በኃይል ቁጠባ መታገዝ ያለበት የኤሌክትሪክ ልማትና ተደራሽነት ማስፋፋት ጥረት

ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል በስፋት ማመንጨት የሚያስችሏት ሰፊ የውሃ፣ የንፋስ፣ የጸሀይ እንዲሁም የጂኦተርማል ሀብት እንዳላት ይታወቃል። ሀገሪቱ እያደገ የመጣውን የኤሌክትሪክ ሃይል ፍላጎቷን ለማርካትም በእነዚህ በተለይ የውሃ፣ የንፋስና የጸሀይ ሃይል ሀብቶቿን በመጠቀም የኤሌክትሪከ ሃይል ለማምረት በሰፊው እየሠራች መሆኑ ይታወቃል።

ሀገሪቱ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኤሌክትሪክ ሃይሏን በስፋት ስታመርት የቆየችው ከውሃ ሃይል ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከንፋስና የጸሀይ ሃይል ሃል በስፋት ወደ ማመንጨት ገብታለች።

በእዚህ የኤሌክትሪክ ሃይል ልማት የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ሃይል ፍላጎት ለመመለስ እየቻለች ከመሆኑ በተጨማሪ ለጎረቤት ሀገሮች ጭምር የኤሌክትሪክ ሃይል በመላክ የውጭ ምንዛሬ እያገስገባች መሆኗም ይታወቃል። በቀጣይም ከሌሎች ሀገሮች የኤሌክትሪክ ሃይል ጥያቄ እየቀረበላትም ነው።

ሀገሪቱ ይህን ሁሉ ሠርታም በኤሌክትሪክ ሃይል ተደራሽ ማድረግ የቻለችው ከሕዝቧ 54 በመቶውን ብቻ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። አብዛኛው በገጠር የሚኖረው የሀገሪቱ ሕዝብ / ከገጠሩ ሕዝብ ከ90 በመቶው በላይ ይባላል/ የኤሌክትሪክ ሃይል ተደራሽ እንዳልተደረግም እንዲሁ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ሀገሪቱ ይህን ሁኔታ ለመቀየርም ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች። ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር የገጠሩን ሕዝብ የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ለማድረግ እያከናወነች ካለችው ተግባር በተጨማሪ ከዋናው ግሪድ በርቀት ላይ የሚገኘውን የገጠሩን ማህበረሰብ በሌሎች የኢነርጂ አማራጮች የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ለሚያደርጉ ሃይል የማመንጨት ሥራዎችም ትኩረት ሰጥታለች።

ሌሎች መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ በሀገር ደረጃ በወጣው የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም 35 በመቶውን በኦፍ ግሪድ አማራጭ ለመድረስ ታቅዷል። 65 በመቶው ደግሞ ዋናው ግሪድ የሚደርስበት ይሆናል። ከዋናው ውጪ ያለው ሥራ በኦፍ ግሪድ የሚከናወን ይሆናል። በዚህም ዋናው የኤሌክትሪከ ግሪድ በማይደርስባቸው አካባቢዎች በሚኒ ግሪድና በመሳሰሉት ህብረተሰቡን ለመድረስ እየተሠራ ነው።

መቶ በመቶ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉንም አማራጮች አሟጦ መጠቀም የግድ እንደሚሆን ታምኖበት እየተሠራ ነው። መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ አብዛኛውን የማህበረሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ የኃይል ማመንጫ ፕሮግራሞች ተቀርፀው ተግባራዊ እየተደረጉ ናቸው።

ለእዚሀም በሀገሪቱ የአጭርና የረጅም ጊዜ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተረዳሽነት ፕሮግራም ተቀርፆ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል። ከዚህ አኳያ በምዕተ-ዓመቱ የልማት ግብ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመብራት ኃይል አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮግራም ወጥቶ እየተሠራ ይገኛል።

አሁን በተጀመረው አካሄድ 200 ያህል በሚሆኑ ከተሞች ላይ አነስተኛ ኃይል የሚያመነጩ ግሪዶችን ለማዳረስ እየተሠራ መሆኑን መረጃው ጠቁሞ፣ 100 በሚሆኑ ከተሞች ደግሞ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን አመልክቷል። ቀሪዎቹ በጨረታ ሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቁሟል። ሌሎች መቶ ያህል ከተሞች ደግሞ ለእዚሁ እየተዘጋጁ መሆናቸው ተገልጿል።

