በአገሪቱ በብዙ አካባቢዎች የሰላም መደፍረስ እና የፀጥታ ችግሮች በመኖራቸው የህብረተሰቡን በሰላም ተንቀሳቅሶ የመሥራት እና የመኖር ህልውና ሲፈታተን ቆይቷል። በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው የሰላም መደፍረስ ክፉኛ ከጐዳቸው ዘርፎች መካከል ትምህርትና ቱሪዝም ዋነኛው መሆናቸው ይጠቀሳል። ትምህርት የአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ (ምጣኔ ሀብታዊ)፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዕድገትና ብልጽግና ኅብለ ሰረሰር ነው።ይሁን እንጂ ከሌሎች አገሮች በተለየ ሁኔታ የትምህርት ጥራት መጓደል ለዓመታት ተገቢው ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል።በዚህም ምክንያት በአገሪቱ የትምህርት ጥራት ከድጡ ወደ ማጡ እያሽቆለቆለ ይገኛል።እስከአሁን በተደረገው እንቅስቃሴ ትልቅ ትኩረትና ሽፋን አግኝተው የቆዩት ብዛትና ተደራሽነት ናቸው።ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ያስችላል የተባለው የትምህርት ፍኖተካርታ ዝግጅት እየተካሄደ ይገኛል።
መንግሥት ለህዝቡ ከሚያቀርበው አገልግሎቶች አንዱ ትምህርት እንደሆነ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 90 /1987 የተጠቀሰ ሲሆን፣ ይኼንንም ሕግ መሠረት በማድረግ በተለያየ ጊዜ የወጡትን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ማለትም እ.ኤ.አ. በ1948 ለሁሉም ዜጋ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ማግኘት፣ በ1991 እና በ2010 የአገሪቱ ልጆች የመማር መብት እንዳላቸውና በተለይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት በጥራት ማግኘት እንዳለባቸው የሚሉትን በትምህርት ፖሊሲ ውስጥ በማካተት፣ የአገሪቱን የትምህርት ክፍል በመዋለ ሕፃናት፣ በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ፣ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠናና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመክፈል ትምህርቱ ለተማሪዎች፣ ለወላጆች፣ ለቀጣሪዎች፣ በአጠቃላይ ለኅብረተሰቡና ለአገሪቱ ጥቅም እንዲሰጥ ታሳቢ በማድረግ አደራጅቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ግጭቶች የተነሳ የትምህርት መቋረጥ በተደጋገሚ ሲያጋጥም ነበር።ይህ ደግሞ በትምህርት ጥራ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉ አይቀርም።በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በሚነሱ ግጭቶች የትምህርት ጥራት መጓደሎች እየተስተዋሉ ይገኛሉ።በተያዘው በጀት ዓመት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት በርካታ ሥራዎች ቢሠሩም የተፈለገውን ያክል ውጤት ማምጣት አልቻሉም።ለዚህ ደግሞ ከአመራር ቁርጠኝነት እስከ በተቋማት ውስጥ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነቶች መጥቀስ ይቻላል።በተማሪዎች መካከል የሚኖሩ መተሳሰቦችን የሚያሳድጉ ሥራዎች በብዛት አለመከናወን ለግጭት መባባስ ዓይነተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል።