ያልጠለቀች ጀንበር …..

ዕትብቷ የተቀበረው ከአባ ጅፋር አገር ከጅማ ምድር ነው ። ተወልዳ ባደገችበት ከተማ ተምራ፣ ትዳር ይዛ ወግ ማዕረግ ማየት አልታደለችም። ድንገት ከቤተሰብ ጋር የተነሳ ግጭት ሰላሟን ነሳት። ይህ እውነት ለቀጣይ ሕይወቷ ዕንቅፋት መስሎ ቢታያት ቆም ብላ አሰበች።

የሀሳቧ ዳር በዝምታ አልተቋጨም። ከ‹‹ነገሩ ጦም እደሩ››ን መረጠች። ውስጧ ርቆ መሄድን ቢያልም ሩቁን መንገድ አሳያት። ውላ ማደር አልፈለገችም። ጓዟን ሸክፋ ተነሳች። ዘመዶቿን ትታ ጅማን ተሰናብታ አዲስ አበባ ገባች።

ዘቢደር ኩራባቸው የአዲስ አበባ ሕይወት በስራ ተቀበላት። ጉልበቷን ሳትሰስት፣ አቅሟን ሳትደብቅ ከሚተጉት ጋር ዋለች። የላቧን ዋጋ ኣላጣችም። በሰራችው ልክ እያገኘች ራሷን አቋቋመች። ዘቢደር መልካም ባለሙያ ነች። የድግስ ዝግጅት ባለ ጊዜ እጇን የሚሹ ፈልገው ያገኟታል። ዝናዋን የሰሙ ሌሎች አድራሻዋን አያጡትም ። ስትፈለግ ትገኛለች። ስትጠራ ትመጣለች።

ለዘቢደር አሁን ጅማና ቤተሰቦቿ ትዝታዎች ናቸው። የአቅሟን ቤት ተከራይታ መኖር ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። ዘቢደር ሥራ ባገኘች ግዜ እረፍት ይሉትን አታውቅም። የተሰጣትን ኃላፊነት በወጉ ልትወጣ ሌት ተቀን ትደክማለች።

ሁሌም እሳትና ሙቀት የማያጣው ውሎዋ አንዳንዴ በድካም ያልፋል። እንዲህ በሆነ ጊዜ ጤናዋ ከስጋት መውደቁ አይቀርም። አዲስ አበባ ስራውን ከጀመረች ወዲህ የስኳር ሕመም አግኝቷታል። ለመፍትሄው የምትወስደውን የኢንሱሊን መርፌ የምትወጋው በራሷ እጅ ነው።

ዘቢደር የስኳር ሕመሟና አድካሚ ስራዋ እየታገሏት ነው። ኑሮን አሸንፎ ለመቆም አትሆነው የለም። አንድ ቀን ግን ይህ አይነቱ ትግል ካላሰበችው አጋጣሚ አደረሳት። እየተራመደች ሳለ ሕመሟ ከመንገድ ጣላት። በዚህ መነሻ ችግሯ እየከፋ፣ ድካሟ እየባሰ ሄደ። ሕክምና ጀምራ፣ መድሀኒቷን ተከታትላ ወደስራዋ ተመለሰች።

በሌላ ቀን…

ከቀናት በአንዱ ዘቢደር እንደልማዷ ከቤት ወጣች። ክረምቱ ሊገባ ‹‹መጣሁ›› ማለት ይዟል። ዕለቱ ካለፉት ቀናት የተለየ አይደለም። ድካም ቢጤ ቢሰማትም መንገዷን አላቆመችም። ባልዘገየ፣ ባልፈጠነ እርምጃዋ ጉዞዋን ቀጠለች። ድንገት በእሷ ላይ የሆነው አጋጣሚ ግን ሁኔታዎችን እንዳልነበሩ ቀየራቸው።

ዘቢደር ዓይኗ ላይ የሆነ ነገር አጭበረበራት። ፊቷን በእጇ ከልላ ልትከላከለው ሞከረች። ማጭበርበሩ እንዳሰበችው አልተዋትም። እንደምንም መሬቱን ፈልጋ በዝግታ አረፍ አለች። ሰውነቷ ቦታ ከመያዙ አንዳች ነገር ዓይኖቿን ሲከልላት ታወቃት። አሁንም በእጇችዋ ፊቷን እየሞዠቀች ሁኔታውን ታገለችው። ማጭበርበሩን ተከትሎ በድንገቴ ጨለማ ተጋረደች።

