካልተሻሻለ ሁለንተናዊ ሥብዕናው የተሟላ ትውልድን መገንባት አዳጋች ይሆናል። ሁለንተናዊ ሥብዕናን ያማሏ ትውልድ ለመፍጠር የትምህርት አመራሩ ርብርብ ይጠበቅበታል።

በትምህርት ዘርፉ የሚደረገው ጥረት ለሀገር ሸክም ያልሆነ፣ ትሩፋት ማምጣትና የችግር መፍትሄ ማፍለቅ የሚችል ትውልድ ለማፍራት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር እንደሆነም አስገንዝበዋል። በዚህም በቀጣይ የተማሪዎች ውጤትና ሥነ ምግባር ላይ ትኩረት ያደረጉ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የተማሪዎችን ውጤት በሚፈለገው ደረጃ ማሳደግ ያስፈልጋል ያሉት ኃላፊው፣ ይህንን ለማድረግ የነበሩ ክፍተቶችን የእቅድ አካል አድርጎ መሥራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

ከዚህም ባሻገር የቀዳማይ ልጅነትን በጨዋታ ላይ የተመሠረተ ሥነ ዘዴ ተግባራዊ እንደሚደረግ እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ወጥነት ያለው አሠራርም እንዲሁ በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።

በትምህርት ዘርፉ ወጥነት ያለው የተጠያቂነት ሥርዓትን በማስፈን ረገድ በተለይም ከክፍለ ጊዜ ብክነት፣ የተማሪና የመምህራን ሥነ ምግባር ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች ለመመለስ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል።

በመድረኩ ባለፉት ቀናት የተካሄዱትን የውይይት ጭብጦች ሪፖርት ያቀረቡ ክፍለ ከተሞች በመዲናዋ በ2016 የትምህርት ዘመን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ ቀድሞ ከነበረው በተሻለ ሁኔታ ተፈጻሚ መሆኑን አንስተዋል።

ትምህርት ቤቶች ሰላማዊና ደህንነታቸው ተጠብቆ ከፖሊስ ጥበቃ ውጪ በመሆን ያለምንም የጸጥታ ችግር ዓመቱን በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ማሳለፋቸው ለሥርዓተ ትምህርት ትግበራው አዎንታዊ ድርሻ እንደነበረው ተገልጿል።

በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚስተዋሉ አዋኪ ድርጊቶች ቢኖሩም አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች ከአዋኪ ድርጊቶች ነጻ መሆናቸውም ተመላክቷል።

በትምህርት ዘመኑ የመምህራንን የቤት ጥያቄ ለመፍታት የተሠሩ ሥራዎች፣ የብዙሃ ቋንቋ ትግበራ፣ የመጽሃፍ ህትመት፣ የኦንላይን ፈተና መጀመር ለመማር ማስተማሩ ስኬት ትልቅ ሚና እንደነበራቸውም ተጠቅሷል።

ዘርፉ ላይ የሚስተዋለው የሰው ሃይል እጥረት፣ የመምህራን የሙያ ብቃት ፈተና ለወጥ አለማምጣቱ፣ አንዳንድ የትምህርት አይነቶች ላይ ያሉ የመጽሃፍ እጥረት፣ የተማሪ የክፍል ጥምርታ፣ የግብዓት አቅርቦት እጥረት፣ የኑሮ ውድነት ጫና፣ የርእሳነ መምህራን ጥቅማጥቅም ጉድለትና መሰል ችግሮች መኖራቸው ጠቅሰዋል። እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም በመድረኩ ተነስቷል።

የውይይት መድረኩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) የመሩት ሲሆን፣ ከማጠቃለያ ውይይቱ በኋላም ተሳታፊዎች በመዲናዋ የተከናወኑ የኮሪደር ልማቶችን ጎብኝተዋል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም

Recommended For You