በተለያዩ መድረኮች፣ ቃለ መጠይቆች እና ውይይቶች ‹‹እገሌ የሙሉ ጊዜ ደራሲ ነው›› ሲባል እንሰማለን። ወይም ‹‹እገሌ የሙሉ ጊዜ ደራሲ መሆን አለበት›› የሚል ማበረታቻ የሚመስል ምክረ-ሀሳብ ሲሰጥ እንሰማለን። የሙሉ ጊዜ ደራሲ መሆን የአንድ ደራሲ ስኬት እንደሆነ ተደርጎ ሲነገርም እንሰማለን። አንድ ደራሲ ትልቅ ወይም የተዋጣለት ደራሲ የሚባለው የሙሉ ጊዜ ደራሲ ሲሆን ነው ማለት ነው።
ለመሆኑ ግን የሙሉ ጊዜ ደራሲ ማለት ምን ማለት ይሆን? የባለሙያ ማብራሪያ የሚያስፈልገው ያን ያህል ውስብስብ ነገር አይመስለኝም። የሙሉ ጊዜ ደራሲ ማለት በአጭሩ መደበኛ ሥራው እና መታወቂያው መጽሐፍ መጻፍና ማሳተም የሆነ ማለት ነው። በሙሉ ጊዜው የሚያነብና የሚጽፍ ማለት ነው። በአጭሩ በደራሲነት ብቻ የሚታወቅ ማለት ነው። በሀገራችን በደራሲነት ብቻ የሚታወቁ ብዙ ደራሲዎችም አሉ።
እዚህ ላይ የማይገባኝ ነገር የሙሉ ጊዜ ደራሲ መሆን (መባል) ለሚጻፉት መጽሕፍት ይዘት ምን ያህል ዋጋ አለው የሚለው ነው። እነዚህ የሙሉ ጊዜ ደራሲ የሚባሉ ሰዎች የሚጽፏቸው መጽሐፍት ከልቦለድ ያለፉ አይሆኑም የሚል የግሌ ግምት አለኝ። ድርሰት ማለት ደግሞ የግል ልቦለድ ብቻ አይደለም፤ ኢ-ልቦለድንም ይጨምራል። ስለዚህ፣ አንድ ደራሲ በር ዘግቶ የሙሉ ጊዜ ደራሲ ከሆነ ምን ይጽፍልን ይሆን? የሚለው ያሳስበኛል።
ዋናው ነገር እነዚህ ደራሲያን የሚጽፉት መጽሐፍ ይዘቱ ምን ይሆናል? የሚለው ነው። አንድ ደራሲ የሙሉ ጊዜ ደራሲ ሆኖ ከሚጽፈውና አንድ ሌላ ደራሲ ደግሞ በሌላ የሥራ ዘርፍ ላይ ሆኖ ቢጽፈው የትኛው በብዛት ተወዳጅና መነጋገሪያ ይሆናል የሚለው ነው። ከዚያ በፊት አንድን መጽሐፍ ተወዳጅና መነጋገሪያ የሚያደርገው ምኑ ነው? የሚለውን እንመልከት።
ለሥነጽሑፍ ሰዎች፤ ሥነጽሑፋዊ ውበቱ ይሆናል። ቀልብ አንጠልጣይነቱ፣ በውስጡ ያለው ፍልስፍና፣ የሚጠቀማቸው ቃላት፣ ፈጠራው እና ሰዎችን በምናብ ወደ ሌላ ዓለም መውሰዱና የመሳሰሉት ተወዳጅነት እንዲኖረው ያደርጋሉ። በዚህም ተለይተው የሚታወቁ ደራሲዎች አሉ። ይህ ግን በብዛት ለልቦለድ ወዳጆች ነው።
የኢ-ልቦለድ መጻሕፍትን ካስተዋልን ግን በዋናነት ተወዳጅ የሚያደርጋቸው ይዘታቸው ነው። ፀሐፊው የወጣ የወረደበት፣ ያስተዋላቸው ቀልብ ሳቢ ነገሮች፣ የፀሐፊው የዕውቀትና የማስተዋል ብቃት … የመሳሰሉት መጽሐፉን ተወዳጅና መነጋገሪያ ያደርጉታል።
አንድ ደራሲ መጽሐፍ የሚጽፈው (ልቦለድም ሆነ ኢልቦለድ) ያስተዋለውን፣ የወጣ የወረደበትን፣ ያነበበውንና የተመራመረውን ከራሱ አተያይ ጋር አስማምቶ ነው። ስለዚህ አንድ ሰው የሙሉ ጊዜ ደራሲ ሲሆን እነዚን ነገሮች አያጣም ወይ? እንቅስቃሴው ውስን አይሆንበትም ወይ?
