
አዲስ አበባ፤ የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለፉት ሁለት ዓመታት 1 ሚሊየን 567መቶ የአሜሪካ ዶላር ማስገኘቱን የኢንቨሰትመንት ኮሚሽን አስተወቀ።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ሀይሉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳሉት፤ የኢንዱስትሪ ፓርኩ በተመረቀ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ስመ ጥር ባለሀብቶችን በማስገባት 1 ሚሊየን 56ሺ 7መቶ የአሜሪካ ዶላር ገቢ አስገኝቷል።
ለኢንቨሰትመንቱ ማነቆ ሆነው የቆዩትን የመሬትና ሌሎች የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግሮችን በመፍታት በኩል መንግሥት ትልቅ ሥራ እየሰራ መሆኑን አቶ መኮንን ጠቅሰው፣ በተለያዩ አካባቢዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ በርካታ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ገብተው እየሰሩባቸው እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
በኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ ፓርክ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች እየገቡ መሆናቸውን አመልክተው፤ የደቡብ ኮሪያው ፑን ኩክ የተባለ ኩባንያ ‹‹ማይክል ኮስ›› በሚባል ዓለም አቀፍ ተቀባይነትና ታዋቂነት ባለው የምርት ምልክት (ብራንድ) ዘመናዊ የሴቶች ቦርሳ እያመረተ መሆኑን በአብነት ጠቅሰዋል፡፡
ካለቪኮ የተባለ የጣሊያን ኩባንያም እንዲሁ የስፖርት አልባሳትን አምርቶ ለውጭ ገበያ እያቀረበ መሆኑንም አመልክተው፣ ሳይቴክስ የተሰኘው የቻይና ኩባንያም እንዲሁ ጥጥ እየፈተለ ክር በማምረት በገበያው ላይ እየተሳተፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኩባንያዎቹ ምርቶቻቸውን በዋናነት ወደ አሜሪካ፣ አውሮፓና ኤዥያ ገበያዎች እየላኩ መሆናቸውንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
እንደ አቶ መኮንን ማብራሪያ፤ትራፓስ የተሰኘ የአሜሪካ ኩባንያ ወደ ፓርኩ በመግባት ለስራው የሚያስፈልጉ የማሽን ተከላዎችንና የሠራተኞች ስልጠና እየሰጠ ሲሆን፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥም ወደ ማምረት ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።በቅርቡም የደቡብ ኮሪያ ፊናንግ የሚባል ኩባንያ ወደ ፓርኩ ለመግባት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል ፡፡
የኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ ፓርክ አገልግሎቱን ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመጀመር የመብራት፣ የቴሌኮም፣ የጉምሩክ፣ የባንክ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡
በቀጣይም የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች ቢሮውን እንደሚከፍትና ባለሀብቶቹ ከስራቸው ሳይርቁ ላላስፈላጊ ወጪ ሳይዳረጉ አገልግሎቱን በአቅራቢያቸው አንዲያገኙ ይደረጋል፡፡የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም ስራውን ለማቃናት የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ በመመደብ እያስተባበረ ነው።
የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለ20 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። ባለፈው ሳምንት የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተመረቀ ሲሆን፣የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክም በቅርቡ እንደሚመረቅ የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል።
እፀገነት አክሊሉ