
እኖር ኤነር፦ የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር በጉራጌ ዞን እኖር ኤነር መገር ወረዳ የ12ኛ ዙር የችግኝ ተከላ መርሃግብር አካሂዷል።
ማኅበሩ መርሃ ግብሩን ያከናወነው “ጉዞ ወደ አረንጓዴ ልማት” በሚል መሪ ሃሳብ ነው።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንደሻው ጣሰው በመርሃ ግብሩ እንደገለጹት፤ በመርሃ ግብሩ የሚተከለው ችግኝ ብቻ ሳይሆን ሰላም፣ ፍቅርና አብሮነትን በመሆኑ ሕዝቡ በአንድነት በችግኝ ተከላው ዐሻራውን ሊያኖር ይገባል።
ክልሉ በግብርና ዘርፍ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ እየሠራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ እንዳሻው፤ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያን ከተረጂነት ለማውጣት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም አረንጓዴ ዐሻራ ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
እንደ አቶ እንደሻው ገለጻ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀግብር እንደሀገር ከተረጅነት ለመውጣት እየተደረገ ላለው ጥረት፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና የአየር ንብረትን ለመጠበቅ ያግዛል።
በሁሉም የልማት ሥራ የክልሉ ሕዝብ በንቃት ሊሳተፍ እንደሚገባ ገልጸው፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ የጽድቀት መጠናቸውን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ሺሰማ ገብረሥላሴ በበኩላቸው፤ ማህበሩ የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን ለመሸፈን ላለፉት 11 ዓመታት ሕዝቡንና አባላቱን በማስተባበር በርካታ ችግኞችን ተክሏል።
ማህበሩ በዘንድሮ የ12ኛ ዙር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከ20 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞችን መትከሉን ገልጸዋል።
በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ምክንያት ለሚያጋጥሙ አደጋዎች የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረኮችን በማዘጋጀት ወገንተኝነቱን አሳይቷል ብለዋል።
ማህበሩ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ፣ የውሃ ተቋምና መሰል የመሠረተ ልማት ሥራ ሲሠራ መቆየቱን አስረድተዋል።
የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በበኩላቸው፤ ህብረተሰቡ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ በማሳደግ ለውጤት በማብቃት ረገድ ተሳትፎውን በማጠናከር እንደ ሀገር የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት መረባረብ አለበት ብለዋል።
በክልሉ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በርካታ ችግኞች ተዘጋጅተው በአሁኑ ወቅት የተከላ ሥራው በተለያዩ ዞኖችና ከተሞች በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ አርሶ አደሩ በዝናብ እጥረት ምክንያት ሲያጋጥመው የነበረውን ችግር መቅረፍ መቻሉን ገልጸዋል።
በችግኝ ተከላ መርሃግብሩ ላይ የፌዴራል፣ የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የልማት ማህበሩ አጋሮች፣ ደጋፊዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
በዘንድሮው ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከት ታቅዶ ከሰኔ ወር ጀምሮ ተከላ መጀመሩን የሚታወስ ነው።አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም