የኮብል ስቶን መንገድ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮች፣ ወዘተ ግንባታዎች ለከተሞች ነዋሪዎች መሰረታዊ ነገሮች ከመሆናቸው በተጨማሪ በከተሞቹ ገጽታ ላይ ህይወት ይዘራሉ፡፡ የመሰረተ ልማት በተገነባላቸው ከተሞች እየተስተዋለ ያለውም ይሄው ነው፡፡
በዚህ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራ ከተሞች የራሳቸውን ሚና ቢኖራቸውም፣ በአንዳንድ ከተሞች ላይ የዓለም ባንክ ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ መንግሥትና በዓለም ባንክ መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት በከተሞች መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም በዓለም ባንክ መስፈርት በተመረጡ ከተሞች ላይ አፈፃፀሙ ያለበትን ደረጃ በጥንካሬም በድክመትም በጋራ መገምገምና ለቀጣይ ሥራ ማነሳሳትን ዓላማ ያደረገ መድረክ በቅርቡ በአዳማ ከተማ በተካሄደበት ወቅት እንደተጠቆመው፤ የከተሞች መሠረተ ልማት ማስፋፊያ የተጀመረው በ2001 ዓ∙ም በ19 ከተሞች ሲሆን፣ በ2007 ዓ∙ም በ26 ከተሞች በአጠቃላይ 44 ከተሞች እስከያዝነው ዓመት ድረስ የልማቱ ተጠቃሚ ሆነዋል።
በመንግሥትና በዓለም ባንክ ትብብር እየተሠሩ ያሉ የከተሞች የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ሥራዎች ዓላማቸው ከተሞችን ማስዋብ እና የሥራ አጥ ቁጥርን መቀነስ ነው። የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ሥራዎች ሲሠሩ ግን የህዝብን ፍላጎት ተንተርሶ መሥራት፣ የህዝብን ቅሬታና አቤቱታ መስማትና እልባት መስጠት በልማት ስም ገንዘቦች ለምዝበራና ብክነት እንዳይጋለጡ ጥረት ማድረግ የህዝብን ገንዘብ ለማባከን የሚፈልጉትንም ማጋለጥ ይገባል። የፌዴራልም ሆነ የየክልሎቹ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በዚህ ረገድ ጠንክረው ቢሠሩ ተሰሚነታቸውን ይበልጥ ለማጎልበት ይረዳቸዋል።
በፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የጥናትና ምርምር ቡድን መሪ ዶክተር አሰፋ መኮንን እንደተናገሩት፤ በኮብል ስቶን፣ በከተሞች ተፋሰስ መሠረተ ልማት ኅብረተሰቡ አውቆና ተሳትፎ ግልጽ ሆኖ አምኖበት ሊሰራ ይገባል፡፡ በጥራት፣ በግዢና በካሳ ክፍያ ያሉት ችግሮች ቅሬታ ቀርቦ ካልተፈቱ ወደ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ቅሬታ ሰሚ ጽ/ቤት ይቀርባል። በየወረዳው የእያንዳንዱ ቅሬታ ሰሚ ጽ/ ቤት መረጃ ተሰብስቦ ለክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ይቀርባል። የክልሉ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ደግሞ አጠናክሮ ወደ ፌዴራል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ይልካል። የፌዴራሉ ደግሞ የዘጠኙን ክልሎች እና የድሬዳዋና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሮችን ሪፖርቶች ጨምሮ አጠናክሮ በየስድስት ወሩ ለዓለም ባንክ ሪፖርት ያደርጋል።
የዓለም ባንክ ለፌዴራል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኃላፊነት ሲሰጠው ሪፖርት ማድረግ እና ተከታትሎ የተለያየ መፍትሔ እንዲሰጥ ነው ያሉት ዶክተር አሰፋ፣ ኮሚሽኑ ከዚህ አኳያ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ይገልፃሉ።
ዶክተር አሰፋ፤ ሪፖርቱ ብዙ ቅሬታዎች እንዳሉ መማልከቱን፣ በካሳ ክፍያዎች፣ ጥራት እና ግዢ ላይ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ከሪፖርቱ መረዳት መቻሉን ጠቅሰው፣ ሚያዝያ ላይ የኮሚሽኑ ሰራተኞች ለቁጥጥር ወደ መስክ በወጡበት በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን መመልከት መቻሉን ይገልጻሉ።