አንድ ደራሲ የሙሉ ጊዜ ፀሐፊ ሆነ ማለት ከቤት አይወጣም ማለት እንዳልሆነ ይገባኛል። በብዙ የግል ጉዳዮች ምክንያት ይንቀሳቀሳል። ዳሩ ግን አንድ የሙሉ ጊዜ ደራሲ በግል ጉዳዩ ሲንቀሳቀስ እና አንድ ሌላ ሰው በሥራው ምክንያት በሰፊው ቢንቀሳቀስ የትኛው የበለጠ አካባቢያቸውንና ሀገራቸውን ያስተውላሉ?
በእነዚህ ምክንያቶች የሙሉ ጊዜ ደራሲ ሲባል አይገባኝም። ደራሲ ሲባልም የግድ የሆነ በሥነ ጽሑፍ የታወቀ ሰው የሚጽፈው ብቻ አይደለም። አንድን መጽሐፍ ተወዳጅ የሚያደርገው ይዘቱና የሥነጽሑፍ ውበቱ ሲሆን፤ ይህም የሚሆነው ይዘቱ የማኅበረሰቡን የልብ ትርታ የሚነግር ሲሆን ነው።
እዚህ ላይ ግን ደራሲ በዕውቀቱ ሥዩምን በተለየ መንገድ ምሳሌ ማቅረብ ሳያስፈልግ አይቀርም፤ ምክንያቱም በዕውቀቱ ሥዩም የሙሉ ጊዜ ደራሲ ሆኖ (በሌላ ዘርፍ አይታወቅም) የሚጽፋቸው ጽሑፎች ግን ከማንም ተንቀሳቃሽ ሰው የተለዩ ናቸው። የማኅበረሰቡን ሕይወት በሚገባ ያውቀዋል። የጽሑፉ መቼት ብዙ ጊዜ በእግር ጉዞ እና የታችኛው መደብ የማኅበረሰብ ክፍል የሚኖርበትን የሚያሳይ ነው። ስለዚህ የሙሉ ጊዜ ደራሲ ከሆኑ እንደ በዕውቀቱ ሥዩም መሆንን ይጠይቃል።
በነገራችን ላይ፣ በሀገራችን ስመ-ጥር እና በድርሰት ዓለም ፈር ቀዳጅ ሆነው ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎችን የሠሩ ሰዎች የሙሉ ጊዜ ደራሲ አልነበሩም። ‹‹ደራሲ›› የሚለውን ክብር ያስገኙላቸውን ሥራዎች የሠሯቸው በሌላ ኃላፊነት ላይ ሆነው ነው። እነዚያን ድንቅ መጻሕፍት ለመጻፍ ያስቻላቸው በእነዚያ ቦታዎች ላይ መሆናቸው ነው። የትምህርት ዘርፋቸውንም ካየን በቋንቋና ሥነ ጽሑፍ የተመረቁ አልነበሩም። የእነርሱ ሥራ ግን ለቋንቋና ሥነ ጽሑፍ መሠረት ሆነ። እንዲያውም አብዛኞቹ በመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ ነበሩ። ጥቂቶቹን እናስታውስ።
‹‹መጽሐፍ ማንበብ አልወድም›› በሚሉ ሰዎች ሳይቀር የሚታወቀው የፍቅር እስከ መቃብር ደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁ የተዋጣላቸው ዲፕሎማት ነበሩ። ለምሳሌ፤ በተባበሩት መንግሥታት፣ በእንግሊዝ፣ ኒውዮርክ እና እሥራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ነበሩ። ምናልባትም ብዙዎች የሚያውቋቸው ግን በደራሲነት ብቻ ሊሆን ይችላል። የሀገሪቱ መሪ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በተመስጦ የሚያዳምጡት ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድን እና ሀዲስ ዓለማየሁን ነበር ይባላል። በእንዲህ አይነት የሥራ ኃላፊነት ላይ የነበሩት ሰው ፍቅር እስከ መቃብርንና ሌሎች መጽሐፎቻቸውን አበረከቱልን።
ኦሮማይ፣ የቀይ ኮከብ ጥሪ፣ ከአድማስ ባሻገር፣ ሀዲስ በሚሉት መጻሕፍቱ የደራሲ ተምሳሌት ሆኖ የሚጠቀሰው በዓሉ ግርማ በደርግ ዘመነ መንግሥት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ተጠሪ ነበር። ወዲህ ደግሞ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እስከመሆን የደረሰ ጋዜጠኛ ነበር።
