በክልሉ እያደገ የመጣውን የአፈር አሲዳማነት ለመከላከል የተለያዩ አማራጮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው

መንዲ:- በኦሮሚያ ክልል ከዝናብ መብዛት ጋር ተያይዞ እየጨመረ የመጣውን የአፈር አሲዳማነት ለማስቀረት የተለያዩ አማራጮችን በጥናት በመለየት ተግባራዊ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡ በጥናት ከተለዩት መካከል አቮካዶ፣ ማንጎ፣ እና ቡና የመሳሰሉትን በመትከል የተሠራው ሥራ ተጠቃሽ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ የተመራው ጉብኝት በወለጋ የተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች የተለያዩ የግብርና ሥራዎች ጉብኝት ባካሄደበት ወቅት የክልሉ የግብርና ምርምር ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የምርምር ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር አሰፋ ታኣ እንደገለጹት፤ በጉብኝቱ ወቅት ከታዩት መካከል በምዕራብ ወለጋ መነሲቡ ወረዳ በአፈር አሲዳማነት እና በምስጥ ከተጎዱ አካባቢዎች አንዱ ነው።

ዶክተር አሰፋ የአፈር አሲዳማነት በኦሮሚያ ክልል እያደገ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዝናብ መብዛት ለዚህ ምክንያት መሆኑን አመክተዋል።

አሲዳማ አፈሩን በኖራ ለማከም አንድ ዓመት ኖራ ከተጨመረበት ለአምስት ዓመት የአፈር ማዳበሪያ በመጨመር መሬቱ ላይ ምርት ማግኘት የሚቻል መሆኑንም ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው፤ የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከል በስፋት አቮካዶ፣ ማንጎና ቡና መትከል እንደሚገባ አመላክተዋል።

የአርሶ አደሩን ገቢ ለማሳደግ አቮካዶ በአካባቢው ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እየለማ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

በተለይም ከክልሉ መንግሥት በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ሀገር ውስጥ የሌሉ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ከውጭ በማስገባት እየተሠራ ነው ብለዋል።

በክልሉ ለአቮካዶ በሚሆኑ ቦታዎች በትኩረት እየተሠራ ነው ሲሉም 10 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ የአቮካዶ ችግኝ በማዘጋጀት 30 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በዚህ ዓመት የሚተከል መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህ ላይ የተሠማሩ ባለሀብቶች በመንግሥት በኩል ማበረታቻ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።

አቮካዶ በሦስት ዓመት የሚደርስ በመሆኑ ሳይንሱን ተከትሎ ከተሠራ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚቻል ነው። በአቮካዶ የሚሸፈነውና ከውጭ ምንዛሪ የሚገኘው ገቢ በየዓመቱ እየጨመረ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአቮካዶ ላይ በትኩረት ከተሠራም በአሲዳማነት እና በምስጥ የተጎዳ መሬት የሚታከም መሆኑንም አመላክተዋል። ቡና፣ የሻይ ቅመም አሲዳማነትን መቋቋም የሚችሉ ተክሎች ናቸው።

እንዲሁም ኖራን በስፋት ማዳረስ አሲዳማ አፈርን ለማከም አንዱ አቅጣጫ ነው ብለዋል።

የምዕራብ ወለጋ ዞን መነሲቡ በወረዳ አስተዳዳሪ ገመቺስ ሲሪቃ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በወረዳው ያለው መሬት በአሲድና በምስጥ የተጎዳ ነው።

በመሆኑም ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ በመስጠትና ከአፈር ጥበቃው በመነሳት ከበቆሎ ወደ አቮካዶ ምርት በመቀየር የበለጠ ውጤት እየተገኘበት ነው።

ከአፈር ጥበቃው በመነሳትም በወረዳው ለመጀመሪያ ጊዜ 60 ኩንታል ያህል አቮካዶ ለውጭ ገበያ መቅረቡን አስታውሰዋል።

ወረዳው 52 ያህል የገጠር ቀበሌዎች የሚገኙበት ሰፊ ወረዳ ሲሆን፤ በ25 ቀበሌዎች ያህል የአቮካዶ ክላስተር ለማስፋፋት እየተሠራ ነው።

በቀጣይም በእነዚህ አካባቢዎች የአቮካዶ ምርት ለማስፋፋት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን  ሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You