ደራሲና ተርጓሚ አውግቸው ተረፈ በሞት ተለይቶናል። ነፍስ ይማር! አውግቸው ተረፈ ማነው? ያልተነገረ ታሪኩስ? እነሆ ቁንፅል ታሪክ፤ ይህ ደራሲ የሦስት ስሞች ባለቤት ነው፤ ንጉሤ ሚናስ፣ ኅሩይ ሚናስ እና አውግቸው ተረፈ። ንጉሤ ወላጆቹ ያወጡለት ስም ነው። አጎቱ ኅሩይ ብለው ሰየሙት። “አውግቸው”ን መርካቶ መጻሕፍ ሲነግድ ራሱ ለራሱ እንደቀልድ ያወጣው ስም ነው። በኋላም “አውግቸው ተረፈ”ን እንደ ብዕር ስም ይጠቀምበት ጀመር። አውግቸው ተረፈ በቢቸና አውራጃ በ1943 ተወለደ።
አውግቸው የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው በጎጃም ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናት ነበር። በ1960ዎቹ ጎጃምን ለቅቆ ወደ አዲስ አበባ አቀና። በወር ሦስት ብር እየተከፈለው ቀጨኔ መድኃኔዓለም ቅኔ ትምህርት ቤት በመምህርነት ገባ። በራሱ አንደበት፣“… ቀጨኔ መድኃኔዓለም ገባሁና አልስማማኝ ሲል ወደ ቅድስት ማርያም ሄድኩ። እዚያ አንድ ጓደኛዬን ስላገኘሁት ቅድስት ማርያም ዝም ብዬ ተቀመጥኩ። ቅድስት ማርያም ለአንድ ዓመት ያህል ተቀመጥን። የተማሪዎች ማደሪያ ነበር። ቅዳሴ እንማራለን ብለን ተመልሰን ገባን። እየተማርንም እያቋረጥንም ቁጭ አልን። ከዚያ ከቅድስት ማርያም አባረሩንና ለ6 ወር በረንዳ እያደርን ቁራሽ እየለመን እናድር ነበር። ከዚያ እኔ ወደ ጡረታ ሰፈር መጣሁና ከአንድ ዓይነ ስውር ጋር እሱን እየመራሁ ለሁለት ዓመት ተቀመጥኩ። ከዚያ በኋላ ከሌላ ዓይነ ስውር ጋር አለቃ ነቢየ ልዑል ከሚባሉ ዘንድ በወር 12 ብር ቀጠሩኝና እሳቸውን እየመራሁ ቢሮ ስለነበራቸው መጻሕፍ ቅዱስ … ያስተምሩ ስለነበር መጻሕፍ ቅዱስ እያነበብኩላቸው፣ እየጻፍኩላቸው፣ እየመራኋቸው ለአንድ ዓመት ቁጭ አልኩ።”
አውግቸው መጻሕፍ መነገድ የጀመረው በጓደኛው ጥቆማ እንደነበር ይናገራል። ከመጻሕፍ ንግዱ ጎን ለጎን ዘመናዊ ትምህርቱን በንጉሡ ወልደጊዮርጊስ ትምህርት ቤት በማታ ፕሮግራም ከ3ኛ ክፍል ጀመረ። በ1985 ዓ.ም ለ“እፎይታ” መፅሔት እንደተናገረው፣ “ግማሽ የቀን ፣ ግማሽ የማታ እየተማርኩ 12ኛን ክፍል ከጨረስኩ በኋላ ዩንቨርሲቲ የመግባት ዕድል አገኘሁ። ይሁን እንጂ ገና የአንደኛ ዓመት ተማሪ እያለሁ ወቅቱ የኢህአፓ እንቅስቃሴ ስለነበር እኔም የኢህአፓ አባል በመሆኔ ትምህርት መማር የለብንም በሚለው የትግል አቋም አቋርጨ ወጣሁ። ከዚያ በቃ ወደ መጻሕፍ ንግድና ወደ ሌላ ሥራ ተሰማራሁ።”
በ1974 ዓ.ም በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት በአርታኢነት ተቀጠሮ ለሰባት ዓመታት ያህል ሠርቷል። አውግቸው የአዕምሮ ህመም የጀመረው በዚህ ወቅት እንደሆነ ይናገራል፣ “እኔ የታመምኩት ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ስሠራ ከጧት ጀምሮ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ድረስ ያለማቋረጥ አነብ ስለነበር… ነው።”
የአውግቼው ተረፈ የመጀመሪያ ጽሑፍ “እነ ወተቴ” የሚል አጭር ልቦለድ ነው። በ1972 ዓ.ም ነበር የጻፈው። አውግቸው ያልታተሙና የጠፉ ሥራዎቹን ጨምሮ ከ20 በላይ መጻሕትን የጻፈና የተረጐመ ጸሐፊ ነው። ጥቂት የማይባሉ ድርሰቶች ጠፍተውበታል። በአንድ ወቅት ስብሐት ገብረእግዚአብሔር እንዳለው፣ “አንድ ጊዜ ርዕስ የሌለው ረዥም ልቦለድ ደርሶ አንብቤ፣ ከመጠን
በላይ ተገርሜበት በኋላ ጉድጓድ ጣለው።”እጅግ ሰፊ እንዲሁም ረጅም ከሆነው የደራሲው ህይወት ለመታሰቢያነት የተቀነጨበ።
ደራሲና ተርጓሚ አውግቸው ተረፈ ከሠራቸው ሥራዎች መካከል ”ወይ አዲስ አበባ”፣” እብዱ ” እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው።
የአጫጭር ልቦለዶች ደራሲና ተርጓሚ አውግቸው ተረፈ ለአራተኛ ጊዜ በተካሄደውና ለአገራቸውና ለወገናቸው ላቅ ያለ አገልግሎት የሰጡ ዜጎች በሚከብሩበት የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት መርሐ ግብር ላይ ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በአቤል ሲኒማ አዳራሽ የዓመቱን የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚ እንደነበር ይታወሳል::
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2011
አብርሃም ተወልደ