ትምህርትን ማደናቀፍ የሕዝብ ጠላትነት መገለጫ ነው!

ማንኛውም ለሀገርና ሕዝብ አስባለሁ፤ እሠራለሁ፤ አልያም እታገላለሁ የሚላ ኃይል፤ ከመናገር የተሻገረ በተግባር የሚገለጽና ሕዝባዊ ረብ ያለው ሥራን የማከናወን ልምምድ ሊኖረው ይገባል። ይሄ ባልሆነበትና ከሚነገር ሀቲት በተቃርኖ የሚገለጽ ድርጊት ባለቤት ሆኖ ግን ስለ ሀገር ቆሜያለሁ፣ ስለ ሕዝብም እታገላለሁ ማለቱ ትርጉም አይኖረውም።

በኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ የሚታየውም ይሄው ሀቅ ነው። ለምሳሌ፣ አሁን ያለንበት ወርሃ መስከረም በመላው ሀገሪቱ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ተቀብለው ተገቢውን እውቀት የሚያስቀስሙበት ወቅት ነው። በዚህ ረገድ በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይም በአማራ ክልል ያለው እውነት ከዚህ የተቃረነ ነው።

ለአብነት፣ በአማራ ክልል ባለው የጽንፈኞች እንቅስቃሴ ምክንያት መምህራን ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ መንገድ ላይ እየተጠበቁ የሚገደሉበት፤ ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ገበታቸው ሄደው እውቀት እንዳይቀስሙ በዛቻና ማስፈራሪያ የሚከለከሉበት፤ ትምህርት ቤቶችም ትውልድ የመቅረጫ አውድነታቸውን እንዳይላበሱ የሆኑበት ነው።

በዚህ ድርጊትም ትውልድን ለማነጽ ወደ ትምህርት ቤት የሚያቀኑ መምህራን በመንገድ ላይ ተገድለዋል። ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ገበታቸው ገብተው የሚማሩበትን ዕድል ተነፍገዋል። ትምህርት ቤቶችም ትውልድን ተቀብለው ሊያንጹ ሲያደርጉ የነበረው ሽርጉድም ለፍሬ እንዳይበቁ ሆነዋል።

ይሄ የሆነው ደግሞ ለሀገር ዋልታ ነን፤ ለሕዝባችንም የምንሞት የሕዝብ ጋሻ ነን የሚል የማታለያ ሃሳብን በሚያራምዱ ጽንፈኛ ኃይሎች አደናቃፊነት ነው። በዚህ የማደናቀፍ ሥራቸውም ነው ዛሬ ላይ በአማራ ክልል ወደ ትምህርት ገበታ ደርሶ ዕውቀት ሊቀስም ከሚገባቸው ሰባት ሚሊዮን ያህል ሕጻናትና ታዳጊዎች መካከል እስካሁን ከአራት ሚሊዮን በላዩ ወደ ትምህርት ገበታቸው መድረስ አልቻሉም።

በዚህ መልኩ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ጽንፈኛ ኃይሎች፣ ከዚህ ድርጊታቸው ሊታቀቡ፤ ስለ ነገው የሀገር ተረካቢ የክልሉ ታዳጊ ወጣቶችና ሕጻናት ተስፋ ግድ ሊላቸው፤ እና እነዚህን ታዳጊ ወጣቶችና ሕጻናትን የጥፋት አጀንዳቸው ማስፈጸሚያ ካደረጉበት አካሄድ ሊታቀቡ፤ በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ እንቅፋት ከመሆን ሊቆጠቡ ይገባል።

ይሄ ተግባር ዛሬ ላይ ለራስ ጥቅም ማስፈጸሚያነት እየተካሄደ ያለ ቢሆንም፤ በነገው የክልሉ ሕዝብ ሁለንተናዊ እድገትና ተጠቃሚነት ላይ፤ በዋናነትም ነገን በብዙ ተስፋና ሕልም ለሚጠብቁ ታዳጊ ወጣቶችና ሕጻናት ሕይወት ላይ መቆመር ነው። ዛሬን ያልተማረ ትውልድ ነገ ለሀገርም ለሕዝብም የሚተርፍ እውቀትና አቅም አይኖረውም። እውቀትና አቅም የሌለው ትውልድ በተፈጠረ ቁጥር ደግሞ በሀገርም ሆነ በሕዝብ ላይ አደጋን ይዞ ነው የሚመጣው።

ምክንያቱም፣ ያልተማረ እና ያላወቀ ትውልድ ሕልም የለውም። ሕልም የሌለው ትውልድ ደግሞ ለሀገርም ለሕዝብም የሚሆን ሃሳብም ተግባርም የለውም። ሀገር እንደ ሀገር፣ ሕዝብም እንደ ሕዝብ ደግሞ በትውልድ ሕልምና ሃሳብ ካልተመራ፤ በተግባር የሚገለጥ በትውልድ እውቀትና ትልም ካልታገዘ ከዛሬ ፈቀቅ የሚል ነገር አይኖረውም። ይልቁንም ነገን የማያልም፣ ከዛሬ የሚሻገር ሕልምና ግብ የሌለው ትውልድ በተፈጠረ ቁጥር ጉዞው የቁልቁለት፤ መንገዱም የኋሊት ነው የሚሆነው።

በተለይ ደግሞ ዛሬ ላይ በታጠቁ ጽንፈኞች ወደ ትምህርት ገበታው እንዳይሄድ የተፈረደበት የአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ያለ ታዳጊ ወጣትና ሕጻን፤ ነገ ላይ በሀገር ግንባታ ሂደትም ሆነ በሕዝቦች ሁሉን አቀፍ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እውን መሆን ሂደት ውስጥ እዚህ ግባ የሚባል ሚና እንዳይኖረው የሚያደርግ ነው።

ሊታወቅ የሚገባው ግን፣ ሀገር የምትገነባው፤ ሕዝብም ወደ ተሟላ ከፍታው ሊደርስ የሚችለው ዜጎች በእውቀትም በሙላትም የድርሻቸውን መወጣት ሲችሉ ነው። አሁን እየተደረገ ባለው የታጠቁ ጽንፈኛ ኃይሎች አካሄድ ግን ይሄ እሳቤ ፈጽሞ የተዘነጋ በመሆኑ፤ ከዚህ ነገ ላይ ክፉ ጥላን አጥልቶ ከሚያልፍ ተግባራቸው ሊቆጠቡ ይገባል።

ከዚህ በተጓዳኝ ዛሬ ላይ የሚፈጸሙ ማናቸውም ተግባራት፣ በነገው የትውልዶች እድል ፈንታ ላይ የሚወስኑ እንደመሆናቸው፤ ከጽንፈኛ ታጣቂ ኃይሎች ባሻገር ያሉ የትምህርት ባለድርሻዎች ከእነሱ የሚጠበቀውን ተገንዝበው ከወዲሁ ኃላፊነታቸውን መወጣት፤ የጸጥታ ኃይሉ ለክልሉም ሆነ የሰላም ችግር ባለባቸው አካባቢዎች እያከናወነ ያለውን ተግባር በሙላት መደገፍና ለዘላቂ ሰላሙ አቅም መሆን ይጠበቅባቸዋል። ይሄ ሲሆን ነው የዛሬ ተግባራችን በትውልዶች ነገ ላይ የተሻለ ነገርን የሚያኖረው!

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You