ከዓለም ቁጥር አንድ የማራቶን ውድድሮች የሚመደበውና በርቀቱ በርካታ የዓለም ክብረወሰኖች የተሰበሩበት የበርሊን ማራቶን ነገ ይካሄዳል። የዓለም አትሌቲክስ የፕላቲንየም ደረጃ ከሰጣቸው ጥቂት የማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው ይህ የበርሊን ማራቶን 50ኛ ዓመቱን የሚደፍን ቢሆንም፤ ከዚህ ቀደም ድምቀት የሆኑት ከዋክብት አትሌቶች አይሳተፉም።
ላለፉት 11 ዓመታት በርሊን ማራቶንን ገናና ያደረጉትና ረጅም ዓመታትን እርስ በእርስ በመፎካከር የሚታወቁት ኢትዮጵያዊው ጀግና አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና ኬንያዊው ኢሉድ ኪፕቾጌ ነበሩ። ይሁንና ሁለቱ አንጋፋ የማራቶን ከዋክብት ከፓሪስ ኦሊምፒክ መልስ በሚደረገው በዚህ ውድድር ላይ አይገኙም። ባለፈው ዓመት በሴቶች የዓለም ክብረወሰንን ከእጇ ልታስገባ የቻለችውና የፓሪስ ኦሊምፒክ በርቀቱ የብር ሜዳሊያ ያጠለቀችው ትዕግስት አሰፉም በተመሳሳይ በበርሊን ማራቶን የተሳታፊዎች ዝርዝር ውስጥ የለችም። ነገር ግን በርቀቱ ፈጣን ሰዓት ያላቸው ወጣት አትሌቶች የ50ኛው ዓመት የበርሊን ማራቶን ድምቀት ለመሆን ተዘጋጅተዋል።
የኢትዮጵያ እና ኬንያ አትሌቶች በወንዶች እአአ ከ1999 አንስቶ በሴቶች ደግሞ ከ2009 አንስቶ አንድም የሌላ ሀገር አትሌት ሳይቀላቅሉ እርስ በእርስ በመተካካት የበላይነቱን ይዘዋል። በዚህ ውድድር የሚካፈሉት አትሌቶች አብዛኛዎቹ ወጣት ቢሆኑም እንደተለመደው አዲስ ነገር ያሳያሉ ተብለው ይጠበቃሉ። ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ታደሰ ታከለ እና ትዕግስት ከተማ ደግሞ ባላቸው ፈጣን ሰዓት በውድድሩ ከሚካፈሉ ታዋቂ አትሌቶች መካከል በቀዳሚነት ሊቀመጡ ችለዋል።
ባለፈው ዓመት በዚሁ የበርሊን ማራቶን ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ የቻለው አትሌት ታደሰ ታከለ በድጋሚ የጀርመኗ ከተማ ላይ ከትሟል። በ3ሺ ሜትር መሰናክል ሩጫዎች የሚታወቀውና ሀገሩንም በዓለም ከ20 ዓመት በታች እንዲሁም በአፍሪካ ቻምፒዮና በመወከል የብር ሜዳሊያ ማስመዝገብ የቻለው አትሌቱ በማራቶን የሁለተኛ ጊዜ ተሳትፎውን በበርሊን ያካሂዳል። የ22 ዓመቱ ወጣት ማራቶንን መሮጡ ጥያቄን ቢያጭርም ይበልጥ አስገራሚው ጉዳይ ግን በመጀመሪያ ተሳትፎው ስኬታማ መሆኑ ነው። በማራቶን የዓለም ፈጣኑን አትሌት ኪፕቾጌን ተከትሎ የገባበት 2:03:24 የሆነ ሰዓትም ፈጣን እና ከልምዱ አንጻር የማይጠበቅም ነበር። ይሁንና አትሌቱ ካለው ብቃት አንጻር በዚህ ውድድር አሸናፊ ሊሆን አሊያም ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆን እየተጠበቀ ነው።
በውድድሩ ከሚሳተፉ ታዋቂ አትሌቶች መካከል ፈጣን የሆነ ሰዓት ያላቸው አምስት ሲሆኑ በርቀቱ ያላቸው ፈጣን ሰዓትም ከ2 ሰዓት ከ05 ደቂቃ በታች ነው። ተጠባቂ ከሆኑት መካከል አንዱ ኬንዊው ኪብዎት ካንዳይ በተመሳሳይ የዘንድሮ የማራቶን ተሳትፎው ለሁለተኛ ጊዜ ነው። በግማሽ ማራቶን ውጤታማነቱ የሚታወቀው አትሌቱ ከዚህ ቀደም የርቀቱን ክብረወሰን መጨበጥ ችሎ ነበር። በቫሌንሺያ ግማሽ ማራቶንም ለተከታታይ ሶስት ዓመታት አሸናፊ መሆን ችሏል። በመሆኑም ይህ ውድድር በርቀቱ አዳዲስ በሆኑ አትሌቶች መካከል የሚደረግ መሆኑ ፉክክሩንም እጅግ አጓጊ አድርጎታል። ደማቁ የበርሊን ማራቶንም ከረጅም ዓመታት በኋላ አዳዲስ አሸናፊ አትሌቶችን ያገኛል በሚልም ይጠበቃል።
የሴቶቹ ምድብም በኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚመራ ሲሆን፤ ትዕግስት ከተማ እና ገንዘቤ ዲባባ ደግሞ አሸናፊ ይሆናሉ የሚል ቅድመ ግምት ያገኙ አትሌቶች ናቸው። የዘንድሮው የዱባይ ማራቶን አሸናፊዋ ትዕግስት የማራቶን ተሳትፎዋ ለመጀመሪያ ጊዜ ቢሆንም 2:16:07 በመሮጥ የቦታውን ፈጣን ሰዓት አስመዝግባለች። ከወራት በኋላ በተሳተፈችበት የለንደን ማራቶን ግን ሰባተኛ ደረጃን በመያዝ ነበር ያጠናቀቀችው። ሆኖም አትሌቷ ካላት ፈጣን ሰዓት አንጻር ለአሸናፊነት ከሚጠበቁት 10 የበርሊን ማራቶን የዘንድሮ ተሳታፊዎች መካከል ቀዳሚነቱን ልትይዝ ችላለች።
በሌላ በኩል በመካከለኛ ርቀት የመም ሩጫዎች ስኬታማዋ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ወደ ጎዳና ላይ ሩጫዎች ፊቷን ከመለሰች ወዲህ ብቃቷን የምታሳይበት መድረክ እንደሚሆን ይጠበቃል። በሪዮ ኦሊምፒክ የ1ሺ 500 ሜትር የብር ሜዳሊያ ባለቤቷ አትሌት ባለፈው ዓመት የቺካጎ ማራቶንን የሮጠችበት 2:21:47 የሆነ ሰዓት የግሏ ፈጣን በመሆን ተመዝግቦላታል። በኢትዮጵያ በኩል በርካታ አትሌቶች የሚካፈሉ ሲሆን፤ የብርጓል መለሰ፣ መስታወት ፍቅር፣ አዝመራ ገብሩ፣ ሲሳይ መሠረት፣ አባበል የሻነህ እንዲሁም ፍቅርተ ወረታ የአሸናፊነት ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም