“ከኮሚሽኑ ምስረታ በኋላ ኢትዮጵያን በጸጥታው ምክር ቤት አጀንዳ ለማድረግ ምክንያት አይኖርም” -ፕሮፌሰር መኮንን አያና

አዲስ አበባ፡- ከናይል ተፋሰስ የትብብር ኮሚሽን ምስረታ በኋላ ኢትዮጵያን በውሃ ምክንያት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አጀንዳ አድርጎ ማቅረብ ምክንያት እንደማይኖር በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሀብት ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር መኮንን አያና አስታወቁ።

ፕሮፌሰር መኮንን አያና ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በሐምሌ ወር በ2016 ዓ.ም መጀመሪያ ደቡብ ሱዳን የናይል ስምምነት ማዕቀፍን ስድስተኛ ሀገር በመሆን በፓርላማ አጽድቃለች። በዚህም ከ11 የናይል ተፋሰስ ሀገራት ውስጥ ስድስት ሀገራት በፓርላማ በማጽደቃቸው ቋሚ የናይል ተፋሰስ ሀገራት ኮሚሽን ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ መግባት የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ከኮሚሽኑ ምስረታ በኋላም ኢትዮጵያን በጸጥታው ምክር ቤት አጀንዳ ለማድረግ ምክንያት አይኖርም።

ኮሚሽኑ መመስረት በጋራ ውሃውን ማስተዳደር፣ መጠቀም፣ ቀጣይነት ያለው ጥበቃን ለማድረግና መረጃን የመቀያየር መብትን እንደሚሰጥም ገልጸዋል።

እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ፤ ኮሚሽኑ ከተመሠረተ በኋላ አንዳንድ ሀገራት በተናጠል ተሰሚነት አለኝ በሚል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ በየሀገራቱ ኢትዮጵያን አጀንዳ አድርጎ የሚያቀርቡበት ምንክንያት ውሃ አያነሳም። ኮሚሽኑ በዓለም ደረጃ እውቅና ስለሚኖረው በተናጠል እየዞሩ ስም ማጥፋት፣ የተሳሳተ መረጃ መልቀቅ፣ በተናጠል የመጠቀም ፍላጎትንና ኢትዮጵያ ላይ ጫና መፍጠር እየቀነሰ ይመጣል።

የኮሚሽኑ መመስረት ውሃው የአንድ ሀገር ብቻ ሳይሆን የተፋሰሱ በሙሉ መሆኑን ያረጋግጣል ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ኮሚሽኑ ውሃን በትብብርና በፍትሐዊነት መጠቀምን የሚቆጣጠርና ሕጋዊ በማድረግ ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

እንደ ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ ግብጽ፣ ሱዳን፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያልፈረሙ ሀገራት ሲሆኑ የኮሚሽኑ ምስረታ እውን ሲሆን ቀስ በቀስ ኮሚሽኑን የሚቀላቀሉ እንደሚሆን ይጠበቃል። ከዚህ ውጭ የሚደረጉ ጥረቶች ተሰሚነት አያገኙም፤ ስድስት ሀገራት የተስማሙበትን ስምምነት አልስማማም ማለት አያዋጣም። የኮሚሽኑን ምስረታም ወደ ኋላ መመለስ አይችሉም ።

ተመራማሪው እንደሚሉት፤ የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እ.ኤ.አ ከ1999 እስከ 2008 ለአስር ዓመታት በናይል ተፋሰስ ሀገሮች መካከል መተማመን እንዲኖር ሰፊ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የዓባይን ውሃ በጋራ፣ በእኩልነትና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ መጠቀምና አብሮ መንከባከብ የሚያካትት ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የሚተዳደሩባቸውን መርሆዎችን ጭምር ያካተተ ማዕቀፍ አለው ብለዋል።

የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የሚተዳደሩበትን መርሆዎችን ያካተተ ነው ያሉት ፕሮፌሰር መኮንን፤ ግብጽ ከሕጉ ውስጥ ውሃን በምክንያታዊነትና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚሉት አሠራሮች እንዲነሱ ስትከራከር እንደቆየችና በዚህ ፈንታም ‹‹የውሃ ደህንነት›› በሚል እንዲተካ በማድረግ በቅኝ አገዛዝ ወቅት የነበሩትን የውሃ አጠቃቀምን የሚያካትት፣ የሚያከብርና እውቅና የሚሰጥላቸውን አንቀጽ ማካተተ ይፈልጋሉ ነው ያሉት።

ይህ ደግሞ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት በግዛታቸው ውስጥ ያለውን ውሃ እንዳይጠቀሙ የሚያደርግና እውቅና የማይሰጥ በመሆኑ ተቀባይነት አለማግኘቱን ጠቅሰዋል።

ኮሚሽኑ የግድ የሚመሠረት ከሆነ ደግሞ ለግብጽ ድምጽን በድምጽ መሻር መብት እንዲሰጥ ይሻሉ ያሉት ፕሮፌሰር መኮንን፤ ነገር ግን የትኛውም የተፋሰሱ ሀገራት ይህን እንደማይቀበሉት አብዛኛው የተፋሰሱ ሀገራት የትብብር ማዕቀፉን በምክር ቤቶቻቸው በማጸደቅ አረጋግጠዋል ነው ያሉት።

ከግብጽ ፍላጎት ውጪ በሆነ መልክ ኮሚሽኑ እውን እየሆነ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትና ኮሚሽኑ ግብጽ እንዲካተቱ የምትፈልጋቸውን አግላይ ሕጎችን ያልተቀበለ ነው። እንዲሁም የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ አቋም የሆነውን በቅኝ አገዛዝ ወቅት የተፈረሙ ውሎች ኢትዮጵያን አይገዙም የሚለውን አቋሟን ሕጋዊ መሠረት የሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።

ሞገስ ጸጋዬ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You