ከበደ ሚካኤል የትምህርት ሚኒስትር ነበሩ። የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ረጅም ልቦለድ ደራሲ የሆኑት አፈወርቅ ገብረእየሱስ፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ፣ መርስዔ ኀዘን ወልደቂርቆስ፣ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም … የመሳሰሉት በመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ ነበሩ። የአደፍርስ ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ እንደዚሁ በመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ ይሠራ ነበር።
እዚህ ላይ አንድ ከግምት መግባት ያለበት ነገር የዘመኑ ዓውድ ነው። በዚያን ዘመን ። የተማሩ። የሚባሉት በመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ ያሉት ናቸው። ስለዚህ ደራሲ የመሆን ፍላጎቱና ዕድሉ የሚኖራቸውም እነርሱው ናቸው።
በዚህ ዘመን ግን ነገሩ ተቀያይሯል። ብዙ ነገር የማስተዋል ዕድል ያላቸው በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ ያሉት ቢሆኑም፤ ግን አይጽፉም። ደራሲ ማለት በሥነ ጽሑፍ የተመረቀ፣ ሥራውም መጽሐፍ መጻፍ ብቻ የሆነ እስኪመስል ድረስ ለጥቂት ልቦለድና ግጥም ፀሐፊዎች ብቻ ተሰጥቷል። አንድ በሌላ ዘርፍ ላይ ያለ ሰው መጽሐፍ ሲጽፍ ‹‹ደራሲ›› እየተባለ ይቀለድበታል። ዋናው ነገር የጻፈው መጽሐፍ ሥነ ጽሑፋዊ ውበቱና ይዘቱ ምንድነው? የሚለው ነው እንጂ፤ እንጂነርም ሆነ ሐኪም፣ የቤት ሠራተኛም ሆነች የበረራ አስተናጋጅ፣ ዳኛም ሆነች ወታደር ደራሲ መሆንና መባል ትችላለች/ይችላል።
ስለዚህ፣ የሙሉ ጊዜ ደራሲ ማለት ምን ማለት ነው? አንድ ሰው እንዴት የሙሉ ጊዜ ደራሲ መሆን ይችላል? የሙሉ ጊዜ ፀሐፊ ከሆነ ምንድነው የሚጽፍልን? ከየት ያመጣውን? ለመጻፍ ተብሎ የሚደረግ እንቅስቃሴ እግረ መንገድ እንደሚገኘው ሀሳብ ማራኪ ይሆናል ወይ? ‹‹እስኪ ለድርሰት ሀሳብ የሚሆነኝ ነገር ለማግኘት ወጣ ልበል›› ተብሎ ቢወጣ ተፈጥሯዊ የሆነውን (በእግረ መንገድ የሚገኘውን ማለት ነው) ያህል አስገራሚ ይሆናል ወይ? ለመጻፍ ተብሎ የሚኬደው ምናልባትም ለዘገባ ሥራ ነው። የሚጻፈውም ሥነጽሑፋዊ በሆነ መንገድ ሳይሆን በቀጥታ ሁነቱን ለሕዝብ ለመናገር ነው።
አንድ ሐኪም፣ ኢንጂነር፣ ዳኛ፣ ወታደር፣ ባለሥልጣን፣ ወይም በየትኛውም የግል ዘርፍ ላይ የተሠማራ ሰው ግን በእንቅስቃሴዎቹ ውስጥ ሁሉ ያጋጠሙትንና ያስተዋለውን የራሱን ሥነ ጽሑፋዊ የፈጠራ ውበት ጨምሮ ቢጽፍ የብዙዎችን የልብ ትርታ የሚዳስስ ይሆናል። ችግሩ ግን በሀገራችን በእነዚህ ሙያዎች ላይ የተሰማሩ ሰዎች የመጻፍ ድፍረት የላቸውም። ምክንያቱም ደራሲ ሲባል ለእነዚያ በልቦለድና በግጥም ለታወቁት ሰዎች ብቻ የተሰጠ መስሎ ነው የሚታያቸው።
ድርሰት ማለት መጻፍ ማለት ነውና ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚሰጥ መሆን የለበትም።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2016 ዓ.ም