መተግበሪያው ዜጎችን ያሳተፈ የወንጀል መከላከል ሥራ እንዲሠራ አስችሏል

አዲስ አበባ፡- በቅርቡ ወደ ሥራ የገባው የዜጎች ተሳትፎ የሞባይል መተግበሪያ (EFPapp) ዜጎችን ያሳተፈ የወንጀል መከላከል ሥራ ለመሥራት እና ፖሊስ ይበልጥ መረጃ መር እንዲሆን ማስቻሉን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ። መተግበሪያው ወደ አገልግሎት ከገባ ወዲህ ከአንድ ሺህ 452 በላይ የወንጀል ጥቆማዎች ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFPapp) በመጠቀም የተገኙ የወንጀል ድርጊቶችን በተመለከተ ትናንት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት በፌዴራል ፖሊስ የቴክኖሎጂ ማስፋፊያ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደምሴ ይልማ እንደገለጹት፤ መተግበሪያው ዜጎችን ያሳተፈ የወንጀል መከላከልና መረጃ መር ሥራ እንዲሠራ አስችሏል።

መተግበሪያው ተግባራዊ ከተደረገ አንስቶ 682 ለፌዴራል ፖሊስ እና 770 ለአዲስ አበባ ፖሊስ ጥቆማዎች ደርሰዋል ያሉት ኮማንደር ደምሴ፤ ይህም መተግበሪው የፖሊስን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ኮማንደር ደምሴ እንደገለጹት፤ በዜጎች ከደረሱ ጥቆማዎች መካከል አብዛኛው ተገቢውን ምላሽ ተሰጥቶ፣ የተወሰኑት በሂደት ላይ ናቸው። 10 የሚሆኑት ግልጽ ያልሆኑና ማስረጃ ያልተገኘላቸው ሆነው ተገኝተዋል።

ኮማንደር ደምሴ ፤ መተግበሪያው ፖሊስ የሚሠራቸው ሥራዎች ከማቅለል በተጨማሪ ወንጀል የተፈጸመባቸው ዜጎች ፈጣንና ትክክለኛ ውሳኔ እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ዜጎች ሰው ሰራሽም ይሁን ተፈጥሯዊ ጉዳቶች ሲያጋጥሙ መረጃ ለፖሊስ የሚያደርስበት እንዲሁም ፖሊስም መረጃውን ተጠቅሞ ተገቢውን ምላሽ የሚሰጥበት ነው ያሉ ሲሆን በተጨማሪም ጥቆማውን የላከው አካል ጉዳዩ ከምን እንደደረሰ መከታተል የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።

እንደ ኮማንደር ደምሴ ገለጻ፤ ከመተግበሪያው ጎን ለጎን 991 ነጻ የጥሪ ማዕከል በሀገር አቀፍ ደረጃ የፖሊስ የጥሪ ማዕከል እንዲሆን እየተሠራ ነው። ፌዴራል ፖሊስና አዲስ አበባ ፖሊስ ላይ ተግባራዊ ተደርጓል።

መተግበሪያው መረጃዎቹ በምስል፣ በድምጽና በተንቀሳቃሽ ምስል ማቅረብና ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የተሰጣቸውን ተልዕኮ ላልተገባ ዓላማ የሚያውሉ የፖሊስ አባላት መከታተል የሚያስችል መሆኑንም ነው ኮማንደር ደምሴ ያስረዱት።

በተጨማሪም ተጠያቂነትን በማስፈን መረጃው እንደተላከ ለየትኛው ፖሊስ ጣቢያ ነው የሚቀርበው የሚለውን ለመለየት፣ ጥቆማው የደረሰው ኃላፊ በአግባቡ መሥራቱን አለመሥራቱን ለማወቅ እንዲሁም ሁነት በሚካሄድበት ጊዜ ከማዕከል ሆኖ እርምት መስጠት ያስችላል።

መተግበሪያው በሱማሊኛ፣ በአፋርኛ፣ በትግሪኛ፣ በአማርኛ እና በኦሮሚኛ ቋንቋዎች ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ኮማንደር ደምሴ አመላክተዋል።

ፌዴራል ፖሊስ ወንጀልን በጋራ መከላከል የሚያስችለውን የዜጎች ተሳትፎ የሞባይል መተግበሪያ ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱ የሚታወስ ነው።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም

Recommended For You