የግጭቶቹ መባባስ ደግሞ የትምህርት መቆራረጦች እንዲፈጠር በማድረጉ የትምህርት አሰጣጡ በተፈለገው የጊዜ ሰሌዳ እንዳይከናወን እንቅፋት ፈጥሯል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችም በዋናነት ከውጭ የፖለቲካ አጀንዳዎችና ከተማሪዎች አገልግሎት ጋር በተያያዙ በሚነሱ ጥያቄዎች ምክንያት የመማር ማስተማር ሂደቱን እያወኩ ይገኛሉ።በተለይም በተማሪዎች መካከል ማንነትን መሰረት አድርገው የሚነሱ ግጭቶችን ተከትሎ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። የአካል ጉዳት ከመድረሱም በተጨማሪ ንብረትም ወድሟል። በዚህ ክስተትም የመማር ማስተማር ሂደቱን ከመስተጓጎሉም ባሻገር ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች ለደህንነታቸው በመስጋት ወደየመጡበት ለመመለስ ሲገደዱ፤ ሌሎች ደግሞ ስጋት ውስጥ ሆነው በየተቋማቱ ባልተረጋጋ መንፈስ እየተማሩ ይገኛሉ።
በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ወረታው ሞትባይኖር፤ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርት የሚሰጡት ባስቀመጡት ካላንደር ነው።በዓመቱ ምን መከናወን እንዳለበት ያስቀመጡት ቋሚ የሆነ እቅድ አለ።ነገር ግን በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱ ግጭቶች እዚህ ካላንደር ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ።መሰጠት ያለባቸው የትምህርት ዓይነቶች በአግባቡ ስለማይሰጡ መምህራን ላይ እንቅፋት ይፈጥራል።ይህንን ለመቅረፍ ተቋማት የተቋረጡ ትምህርት ክፍለ ጊዜዎች እንዲካካሱ ማድረግ ተጨማሪ ጊዜ የሚፈልጉ ከሆነ ደግሞ ቀን ጨምሮ መሸፈን አለበት።
እንደ አቶ ወረታው አባባል፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የትምህርት መቋረጦች የትምህርት ጥራት ላይ ምን ዓይነት ችግር እንዳለ ለማወቅ ቀደም ብሎ የተማሪዎች ውጤት መታየት አለበት።አሁን ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውም ውጤት አብሮ መታየት አለበት።እንደ አገር ሲታይ ግን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ አለመረጋጋት ሲኖር በተማሪዎች ላይ የስነልቦናና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ያመጣል።በተለይ በፈተና ወቅት ተረጋግተው እንዳያነቡና ትምህርታቸው ላይ በተገቢው ትኩረት እንዳያደርጉ ተፅዕኖ ያደርግባቸዋል።
የትምህርት መቆራረጦች ሲኖሩ መምህራን ጊዜያቸውን በአግባቡ አይጠቀሙም የሚሉት አቶ ወረታው፤ ለምሳሌ ማስተማር ባለባቸው ጊዜ ሳያስተምሩ ቀኑ እየተገፋ ሲሄድ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ይናገራሉ።በተባለው ጊዜ ማስተማርና መፈተን ካልቻሉ ተማሪዎቹና መምህራን ላይ ጫና ይፈጥራል።ይህ ደግሞ ትምህርት ጥራቱ ላይ ችግር እንደሚፈጥር ይገልፃሉ።በአገሪቱ ሲታይ ትምህርት መጀመር ያለበት መስከረም ተብሎ ቢታቀድም በተግባር ግን ህዳር ወይም ታህሳስ ላይ እንዲጀመር ይደረጋል።አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በመሀል ችግሮች ሲፈጠሩ በማስተማር ሥራው ላይ ትልቅ ችግር ያመጣል።ትምህርት አሰጣጡን ወደ ክረምት እንዳይገፋ ደግሞ አገሪቱ ላይ የበጀት እጥረት እንዳለ ያመላክታሉ።
