ላምበረት አካባቢ ባለፈው እሁድ ማታ ነው። ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር በመንደር መሃል ባሉ የኮብልስቶን መንገዶች ውስጥ እየሄድን ነው። ወደ ዋናው መስመር ልንገባ ትንሽ ሲቀረን በመንደሮች መሃል ባለው መንገድ ላይ ሰዎች ተሰባስበዋል።
አንድ ወጣት በከፍተኛ ድምጽ ይናገራል፤ አንድ አባት አንገታቸውን ደፍተው ያዳምጡታል። ሌላው ሰው ግራና ቀኝ ሆኖ ግማሹ ያዳምጣል፤ ግማሹም ተመስጦ የራሱ ዓለም ውስጥ ነው። ልክ አጠገባቸው ስንደርስ የአረቄ ቤት በር ነው። በሩ ላይ የተመሰጡት ሰዎች የልጁን ምክር እያዳመጡ ሳይሆን በራሳቸው ዓለም ውስጥ ናቸው።
ፍጥነታችንን ከመቀነስም አልፈን ቆም አልን። ወጣቱ ልጅ በኃይል እየተናገረ የነበረው አባቱን ነው። አባቱ መሆኑን ያወቅንም ጠይቀን ሳይሆን በሚናገራቸው ነገሮች ነው። ልጁ ቁጣ የቀላቀለ ምክር ያወርደዋል።
በአባትየው ተደጋጋሚ አረቄ ቤት መሄድ የተሰላቸ ይመስላል። ‹‹ዝም ብልህ እኮ ትንሽ ቆይተህ ደግሞ ሴተኛ አዳሪ ቤት ነበር የምትገኝ!›› ብሎም መረር ያለች ቃል ተናገረ። ይሄ ሁሉ ሲሆን አሁንም አባትየው አንገታቸውን ደፍተው ፀጥ ብለው ያዳምጣሉ። አይቆጡም ወይም አጥፍቻለሁ ማረኝ አይሉም።
ከሁኔታው እንደተረዳነው አባትየው ከዚህ በፊትም ‹‹ተው›› ተብለው ያልተዉ ናቸው። ልጅየው እናቱ በዚህ ድርጊት እንደተሰላቹ ይናገራል። ወደ ምክሩ ሲመለስም ‹‹አንተ አረቄ ለአረቄ ቤት እየሄድክ እኔም ጠጪና አጫሽ ብሆን ‹ተው› ትለኝ ይሆን?›› እያለ አባቱን የምጸት ጥያቄ ይጠይቃል።
በዚሁ ሁኔታ ውስጥ ከአባትየው አንዲትም ቃል ሳንሰማ እጃቸውን ከኪሳቸው ከተው፤ አንገታቸውን ደፍተው ወደ ዋናው አስፋልት ከሚያስወጣው መንገድ በተቃራኒ ሄዱ (ወደ ቤታቸው መሰለን)። ልጁም ቁጣ ከቀላቀለ ንግግሩ ለዘብ ብሎ ምክር ብቻ እያወራ ተከተላቸው። እኛም ወደመንገዳችን ሄድን።
ሁለቱንም ነው ያመሰገንኳቸው። እንዲያውም ከአባትየው ልጀምር። በነገራችን ላይ አባትየውን ሳመሰግን ከጓደኛዬ ጋር የተለያየ ሀሳብ ስለያዝን እየተከራከርን ነበር። እንዴት በዚህ ዕድሜያቸው፤ ለዚያውም ቤተሰብ እያላቸው ይጠጣሉ ነው የጓደኛዬ ወቀሳ። ይሄ ግልጽ ነው። ቤተሰብ እያላቸው ለዚያውም በስተርጅና ከአረቄ ቤት እየተፈለጉ መምጣት አልነበረባቸውም።
ከዚህ በተጓዳኝ ግን አንድ ያመሰገንኩባቸው ነገር አለ። ሰውየው ልጃቸው ሲመጣ በጣም ነው ያፈሩት፤ በጣም ነው የተጸጸቱት። ያ ልጁ ሲናገረው የነበረው ሁሉ እውነት ነው ብለው ተቀብለዋል ማለት ነው። እርግጥ ነው ከድርጊታቸው ካልታቀቡ ፀባይን ማሳመር ብቻ የቤተሰቡን ጥያቄ አይመልስም። ግን ደግሞ ከሌላው ሰካራም ሁሉ ይለያሉ።
