አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ የሚታዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመታገል የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ሥራና ርብርብ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዶክተር አዲሱ ገብረአግዚአብሔር አስታወቁ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የምስራቅ አፍሪካ ቢሮ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በመሆን 70ኛ ዓመት የሰብዓዊ መብት ቀንን በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ትናንት ባከበረበት ወቅት ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረአግዚአብሔር እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የሚታዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና የመንጋ ፍትህን ለመከላከል የሁሉም ባለደርሻ አካላት ተሳትፎ ያስፈልጋል።
በኢትዮጵያ በርካታ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች አንዳሉ ጠቅሰው፣‹‹ሰብዓዊ መብትን የማክበርና የማስከበር ተልዕኮው ቀላል ባይሆንም በተቻለ መጠን ግን የእለት ተእለት አጀንዳ በማድረግ መስራት ውጤቱን ሩቅ አያደርገውም።››ብለዋል፡፡
ባለፉት ጊዜያት በኢትዮጵያ ውስጥ የመብት ጥሰቶች መከሰታቸውን በኮሚሽኑም ምርመራ መረጋገጡን ተናግረው፤ ‹‹ወደፊት ግን ይህ ሁኔታ እንዳይቀጥል ማድረግ የሚቻለው የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሲጎላ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በዚህ በ70ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ጎልቶ መውጣት ያለበት ከዚህ በፊቱ ምን ተምረናል? ወደፊትስ ለልጆቻችን ምንድነው የምናቆይላቸው ?የሚለውን ሊሆን ይገባል›› ሲሉ ገልጸዋል።
የዜጎች መብት የተከበረባት ዜጎች እንደ ሰው የተቆጠሩባት አገር የመፍጠር ተልዕኮ ቀላል እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ ብዙ ውጣ ውረድ የታለፈበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡እነዚህን የመፈተሽ፣ ተፈጻሚነታቸውን የማረጋገጥ፣ በፍትህ አካላት በኩል ያለውን አካሄድ ቆም ብሎ ማየት የሁሉም ተቋማት ድርሻ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ ውስጥ ስትታይ በታላቅ ቁርጠኝነት ሰብዓዊ መብትን ለማረጋገጥ የተሰለፈች መሆኗን አስታውቀው፣ ፤ይህንንም ቁርጠኝነቷን በሙሉ ልብ ወደ ሥራ ለማስገባት የሁሉም ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ታገሰ ገለጻ፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች እንዲከበሩ ለማድረግና ተጥሰው ሲገኙም ተጠያቂነት ያለው አሰራር ለመዘርጋት ከምን ጊዜውም በላይ ዝግጁነቱ አለ፡፡
በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የኢትዮጵያ ተወካይ የሆኑት ሚስ ዋኔ ዋዴ በበኩላቸው፤ ሰዎች በሚኖሩበት አገር በቀለማቸው፣ በሀይማኖታቸው፣ በጾታቸው አልያም በብሔራቸው አድሎ ሳይደረግባቸው የመኖር መብት እንዳላቸው አመልክተዋል፤ ‹‹በመሆኑም ይህንን ጉዳይ ላለፉት 70 ዓመታት ስንታገል ነበር፤ አሁንም ይቀጥላል›› ብለዋል።
ብዙ አገሮችም የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ኮንቬንሽኖችን ቢፈርሙም ተግባራዊነቱ ላይ ልዩነት እንዳላቸው ጠቅሰው፣ ይህ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ በሁሉም አገር እንዲሁም በሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ተፈጻሚ እንዲሆን መስራትም እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
‹‹እርስ በአርስ መጎዳዳት አቁመን ዓለማችንን ከፍርሀት ነጻ የሆነች ማድረግ አለብን፤ ሀይለኞች እንዲገደቡ ሀይል የሌላቸው ደግሞ ተስፋ እንዲያጭሩ ባለፉት 70 ዓመታት ተሰርቷል፡፡ ጠቃሚ ለውጦችም መጥተዋል፡፡ በዘጠና አገራት ህገ መንግሥት ውስጥም ሀሳቡን ማስረጽ ተችሏል›› በማለት አስረድተዋል።
ኢትዮጵያም የህገ መንግሥቷ አንድ ሦስተኛ የተያዘው በሰብዓዊ መብት ደንጋጌዎች መሆኑ ይታወቃል።
እፀገነት አክሊሉ