እንደ ዶክተር አሰፋ ገለጻ፤ ከከተሞች 37 በመቶው ከገቢ ምንጫቸው ለከተሞች መሠረተ ልማት እንዲያዋጡ የዓለም ባንክ ያስገድዳል፡፡ ገቢ አሰባሰቡ እንዲሰፋም ሥርዓት እየተዘረጋ ነው፡፡
በፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በኩል በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ ከዚህ ክልሎችን በማገዝ ድጋፍና ክትትል ያደርጋል። ከዚህ አኳያም የደቡብ ክልል ይጠቀሳል፡፡
በደቡብ ለክልሎች ልማት ከተመደበው የፕሮጀክቱ ገንዘብ ውስጥ በዲላ ከተማ ብቻ 4 ሚሊዮን ብር የመዘበሩ አሥር ሰዎች በጥርጣሬ ተይዘው እንደ ነበር፣ ስድስት ሰዎች ክሳቸውን በዋስ እየተከታተሉ መሆናቸውን፣ አራት በእስር ላይ እንደሚገኙ ዶክተር አሰፋ መኮንን ያብራራሉ።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ አታክልቲ ግደይ ለከተሞች መሠረተ ልማት የሚወጣ ገንዘብ ምንጮቹ መንግሥት፣ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ድርጅቶችና የፀረ ሙስና ኮንቬንሽን ፈራሚዎች እንዲሁም የሕዝብ ንቅናቄ ናቸው ይላሉ፡፡ ሥነ ምግባርን የማስተማር ሥራ በልመና በጀት እየሠራን ነው የሚሉት አቶ አታክልቲ፣ መፅዋች ያቆመ ጊዜ ትግሉ እንዳይቆም ከወዲሁ እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት ወይም ተቋም ለዚህ ሥራ በጀት መድቦ ቢንቀሳቀስ የተሻለ መሆኑንም ያስገነዝባሉ።
በዓለም ባንክ ከፍተኛ የሕዝብ ዘርፍ ስፔሻሊስት አቶ ብርሃኑ ለገሰ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት እጦት በከተሞች ላይ እንደሚስተዋል ጠቅሰው፣ ጎብኚን ለመሳብ ለማደግ መሠረተ ልማት ወሳኝ ነው ይላሉ:: መንገድ፣ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል የመሳሰሉትን የኅብረተሰቡን ፍላጎት ለመለየት በማወያየት የሚሠራ መሆኑን ይገልፃሉ። ከተሞች የገቢ ምንጮቻቸውን በአግባቡ አይጠቀሙም የሚሉት አቶ ብርሃኑ፣ በማዘጋጃ ቤታዊ ስርዓት የገቢ ምንጫቸውን ለማሳደግም አይጥሩም ሲሉ ይናገራሉ።
የፕሮጀክቶች ዲዛይን፣ የሥራ ዝርዝር እንዲሁም የፕሮጀክት መሥሪያ ቦታ አስቀድሞ አለማዘጋጀት እና ፕሮጀክቶችን ከከተማው ማስተር ፕላን ጋር አለማድረግ፣ የካሳ ግምት በልምድ ላይ ተመስርቶ መስራት፣ ለሙስና መጋለጥ እንደሚስተዋል ጠቁመው፣ ችግሩን ለመፍታት ጥረት መደረግ እንዳለበት አስረድተዋል።
የፌዴራል ስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ እንደሚሉት፤ የከተሞች የልማት ፕሮግራም በታለመለት መልኩ ተግባራዊ ሆኖ ህዝቡን ተጠቃሚ እንዲያደርግ ለየከተሞቹ የተመደበ ገንዘብ ከሙስናና ብክነት በራቀ መልኩ ለታሰበለት ዓላማ እንዲውል ማድረግ ይገባል።
በሀገሪቱ ለሚገኙ 117 ከተሞች ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ ለሚሠሩ መሠረተ ልማት ሥራዎች በ835 ሚሊዮን ዶላር የዐቅም ግንባታ ከተሞቹን የማዘመንና ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ሥራዎች እየተሠራ ይገኛል የሚሉት ምክትል ኮሚሽነር ወዶ አጦ፣ የከተሞች ከንቲባዎችና የማዘጋጃ ቤቶች ሥራ አስኪያጆችና የሥራ መሪዎች የተሰበሰበውን የልማት ገንዘብና ዕቅድ የመምራት፣ የመከታተልና የመቆጣጠር የበለጠ ኃላፊነት እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ።
በዓለም ባንክ የደቡብ ክልል የከተሞች ተቋማዊ መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዳምጤ ዳታ በክልሉ 23 ከተሞች በዓለም ባንክ ድጋፍ እና በመንግሥት ትብብር የመሠረተ ልማት ሥራዎች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ይገልፃሉ።