የሰካራም ትልቁ ችግሩ እኮ ገንዘብ ማጥፋቱ ብቻ ሳይሆን ቤት ገብቶ መበጥበጡ ነው። ምንም እንኳን ሰውየው ቤት ሲገቡ ምን እንደሚሉ ባናውቅም ልጁ ሲቆጣቸው ካሳዩት ዝምታ ተነስተን ግን እዚያም ምንም እንደማይሉ መገመት ይቻላል።
ሰውየውን ማመስገን የፈለኩት የሚያስመሰግን ሥራ ሰርተው አይደለም፤ መጠጥ ቤት መገኘት ምኑም አያስመሰግንም (ለዚያውም በዚያ ዕድሜያቸው)። ከእርሳቸው የሚጠበቅ መካሪነትና አስተማሪነት፤ አርዓያነት ነው።
ያመሰገንኩባቸው ግን አንድ ነገር አለ፤ ይህንኑም አድርገው ከልጁ ጋር ‹‹ምን አገባህ!›› በሚል ወደ ስድድብ አለመግባታቸው። ልጃቸው ከመጠጥ ቤት ገብቶ ‹‹ውጣ!›› ሲላቸው ሹልክ ብለው መውጣታቸው ቢያንስ በከፊል አያስመሰግናቸውም?
ወደ ልጅየው ስንመጣ ትልቁ ምስጋና ለእርሱ ነው። አስቡት! ወጣት ነው። ወጣቶች በምን እንደሚታሙ የምናውቀው ነው። በመጠጥና በሌሎች አደንዛዥ ሱሶች የተጠመዱ ናቸው። ከእናትና አባት ተደብቀው መጠጥ ቤት ይሄዳሉ፤ ይህ የነገርኳችሁ ገጠመኝ ግን በተቃራኒው ነው። ልጅየው መጠጥ ቤት ተገኝቶ አባትየው ሊያስወጡት መጥተው ቢሆን ኖሮ ብዬ አሰብኩ፤ ምናልባትም ‹‹አሻፈረኝ›› ማለቱ አይቀርም ነበር።
ልብ አላልንም ወይም አጋጣሚውን አላገኘን ይሆናል እንጂ እንዲህ አይነት የልጅ አዋቂ፣ የልጅ አሳቢ፣ የልጅ መካሪዎችም አሉ። እንዲያውም እኮ የተማረ መሃይም ሆነን እንጂ ከአዛውንት አባቶች የተሻለ ዕድሜያችንን በትምህርት ያሳለፍን ወጣቶች ነበር አይደል? አባቶች ወጣት በነበሩበት ዘመን አሁን ያለው ሰፊ የትምህርት ዕድል አልነበረም፤ እንዲህ በቴክኖሎጂ የረቀቀና የፈጠነ አልነበረም።
ጊዜያቸውን በትምህርት ላይ ስለማያሳልፉ መጠጥ ቢለምዱ አይደንቅም። አስደናቂ የሚሆነው ግን የዚህ ዘመን ወጣት ይሄ ሁሉ አማራጭ እያለው ጊዜውን መጠጥ ቤት ሲያሳልፍ ነው።
በነገራችን ላይ አዲስ አበባ ውስጥ ስለሆነ እንጂ ገጠር አካባቢ ብዙ ጊዜ ጠጪዎች አባቶች ናቸው። ልጅ አባቱን ‹‹ለምን ትጠጣለህ?›› እያለ ሲመክርና ሲቆጣ ነው የሚታየው። አዲስ አበባ ውስጥ ግን አባትና እናት ልጃቸውን ሲቆጡና ሲቆጣጠሩ ነው የሚታየው። ይህ የሆነው ደግሞ ሱስ ቦታ የሚገኙ ከአባቶች ይልቅ ልጆች ስለሆኑ ነው።
ወጣቶችም ሆኑ አባቶች እንዲህ ቢሰማሙና ቢመካከሩ ሁሉም ነገር ይሰምር ነበር።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22/2011