ራሷን አላመነችውም። ብርሀን ፍለጋ ወደሰማይ አንጋጠጠች። ከጸሀይዋ ሙቀት በቀር የደረሳት የለም። ዓይኖቿን እየገለጠች፣ እየጨፈነች ጭላንጭል ፍለጋ ዋተተች። አዲስ ነገር አልተገኘም። በአፍታ ቆይታ ዓይኗ ከብርሀን ተራርቆ መሄጃዋ ጠፋት።

እንደምንም ከቤት ደርሳ የሆነባትን ለጎረቤት አዋየች። የሰሟት ሁሉ የምትለውን አላመኑም። የፈጠጡ ዓይኖቿን እያዩ ደህንነቷን አረጋገጡላት። በወቅቱ በአቅሟ ለመታከም ሞከረች። የዓይኗ ችግር ሞራ መሆኑ ተነገራት። እንደጅማሬው በርትታ አልቀጠለችም። ወጪው ሲከብዳት ቸልተኝነት አበዛች።

ዘቢደር ግራ ዓይኗን እንደጋረዳት በቀኙ ብቻ ስትመራ ከረመች። ይህ እውነት ግን ብዙ አልቀጠለም። በሌላ ቀን በድንገት የቀኝ ዓይኗም ተስፋ ተጋረደ። ሁለቱም ዓይኖቿ ከብርሀን ተጣልተው ከጨለማ ተዋደዱ። ዘቢደር በድንገት የጀመራት ችግር ከእይታ አራርቆ ዓይነ ስውርነትን አስተዋወቃት።

ትናንት በሩጫ የሚተጉ እግሮች ዛሬ ከቤት ውለዋል። ሰርተው የሚያበሉ እጆች አሁን በችግር ተይዘው የሰው ፈላጊ ሆነዋል። ከምንም በላይ ንቁና ፈጣን የነበሩ ውብ ዓይኖች በጠዋቱ በጨለማ ተጋርደዋል።

ዘቢደር ሁለት ዓይኖቿ ከታወሩ ጀምሮ የሕይወት አቅጣጫዋ ተቀየረ። ከመስራ ወደመቀመጥ፣ ከመኖር ወደ አለመኖር የቀየራት ክፉ አጋጣሚ ካልታሰበ መንገድ አዋላት። ትናንት የሚያውቋት በርካቶች ሊረዷት ተረባረቡ። ዝቅ ያለው ጉልበቷ፣ የታዘዘው ማንነቷ ጥሎ አልጣላትም። ቀን ቆጥሮ ዋጋዋን በመልካም መለሰ። ጎረቤቷቿ፣ ባልንጀሮቿ ታሪኳን የሰሙ ሁሉ ጎዶሎዋን ሊሞሉላት ፈቀዱ።

ጉዞ በነጭ በትር …

አሁንም የሕይወት ትግሉ ቀጠለ። ዘቢደር ከስኳር ሕመሟ እየታገለች ራሷን ልታሸንፍ ቆመች። የሚንከባለሉ ንጹህ ዓይኖቿ ዛሬም አስተውለው የሚያዩ ይመስላሉ። አሁንም በነጭ በትሯ እየተመራች የጎደለ ኑሮዋን ልትሞላ ተንቀሳቀሰች።

ትናንት ትሮጥበት የነበረ ሜዳ ዛሬ ዙሪያው ገደል ሆነባት። የምታውቀው ሁሉ ባዕድ መስሎ ተሰማት። ዘቢደር ከትናንት ማንነቷ ብዙ የሕይወት ሰበዞች ጎደሉባት። ሳታስበው የሌሎች ጥገኛ ያደረጋት ዓይነስውርነት ቀላል የማይባል ዋጋ ያስከፍላት ያዘ። በብዙ ክፉ አጋጣሚዎችም አመላለሳት።

