“በዓለም አቀፍ ተቋማት ፍትሃዊ ውክልና እንዲሰፍን በሚደረጉ ጥረቶች የብሪክስ ማዕቀፍ ጉልህ ሚና ይጠበቅበታል” አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ

አዲስ አበባ፡- በዓለምአቀፍ ተቋማት ፍትሃዊ ውክልና እንዲሰፍን በሚደረጉ ጥረቶች የብሪክስ ማዕቀፍ ጉልህ ሚና ይጠበቅበታል ሲሉ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ። በኒውዮርክ እየተካሄደ ከሚገኘው 79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን የብሪክስ አባል ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ተካሂዷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር በዓለም አቀፍ ተቋማት አስተዳደር እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ፍትሃዊ ውክልና እና ተሰሚነት እንዲሰፍን በሚደረገው የማሻሻያ ጥረት የብሪክስ ማዕቀፍ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል የሚል ተስፋ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

አምባሳደር ታዬ የባለብዙ ወገን ዓለም አቀፍ ተቋማቱ አሳታፊ እና ጠንካራ እንዲሆኑ የተጀመሩ የማሻሻያ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አንስተዋል።

ሚኒስትሩ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ማሻሻያን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር ማሻሻያው ቅድሚያ ለአፍሪካ ውክልና መስጠት እንደሚገባው እና ታማኝ እና ፍትሃዊ ሆኖ መቀጠል አለበት ብለዋል።

አምባሳደር ታዬ በጸጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ ላይ ኢትዮጵያ የምታራምደው አቋም የአፍሪካ አቋም ነው፤ “ለአፍሪካ ሕጋዊ እና ታሪካዊ ጥያቄ እና ኢ-ፍትሃዊ እና ግማሽ ምላሽ ሊሰጠው አይገባም” ብለዋል።

ሚኒስትሩ ውክልናው መልከዓ ምድርን፣ የብሪክስን የጋራ ዕሴቶች እና በብሪክስ ማዕቀፍ አባል ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት እና የተመድን ቻርተር ባማከለ መልኩ መከናወን እንዳለበትም ጠቁመዋል።

እነዚህ መርሆዎች ብሪክስ በዓለም አቀፍ ተቋማት ማሻሻያ እና ፍትሃዊ ውክልና እንዲኖር የሚጫወተውን ሚና የበለጠ ያጠናክሩለታል ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You