በቀጣይ የትምህርት ጉዳይ አሳሳቢ በመሆኑ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካላት ከቤተሰብ ጀምሮ ግልጽ የሆነ ውይይት እና ያሉ እውነታዎች የማሳወቅና እያንዳንዱ የያገባኛል ስሜት ሊፈጥር እንደሚገባ ይጠቅሳሉ።ይህ ሁኔታ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወይም ደግሞ በትምህርት ሚኒስቴር ብቻ የሚፈታ ጉዳይ አይደለም።እያንዳንዱ ከቤተሰብ ጀምሮ ጣልቃ ገብቶ መሠራት እንዳለበት ይጠቁማሉ።
በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኑነትና ኮሙንኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደስአለው ጌትነት በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በአገሪቱ በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የትምህርት መቆራረጦች አሉ።በተቋሙ ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው የትምህርት መስጫ ሰሌዳ ከጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እስከአሁን ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል።በመሀል ሁለት ጊዜ በግጭት ምክንያት ማለትም በህዳር ወር መጨረሻና በታህሳስ ወር መጀመሪያ ሁለት ቀን እንዲሁም ከግንቦት 19 ቀን ጀምሮ እስከ 22/ 2011 ዓ.ም ትምህርት ተቋርጦ ነበር።ከዚህ በተጨማሪ ተማሪዎች በራሳቸው የትምህርት ጊዜን ያቆራርጣሉ።የመጀመሪያው ተማሪዎች ትምህርት የሚያቆራርጡት የዓመት በዓላትን ምክንያት በማድረግ ነው።ለምሳሌ በፋሲካ በዓል ወቅት ከበዓሉ በፊት አንድ ሳምንት እንዲሁም ከበዓሉ በኋላ አንድ ሳምንት ትምህርት ዘግተው ነበር። በዚህ ተማሪዎች ሙሉለሙሉ ትኩረታቸውን ትምህርት ላይ አላደረጉም።በዚህም ተማሪዎች የፈተና ጊዜ ይራዘም በሚል ችግር እየፈጠሩ ይገኛሉ።
እንደዚህ ዓይነት ነገሮች የተቋሙን የሥራ እንቅስቃሴ እያስተጓጎሉ ይገኛሉ የሚሉት አቶ ደስአለው፤ የተቋሙ የሥራ ሂደት በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው የማይሄድ ከሆነ የመጀመሪያው የትምህርት ዘመን በአግባቡ እንዳ ይጠናቀቅ ያደርጋል። በዚህም የትምህርት ጊዜውን ጠብቆ ለማስኬድ በተቋሙና በተማሪዎች መካከል አለመግባባቶች ይፈጥራሉ።የትምህርት ጊዜያት በተቀመጠው መሰረት መካሄድ እንዳለበት ያብራራሉ።የትምህርት መቆራረጦች ሲኖሩ በተማ ሪዎችና በመምህራን ላይ ጫና ይፈጥራሉ።በመጀመሪያ መምህራን ላይ ጫና የሚፈጠረው በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ትምህርቱን መጨረስ ስለማይችሉ በፍጥነት ለማስኬድ ሲጥሩ የሚፈጥረው ጫና መሆኑን ይገልፃሉ።ትምህርቱን በአጭር ጊዜ ለመሸፈን ሲሠራ የሚያስፈልጉ ማብራሪያዎች በአግባቡ ላይቀርቡ ይችላሉ።በዚህ ጊዜ ትምህርቱ በአግባቡ ባለመሸፈኑ ተማሪዎች በአግባቡ እውቀት እንዳያገኙ እንደሚያደርግ ይገልፃሉ።
እንደ አቶ ደስአለው ገለፃ፤ በቀጣይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ካላንደር ሊከበር ይገባል።አገሪቱ ሰላም ሆና በየአካባቢው ያለውን ሰላም በማስተካከል ተማሪዎች ቀደም ብለው የሚገቡበት፣ የትምህርት ጊዜ ያለምንም መሸራረፍ የሚካሄ ድበት መንገድ መፈጠር አለበት።ሌላው መምህራንና ተማሪዎች ቅድሚያ ኃላፊነት በመውሰድ የትምህርት ሰዓት እንዳይሸራረፍ መሥራት አለባቸው።ተማሪዎች ለመማር ዝግጁ ሆነው በሰዓቱ መገኘት እና መምህራኑም በተመሳሳይ ለማስተማር ተዘጋጅቶ መምጣት ይጠበቅበታል።በመሀል ክፍተት ቢፈጠር ክፍተቱን ለመሙላት በመነጋገር ማስተካከል አለባቸው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2011
መርድ ክፍሉ