አቶ ዳምጤ እንደሚሉት፤ በፕሮጀክትና ፕሮግራም መረጣ፣ በግንባታ፣ በግዢና የኮንትራት አስተዳደር ሥራዎች አንዳንድ አካባቢዎች ተጠቃሚ ካለመሆናቸው ጋር በተያያዘ ቅሬታዎች ሊነሱ ይችላሉ። ቅሬታዎች በአግባቡ የሚፈቱበት ሥርዓት ከሌለ በህዝቡ ዘንድ አመኔታ እየታጣ ይመጣል፤ ይህ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይሄድ ብልሹ አሠራሮችን ማስተካከል ያስፈልጋል።
የደብረታቦር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አበበ እምቢአለ መድረኩ የከተሞችን መሠረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዴት መፈታት እንዳለባቸው ከስነምግባርና ፀረ ሙስናና ኮሚሽን ጋር በፌዴራል ደረጃ የተካሄደ እና በኢትዮጵያ ያሉ የዓለም ባንክ ተጠቃሚ ከተሞች የተሳተፉበት ነው ይላሉ።
ምክትል ከንቲባው ከተሞች ብዙ የመሠረተ ልማት ችግር ያለባቸውና በአስተዳደር ችግር እሮሮ የሚነሳባቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የዓለም ባንክ በየዓመቱ ሰፊ ገንዘብ ለከተሞች እንደሚለቅ፣ ይህ በጀት ደግሞ በአግባቡ የኅብረተሰቡን የመሠረተ ልማት ችግር ለመፍታት ወሳኝ ስለሆኑ ያብራራሉ፡ ፡ በዚህ ስራ ውስጥ ከፍተኛ በጀት ከመንቀሳቀሱ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለውን የበጀት ብክነት ለመቀነስ በህዝብ ስም የመጡ በጀቶችን በአግባቡ መጠቀም ይገባል ይላሉ።
‹‹የአደጉ ሀገሮች ለመጪው ትውልድ አስበው ሀብት ያስቀምጣሉ፤ እኛ ግን የመጪውን ትውልድ ሀብት እየተጠቀምን ነው›› የሚሉት ምክትል ከንቲባው፣ ‹‹ያለነው በብድር ስለሆነ ገንዘቡን በአግባቡና ለተባለለት ዓላማ መዋል መቻል ይገባናል።›› ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡
ደብረታቦር ከተማ የዓለም ባንክ የከተሞች መሠረተ ልማት በጀት ተጠቃሚ ናት የሚሉት ምክትል ከንቲባው በጀቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለውም ያመለክታሉ፡፡ የኅብረተሰቡን የመሠረተ ልማት እና የወጣቱን የሥር አጥነት ችግር እየፈታ ያለና ለዜጎች ምቹ መኖሪያ መፍጠርን ትኩረት ያደረገ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ «የሰለጠነውን የዓለም አሠራር ሥርዓት እንድናዳብር እንድንጠቀም ያግዘናል›› ሲሉም ይገልጻሉ፡፡
በጀቱ ስራ ላይ በሚውልበት ወቅት ቅሬታ ካለም በይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ እንዲሁም በስነ ምግባርና ፀረ ሙስና መኮንን በኩል ክትትል እንደሚደረግ ጠቅሰው፣ ቅሬታዎችንም በአግባቡ እየታዩ እንደሚፈቱም ይናገራሉ።
የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ አቶ አደም ከማል የሻሸመኔ ከተማ በዓለም ባንክ የከተሞች መሰረተ ልማት በጀት በሚከናወኑ ስራዎች ጥሩ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
እንደ ከንቲባው ማብራሪያ፤ በከተማዋ የፋይናንስ አስተዳደር ባለሙያዎች ሕግና ሥርዓትን የተከተሉ ግዢዎች እንዲያከናወኑ ማኅበረሰቡ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ መፍጠር የዚህ ፕሮጀክት ግዴታ ነው። በዚህ በጀት አጠቃቀምም ተጠያቂነት አለብን፡፡ ፕሮጀክቶች በመምረጥ እና ጨረታዎች በማውጣት በኩል ማኅበረሰቡ እንዲመክር ይደረጋል፡፡ ለፕሮጀክቶች የሚወጣው ገንዘብ በባለሙያዎች ይታያል፤ይገመገማል፡፡
የነገሌ ቦረና ከንቲባ አቶ አልዬ ዋታ መድረኩ በኅብረተሰቡ ቅሬታ አፈታት ሥርዓት የመዘርጋት፣ ቅሬታዎች ተቀብሎ በየደረጃው የማወያየት ብልሹ አሠራሮችን የማስወገድ አስፈላጊነት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ያመለከተ ነው፡፡ የልማት ሥራዎች ሲሠሩ የህዝቡን ይሁንታ ባረጋገጠ መልኩ መተግበር ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝቧል፡፡ ችግሮች እንዴት መፍታት አለባቸው በሚለው ላይ ግንዛቤ ማግኘት መቻሉን ይጠቅሳሉ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