ከሶስት ሺህ በላይ በአደጋው ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች የሠብዓዊ ድጋፍ ተደርጓል

  • 100 የመጠለያ ድንኳኖች ተተክለዋል

አዲስ አበባ፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተትና ናዳ አደጋ ከሶስት ሺህ በላይ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች የ5 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የሚገመት የሠሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ። ለተፈናቃዮች የሚውል 100 የመጠለያ ድንኳኖች መተከላቸውንም ተመላክቷል።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግኑኙነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አታለለ አቡሀይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ በአደጋው ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ሶስት ሺህ ወገኖች የሚውል የ 5 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የሚገመት የሠብዓዊ ድጋፍ አድርጓል።

እንደ አቶ አታለለ ገለጻ፤ ድጋፉ 520 ኩንታል እህል እንዲሁም አልባሳት፣ መመገቢያና ማብሰያ ቁሳቁሶችን ያካተተ ነው። በአደጋው 600 ሰዎች ተፈናቅለዋል። ለተፈናቃዮች የሚውል 100 የመጠለያ ድንኳን ተተክሏል።

ኮሚሽኑ በሳውላ ከተማ በሚገኘው የአደጋ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል በኩል የሕይወት አድንና የሥነልቦና ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ አታለል፤ ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያምን (ዶ/ር) ጨምሮ ከተለያዩ የፌዴራል ተቋማት የተውጣጣ ቡድን አደጋው ወደ ተከሰተበት ቦታ ድረስ ለጎጂዎች አጸናንተዋል ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን በበኩሏ፤ በክልሉ ጎፋ ዞን፣ ገዜ ጎፋ ወረዳ፣ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ነው። በአሁኑ ወቅት አስከሬን የመፈለጉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የአስቸኳይ አደጋ ጊዜ መልሶ ማቋቋሚያ ኮሚቴ ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ እያከናወነ ይገኛል።የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር እና ከአጎራባች ክልሎች እና ዞኖች የተውጣጡ ባለሙያዎች በሥፍራው በመገኘት ለተጎጂዎች በርካታ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እንደ ወይዘሮ ሰናይት ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት ከአደጋው የተረፉና የተፈናቀሉ ወገኖችን በአካባቢው በሚገኙ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማትና ትምህርት ቤቶች በጊዜያዊነት የማስጠለልና የዕለት ደራሽ ምግብ የማቅረብ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

የተጎዱ ዜጎችን መደገፍና የነፍስ አድን ሥራ ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል ያሉት ወይዘሮ ሰናይት፤ በአከባቢው ተጨማሪ ጉዳት እንዳይከሰት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚደረገው ሠብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ቀበሌ ሐምሌ 15 ቀን 2016 በደረሰው የመሬት ናዳና መንሸራተት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉ ይታወቃል።

በአደጋው ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ሠብዓዊ ድጋፍና ነፍስ የማዳን ሥራ በተለያዩ አካላት ርብርብ እየተካሄደ ይገኛል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፌ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች አደጋው በደረሰበት ቦታ በመገኘት አጽናንተዋል።

የክልሉ መንግሥትና የአካባቢው ነዋሪዎች በአሁኑ ጊዜ የነፍስ አድንና ተጨማሪ አደጋ እንዳይከሰት ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን በርብርብ እያከናወኑ ነው። እንዲሁም ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሚደረጉ የሠብዓዊ ድጋፍ ሥራዎችም በቅንጅት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You