
ምንም ታላቅ በሆነችና በታሪኳ በገነነች ኢትዮጵያ ብንኖርም ያለንበት ድህነት ግን የሚደበቅ አይደለም። በማንኛውም መስፈርት ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበት ደረጃ አይመጥናትም። በኩሩ ህዝቦቿ ከባድ መሰዋዕትነት ነጻነቷን አስጠብቃና ቅኝ ሳትገዛ መኖሯ እውነት ቢሆንም አሁንም ድረስ በድጋፍና በእርዳታ የቆመች አገር መሆኗም አይካድም።
ስለሆነም እንወዳታለን የምንል ከሆነ የሚመጥናት ደረጃ ላይ ልናደርሳት ከእኛ ክሀዝቧቿ ብዙ ይጠበቃል። የምንቆረቆርላት ከሆነም ከህዝቦቿ ችግርና ሰላም ማጣት እንደ እግር እሳት ሊያንገበግበን ይገባል። አገሩ ሳትከብር የሚከብር፤ አገሩ ሰላሟ ሳይረጋገጥ ሰላምን የሚጎናጸፍ ማንም ኢትዮጵያዊ እንደማይኖርም ከልብ ልናምን ይገባል።
ኢትዮጵያና ህዝቦቿ አሁን ያሉበት ደረጃ እንቅልፍ አጥተን እንድንሰራ የሚያደርግ ነው። አሁንም ድረስ ትምህርት ቤት ጠፍቶ በዳስ የሚማሩ፤ ህክምና ብርቅ የሆነባቸው፣ መጫሚያ አጥተው ባዶ አግራቸውን የሚሄዱና ዳቦ ያረረባቸው በርካታ ዜጎች አሉን። ወርሃዊ ፍጆታን በደመወዝ መሸፈንም የሰማይ ያህል የራቃቸው ብዙ ዜጎችም የእኛው ወገን ኢትዮጵያውያን ናቸው።
ይነስም ይብዛም ከዚህ አሰከፊ ሁኔታ ለመውጣት በየቦታው ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም በእዚህ ጥረት ላይ እሳት በመለኮስ የኋልዮሽ የሚጎትቱንና ድህነታችንን የሚያባብሱ ዜጎችም አልጠፉም። በዚህ ዘመን የውጪ ወራሪና አደናቃፊ የለብንም። ስለሆነም ለድክመታችንም ሆነ ለጥንካሬያችን ከእኛ ውጪ ማንም ኃላፊነትን አይወስድልንም።
ይህን ሁሉ መነሻ እንድንደረድር ያነሳሳን ጉዳይ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአገራችን የተከሰተው አሳዛኝና ሊደገም የማይገባው ድርጊት ነው። መፈናቀሉ እየቀነሰና የተፈናቀሉ ዜጎች ወደየቀያቸው እየተመለሱ ነው የሚሉ ዜናዎችን እየሰማን እሰይ አገራችን ተረጋጋችልን እያልን በነበረበት ሰሞን ያለምንም ምክንያት በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ኢሰብኣዊ ግድያ ልብን ይሰብራል።
እንኳን በእረፍት ቀን በሥራ ቀናት እንኳን በየመጠጥ ቤቱ ተኮልኩሎ የጃንቦ እጀታ የጨበጠ በርካታ ሰው ማየት እንግዳ ነገር ባልሆነበት በዚህ ወቅት በግፍ የተጨፈጨፉት እነዚህ ወገኖቻችን እስከ ምሽት ድረስ በሥራ ላይ ነበሩ። እኒህ ሰማዕታት ተረክበውት የነበረው ታላቅ ኃላፊነትና የአገራቸው ሁኔታ እንኳን እረፍትን ሊያሳሰብ ራሰንም እስከመጣል የሚያደርስ ስለሆነም ነበር እንዲህ እንዲተጉ ያደረጋቸው።
ይሁንና ከዚህ በተቃራኒው በቆሙና እኩይ እኩዩ እንጂ በጎ ነገር ማየት በማይሆንላቸው ጨካኞች አሳዛኝ ጭፍጨፋ ተካሂዶባቸዋል። ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያውያን እንዲህ ዓይነት ወንጀል ሲፈጸምባቸው ከማየት በላይ ምን የሚያም ነገር ይኖራል? ይህን ሁኔታ አስመልክቶ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ በአስክሬን ሽኝቱ ወቅት “አገራቸውንና ህዝባቸውን ባገለገሉና ሁሉን ባዳመጡ ለምን ይገደላሉ” ሲሉ በእንባ ታጀበው ሃሳባቸውን የገለጹበት መንገድ እጅግ ውስጥን ይነካል። ለአገር መልፋትና መድከም ፈጽሞ ማሰገደል የለበትም፤ አይኖርበትምም። ግን ደግሞ ከአዕምሯቸው ይልቅ በነፍጥ በሚያስቡ ሰዎች ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ተፈጠረ።
የማንፈልገው ቢሆንም የሆነው ሆኗል። ሰማዕታቱንም አገር አክብሮና አልቅሶ ሸኝቷቸዋል። የዚህ የግፍ ተግባር አስተባባሪም የተገደሉ ሲሆን ከተባባሪዎቻቸውም አብዛኛዎቹ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ይሁንና እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ልንረሳ የማይገባን አንድ ጉዳይ አለ። በተዘጋጀልን የጥፋት አጀንዳና ድርጊት ተጠልፈንና በአሉባልታ ተነድተን ከልማት ስራችን አለመስተጓጎል።
ለማናችንም ግልጽ እንደሆነው በዚህ ክረምት ሊሰሩ የታቀዱ በርካታ ወሳኝ ተግባራት አሉ። ይህ የክረምት ወቅት የግብርና ስራችን የሚፋጠንበት፣ አራት ቢሊዮን ችግኞች የሚተከሉበት፣ ችግረኛ ተማሪዎችና አዛውንቶች የሚደገፉበትና ትምህርት ቤቶችና አቅም ያጡ ዜጎች መኖሪያዎች የሚታደሱበት ነው።
ስለሆነም ሁላችንም ጀነራል ሰአረ፣ ሜጀር ጀነራል ገዛዒ፣ ዶክተር አምባቸው፣ እዘዝ ዋሴና ምግባሩ ከበደ ነን በሚል መርህ በእነዚህ ቅዱስ ተግባራት ላይ እንሳተፍ! ይህንንም በማድረግ ሰማዕቶቻችንን ህያው እናድርጋቸው እንላለን!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22/2011