አዋሽ ባንክ 11 ነጥብ 6 ቢሊዮን ትርፍ አገኘ

የቅርንጫፎቹን ብዛት 947 አድርሷል

አዲስ አበባ፡- አዋሽ ባንክ በ2016 በጀት ዓመት 11 ነጥብ 6 ቢሊዮን ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ ባንኩ በትናንትናው እለት ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት 11 ነጥብ 6 ቢሊዮን ትርፍ አግኝቷል።

የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው፣ የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 300 ቢሊዮን መድረሱንና በበጀት ዓመቱ 11 ነጥብ 6 ቢሊዮን ትርፍ ማግኘቱንም አስታውቀዋል።

የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ 232 ቢሊዮን የደረሰ መድረሱን ገልጸው፤፣ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ45 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ወይም በ24 በመቶ እድገት ማሳየቱንም ገልፀዋል።

ባንኩ ማሰባሰብ የቻለው የውጭ ምንዛሪ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ26 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ ያሳየ መሆኑንም ተናግረዋል።

አዋሽ ባንክ ወደ ባንክ ኢንዱስትሪ የገባ የመጀመሪያው የግል ባንክ መሆኑን አስታውሰው ፤ በየጊዜው ከሕዝቡ ባገኘው አመኔታ የተነሳ ተከታታይነት ያለው እድገት እያስመዘገበ ይገኛል ብለዋል።

ሥራ አስፈጻሚው እንዳሉት፣ ባንኩ ተደራሽነቱን ለማስፋትና የህብረተሰቡን የባንክ ተጠቃሚነት ለማስፋት ባለፈው በጀት 74 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት የቅርንጫፎቹን ብዛት 947 አድርሷል።

ከዚህም በተጨማሪ፣ ደንበኞች የ24 ሰዓት ሙሉ የባንክ አገልግሎት የሚያገኙባቸውን ከ10 በላይ በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ ዲጂታል ቅርንጫፎችን በአዲስ አበባና በተለያዩ ትላልቅ ከተሞች ከፍቶ የተሟላ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ባንኩ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በሚሠራቸው ሥራዎች በየዓመቱ በ100 ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያወጣል ያሉት አቶ ፀሐይ፣ ባለፈው በጀት ዓመትም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ለበርካታ ዜጎች የመኖሪያ ቤቶችን ሠርቶ ማስረከቡን ጠቅሰዋል።

የፈጠራ ክህሎት ኖሯቸው የፋይናንስ አቅም ያጠራቸው ዜጎችን በመደገፍ ረገድ ባንኩ ጠንካራ ሥራ እየሠራ መሆኑንም አንስተዋል። በዚህም፣ ከ5ሺህ በላይ ሥራ ፈጣሪዎች ተሳታፊ የሚሆኑበት “ታታሪዎቹ” የሥራ ፈጠራ ውድድር በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑንም አንስተዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከኢትዮጵያ ምርጥ ባንክ በመባል በብቸኝነት በግሎባል ፋይናንስ መጽሔት መመረጡንና ከዓለም አቀፍ ባንከሮች ከኢትዮጵያ የዓመቱ ምርጥ ኮሜርሻል ባንክ በመባል ዕውቀና ማግኘቱን ያነሱት ሥራ አስፈጻሚው፤ ያለፈው በጀት ዓመት ለባንኩ ስኬታማ ዓመት ነበር ብለዋል።

ባንኩ በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የሚያስችለውን አቅም ለመገንባትና ስኬቱን የበለጠ ለማላቅ የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚሠራም ነው ሥራ አስፈጻሚው ያስታወቁት።

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You