‹‹ከንፈር መሀል ጥሬ››

በአንድ ምሽት በነ ዘቢደር መንደር ድንገቴ የእሳት አደጋ ተነሳ። ይህን ተከትሎም ጩኸት ግርግሩ በረከተ። ነገሩ ባስ ባለ ጊዜም ብዘዎች ሕይወታቸውንና ንብረታቸውን ለማዳን ሩጫ ጀመሩ። ሰፈሩ ሰባ ደረጃ ከሚባለው አካባቢ ነው። አብዛኛው ኑሮው በወንዝ ዳርቻ በመሆኑ አቅጣጫውን ወደ ውሀው አድርጓል።

እሳቱ እየባሰ ችግሩ ስር መስደድ ሲጀምር አብዛኛው እየተጠራራ ‹‹እግሬ አውጭኝ›› ሲል ከአካባቢው ራቀ። ይህ ሁሉ ሲሆን ብቸኛዋን ዓይነስውር ያስታወሳት አልነበረም። ዘቢደር እሳቱ ተቀጣጥሎ ከእሷ ጥግ እስኪደርስ በፍርሀትና በመቁነጥነጥ ቆየች። ተደግፋው ከቆመችበት ግንብ በቀር የጠበቃት አላገኘችም።

እሳቱ አራት ቤቶችን አቃጥሎ፣ ብዙ ንብረቶች አወደመ። ዘቢደር ጭሱና ወላፈኑ ወደእሷ ሲቀርብ ይሰማታል። አሁንም ግን የትነሽ ሲል የሚፈልጋት አልተገኘም። ደጋግማ እየጮኸችና እየጸለየች ፈጣሪዋን ‹‹እየኝ፣ ተመልከተኝ ›› ብላ ተማጸነች። ልመናዋ ከመሬት አልወደቀም። ‹‹ከንፈር መሀል ጥሬ›› እንዲሉ ያን የጨለማ ክፉ አጋጣሚ በተአምር አሸንፋ ከቀጣዩ ቀን ቆመች።

ዘቢደር ይህን ጨምሮ ሌሎች ክፉ ጊዚያትን በሚያስገርሙ አጋጣሚዎች አልፋለች። ነጭ በትሯን ይዛ ስትራመድ መኪና በጥሶ የጣለውን የኤሌክትሪክ ገመድ ከመርገጥ የዳነችበትን ቀን ዛሬም ድረስ አትዘነጋውም።

ዘቢደር ሁሌም የሚያግዟት ‹‹አይዞሽ›› የሚሏትን አታጣም። እንዲያም ሆኖ የብቸኝነት ሕይወት ይፈትናታል። በድንገት ቀኑ በጨለመባት ጊዜ ራሷን ከሁኔታዎች ማስማማት ይጠበቅባት ነበር።

ለእሷ ከድንገቴው የዓይነስውርነት ውጣ ውረድ ጋር መታገል ቀላል አልሆነም። ውላ አድራ ግን ችግር መከራውን ከራሷ አግባባችው። ለቅሶ፣ ትካዜን ትታ ውስጧን አበረታች፣ ጠነከረች። አንድ ሁለት ሲል መቁጠር የጀመረው ጊዜ እንደዋዛ ሰባት ዓመታትን ቆጠረ።

አንዳንዴ በሰዎች፣ ሌላ ግዜ በነጭ በትሯ እየተመራች አሁንም ራሷን ፈለገች። ብርቱዋ ዘቢደር ቀኗን በትካዜ ማሳለፍ ምርጫዋ አልሆነም። የሆነባትን ስታስብ ብታዝንም ውሎዋ በዚህ ስሜት እንዲታሰር አትሻም።

ልበ መልካሞች በሚያደርጉላት ድጋፍ እየታገዘች አስቸጋሪውን ኑሮ ቀጠለች። ውስጧ ተስፋ አላጣም። ከዓይነ ስውራን ትምህርትቤት ገብታ የብሬን ትምህርት ቀሰመች። ለእርምጃዋ እንዲበጅ የመንገድ አቅጣጫ ተሞክሮን ወሰደች።

ሰባ ደረጃን ከውሾች ጋር …

ዘቢደር የምትኖርበት የሰባ ደረጃ አካባቢ ለልማት ተፈልጓል። ነዋሪው ሰፈሩን ለመልቀቅ ጓዙን ከሸከፈ ሰንብቷል። እሷ ተከራይ ነች። ለእኔ የምትለው መጠጊያ የላትም። ቤቶች እየፈረሱ ሰዎች መውጣት ሲጀምሩ በእጅጉ ጨነቃት።

ቀስ በቀስ በዙሪያዋ የነበሩ ቤቶች ተነስተው ስፍራው ባዶ ሆነ። አከራዮቿ ቤታቸውን አፍርሰው ዕቃቸውን ይዘው ወጡ። ጣራው በተነሳ የግድግዳ ጥግ እሷና ውሾቿ ብቻ ቀሩ። ቀኑ አልፎ ምሽት ተተካ። ጨለማ የዋጠው አካባቢ በጭርታ ሲዋጥ ውስጧ ፍርሀት ነገሰ።

ሰፈሩን አቋርጦ የሚያልፍ ወንዝን ይዞ ብቅ የሚሉ ጅቦች ሁሌም ስጋት ናቸው። ይህን የሚያውቁ አንዳንዶች ዘቢደርን እያሰቡ የሚሆነውን ገመቱ። ዙሪያዋን ያሉት ታማኝ ውሾች ግን ‹‹አለንሽ›› ሲሉ ጠበቋት። ዘቢደር ከፈጣሪዋ በታች እነሱን አመነች። ብርድና ውርጩን ችላ የቀን ሌቱን ጨለማ አለፈች።

ዘቢደር በወንዝ ዳርቻ ሰው አልባ ሕይወት ከጀመረች ከአንድ ወር በላይ ሆኗል። ቀኑን አንደምንም አልፋ ምሽቱ ሲደርስ ይጨንቃታል። አሁንም ከፈጣሪ በታች ከሚጠብቋት ታማኝ ውሾች በቀር የደረሰላት የለም።

ዘቢደር አንድ ቀን በድንገት ታመመች። ውሾችና ወንዝ በከበባት ስፍራ ራሷን ማስታመም አልቻለችም። ይህኔ የዓይኖቿ መጥፋት ያጎደለባትን ሕይወት አስባ ከልብ አዘነች። ውሀ ቀድቶ የማይሰጣት ወገን ማጣቷ ልቧን ነካው።

ከቀናት በአንዱ ግን መልካም ዓይኖች ወደ እሷ ተመለከቱ። አንዲት ባልንጀራዋና የቀበሌው አመራሮች ደርሰው ከስፍራው አወጧት።

ዘቢደር ጓዝ ንብረቴን አላለችም። ሙሉ የቤት ዕቃዋንና ልብሷቿን እዛው ትታ ተከተለቻቸው። ሁኔታዋን ያየችው ሴት ልቧ ራራላት። ቀን አስኪያልፍ ብላ በቤቷ አስጠጋቻት። ዘቢደር ስጋትና ሕመም ሲፈራረቅባት የቆየው አካሏ ለጊዜው አረፍ አለ። እንዲያም ሆኖ ውስጧ ጤና የለውም። ሕመም እያዳከማት ነው። ሆስፒታል ገብታ ታክማ ተመለሰች።

ዘቢደር አሁን በጽኑ ታማለች። ሕይወቷን ለማዳን ሕክምና ያሻታል። ስለጤናዋ ግድ ያላቸው ስለእሷ ዝም አላሉም። በአስቸኳይ ከሆስፒታል አደረሷት። አሁን በቀላሉ ታክማ የምትወጣ አልሆነም። የስኳር ሕመሟ ለወራት አልጋ አስይዞ አስተኛት።

ዘቢደርን ያዩ የሕክምና ባለሙያዎች ከልባቸው አዘኑ። ድና ብትወጣ የምትሄድበት፣ እንደሌለ ባወቁ ጊዜ ሊረዷት ተባበሩ። አራት ወራትን ከሆስፒታሉ ግቢ ሳትወጣ ቆየች። ይህ በመሆኑ ዘቢደር አፏ ለምስጋና ተከፈተ። በዓይነስውር አቅሟ በወንዝ ዳር ያሳለፈችውን የብቸኝነትና የጨለማ ጊዜ አስባ ስለነገው ተስፋ ጣለች።

