የግል ድርጅቶች ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት በመመሪያና ደንቦች ዙሪያ ግንዛቤ ሊፈጠርላቸው ይገባል

አዲስ አበባ፡- የግል ድርጅቶች ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት በመንግሥት በመመሪያና ደንቦች ዙሪያ ላይ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ የኢትዮጵያ አሠሪ ፌደሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን ገለጸ።

የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር የግል ድርጅት ሠራተኞች የጡረታ መዋጮ አዋጅን አስመልክቶ ለኢትዮጵያ አሠሪ ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በትናንትናው እለት አካሂዷል።

የኢትዮጵያ አሠሪ ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጌታሁን ሁሴን (ኢ/ር) እንደገለጹት፤ የግል ድርጅቶች በሚሰማሩበት ዘርፍ ያሉ የመንግሥት ደንብና መመሪያዎችን አውቀው ማኅበራዊ ኃላፊነቶቻቸውን የመወጣት ግዴታ አለባቸው።

ይህንን አስመልክቶ በግሉ ዘርፍ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን የገለጹ ሲሆን መመሪያዎቹን የሚያወጡ ተቋማት የአተገባበር ላይ ግንዘቤ እየፈጠሩ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

ለአብነትም የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር አሠሪዎች የሚተገብሯቸው በርካታ አዋጆች ቢኖሩትም በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ባለመስጠቱ በርካታ የግል አሠሪዎች ለተለያ ችግሮች እየተጋለጡ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ፕሬዚዳንቱ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት መንግሥት የሀገሪቱን የኢንቨስትመንት መመሪያዎችን ማሳወቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የግል ድርጅት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሠረት ዘለቀ ከዚህ ቀደም የጡረታ ገቢ የሚያገኙት የመንግሥት ሠራተኞች ብቻ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ግን ማንኛውም ከአንድ በላይ ሠራተኛ ቀጥሮ የሚያሠራ አሠሪ ከሠራተኛው ላይ የጡረታ መዋጮ እንዲቆርጥና እንዲያስገባ የሚያስገድድ አዋጅ መኖሩን ገልጸዋል።

ይህም በግል ድርጅት ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞችን እፎይ የሚያስብል መሆኑን ገልጸው፤ ነገር ግን በርካታ አሠሪዎች አዋጁን ባለመገንዘብ ለቅጣት እየተዳረጉ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አስተዳደሩ ይህንን ችግር ለመፍታትም ከተለያዩ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

አቶ መሠረት በአሁኑ ጊዜ የጡረታ መዋጮ የመክፈል አስገዳጅ አሠራሮች በመፈጠሩ ምክንያት በርካታ መሻሽሎች መኖራቸውንና አብዛኛው የሚባለው የግል ድርጅት የጡረታ መዋጮን እየከፈለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You