የሰኔው በረከት…

ከቀናት በአንዱ ዘቢደርን ያሉ ሰዎች ቀርበው አወሯት። ንግግራቸው። ስለዓይኗ ደህንነት ነበር። ሰዎቹ ‹‹የወደቁትን አንሱ የነዳያን ማህበር›› ከተሰኘ ድርጅት የመጡ ናቸው። ዘቢደር ዓይኗን ሊያሳክሟት እንደሚፈልጉ ስትሰማ ሳታቅማማ ተስማማች። ደርጅቱ እንደእሷ ጊዜና ዕድሜ ዘንበል ያለባቸውን ወገኖች በመደገፍ ይታወቃል።

ከሆስፒታሉ ወጥታ ወደ ድርጅቱ ገባች። አሁን ሰኔ ግም ማለት ጀምሯል። ከጥቂት ጊዚያት በኋላ ዓይኗ እንደሚታከም ቃል ተገብቶላታል። ዘቢደር እነዚህን ቀናት እስኪደርሱ በገጉት ጠበቀች። ተስፋዋ ለመለመ። አንድ ቀን የተያዘላት ጊዜ ቀጠሮው ደረሰ። ሕክምናውን ወደምታገኝበት ሀኪም ቤ ት ተጓዘች።

የሀኪሞቹ የመጀመሪያ ሰራ የቀኝ ዓይኗን ቀዶ ሕክምና መስራት ነበር። እንደታሰበው ሆኖ በስኬት ተጠናቀቀ። ዓይኗ ለቀናት ታሽጎ መቆየት ነበረበት።

ድንገቴው ብርሀን

እነሆ የታሸገው ዓይን ሊፈታ ቀኑ ደርሷል። ዘቢደር በቀጠሮው ዕለት ከሀኪም ዘንድ ቀርባለች። እሽጉን በጥንቃቄ መፈታት ተጀምሯል። እይታዋን ለማረጋገጥ ጥያቄ ቀረበላት። የሰጠችው ምላሽ አስደንጋጭም፣ አስደሳችም ነበር። በጨለማ ውሥጥ የኖረው ዓይኗ በትክክል ደማቁን ብር ሀን ማየት ጀም ሯል።

ዘቢደር ውስጧ ሲመላለስ የኖረው ግማሽ ተስፋ ዕውን ሆኗል። ሰባት ዓመታትን ከጨለማ የተዛመደ ማንነቷ አሁን በከፊል ከብርሀን ተዋዷል። ይህ ለእሷ ከሙሉ በላይ ነበር። እውነታውን የሰሙ ደስታዋን በእኩል ተጋሩ። የቀረቧትን እያየች በስም መጥራት ያዘች። አዲስ ዓለም፣ አዲስ ሕይወትን ተቀበለች።

ሁኔታው በዚህ ብቻ አልቆመም። ሁለተኛውን ዓይን ለመሰራት ሌላ ቀጠሮ ተይዟል። ከአንድ ወር በኋላ ዘቢደር ሀኪም ፊት ቀረበች። ልክ እንደቀድሞው ኣይነት ሕክምና መካሄድ ጀመረ። ግራ ዓይኗ ዳግመኛ ሕክምናውን አገኘ። የዘቢደር ውጤት ተመሳሳይ ነበር። ሁለቱም ዓይኖቿ በብርሀን ከለላ ተገናኙ

ያልጠለቀች ጀንበር …

እነሆ! የሰባት ዓመታት የጨለማ ምዕራፍ በ‹‹ነበር›› ተዘጋ። ይህ ልብ ወለድ መሰል ታሪክ በዚህች ሴት ዕውን መሆኑ የበርካቶች እጅን በአፍ አስጭኗል።

ልበ ቀናዋ ዘቢደር ዛሬ ብድር ከፋይ ሆናለች። በምትገኝበት ድርጅት ደካሞችን ደጋፊ፣ የወደቁትን አቃፊ ነች። ትናንት ከብርሀን፣ ወደጨለማ፣ መልሶም ወደ ብርሀን ላመጣት ፈጣሪዋ ምስጋናዋ የላቀ ነው። ከእሷ ጎን ለነበሩ ወዳጆቿ ሁሉ የተለየ አክብሮት አላት።

አሁን የስኳር ሕመሟ ጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑ ተረጋግጧል። ዘቢደር ድቅድቅ ጨለማዋ ተገፏል። ጀንበሯ አልጠለቀችም። ዛሬም በብርሀን መንገድ ልትመለላስ ውስጧ የበረታ፣ መንፈሷ የጠነከረ ነው።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You