በባዮጋዝ መሠረተ ልማት ግንባታና በመሳሰሉት ላይ በሀገርም በክልሎች እንዲሁም በተቋማትና በግለሰቦች አቅም እየተሠራ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ከማልማት ጎን ለጎን ሃይል ቆጣቢ ምድጃዎችን ለማህበረሰቡ ለማድረስም ዘርፈ ብዙ ተግባሮች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በኤሌክትሪክ ሃይል ልማትና ተደራሽነት ማስፋፋት ላይ የሚሠራው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃኑ ወልዱ ሰሞኑን በተለይ ለኢፕድ እንደተናገሩት፤ ሚኒስቴሩ በእዚህ ልማትና ተደራሽነት ላይ ከአጋር አካላት፣ ከማህበራትና ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ይሠራል።

ሰሞኑንም ይህን የተመለከተ መድረክ ተካሂዷል። ከመድረኩ ዋና ዋና ዓላማዎች አንዱ የማገዶ ቆጣቢ እና የንጹህ ምድጃ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅ ነው። ሚኒስቴሩ በ2019 የወጣውንና 6085 የሚባለውን አዲስ የላቦራቶሪ ፕሮቶኮልንም አስተዋውቆበታል። ፕሮቶኮሉ በ2014 እንደገና መሻሻሉን አቶ ብርሃኑ ጠቅሰው፣ ከዓለም አቀፉ የአይሶ ስታንዳርድ ጋር ተዛማጅ እንዲሆን ተደርጎ መሻሻሉን አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ የገጠሩ ማህበረሰብ ቴክኖሎጂ ሲጠቀም በማገዶ ጢስ ለጉዳት እየተዳረገ ያለበት ሁኔታ እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ባሉት ዓለም አቀፍ ማህበረሰቦችም ጭምር የተወገዘ ነው። ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ያስፈልጋል፤ ጥቅም ላይ የሚውሉት ቴክኖሎጂዎች ግን በላቦራቶሪ መፈተሽ ይኖርባቸዋል፤ በጣም የተሻሻሉትን ለማውጣት የሚያስችል የላቦራቶሪ ፍተሻ ፕሮቶኮል ሊኖርም ይገባል።

በሀገሪቱ ንጹህ የኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን ከማስፋፋት አኳያ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ግዙፍ የጸሀይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በገጠሩ አካባቢ እያስገነባ ይገኛል ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ ባለፈውም ወደ 14 የሚሆኑ ሚኒ ግሪዶችን/ የሶላር ሃይል ማመንጫዎችን/ በመገንባት ለገጠር ትላልቅ ወይም አነስተኛ ከተሞች ሃይል ማቅረብ መቻሉን ጠቅሰዋል።

የእዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች ንጹህ የማብሰያ ምድጃ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ ግፊት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረው፣ ለእዚህም ለገጠሩ ማህበረሰብ ዘመናዊ ወይም ንጹህ ቴክኖሎጂዎችን ማቅረብ አለብን። የገጠሩ ማህበረሰብ የዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆን ሚኒስቴሩ ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የመረጃ አያያዝ ድክመት አለ። ይህን ሊያርም የሚችል ሥራ ተሠርቷል። ይህም የሶላር ተጠቃሚዎች እንዲሁም ሶላር ግሪዱ የት ይገኛሉ? የት አካባቢ የተቋም ሶላር አለ? የሚሉ ጥያቄዎችን የሚመልሱ መረጃዎችን በደንብ መያዝ እንዲያስችል የተዘጋጀው ዲጂታል መተግበሪያ ተሠርቷል፤ መተግበሪያው በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዌብ ሳይት ላይ ይጫናል። ማንኛውም አካል መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። በመድረኩ የቀረቡት ዋና ዋና ሃሳቦችም ይህን ይመስላሉ።

አቶ ብርሃኑ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ግሪዶችን በከፍተኛ ሁኔታ ለማስፋፋት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዋናው ግሪድም/ የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ/ የገጠሩን ማህበረሰብ ፍትሃዊ የኢነርጂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ሀገሪቱ ከዋናው የውሃ ሃይል በተጨማሪ ብዙ የኢነርጂ ምንጮች አሏት። ከእነዚህ መካከል አንዱ ባዮ ማስ ነው። አብዛኛው የሀገሪቱ ሕዝብ የሚኖረው በገጠር እንደመሆኑ የኢነርጂ ምንጩ በአብዛኛው ማገዶ ነው። ይህን ማገዶ ግን በጣም በሠለጠነና ኢነርጂ ቆጣቢ በሆነ መንገድ፣ ጤናን እና አካባቢን በማይጎዳ መልኩ እንዲጠቀም ለማድረግ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጥረት እያደረገ ይገኛል።

እነዚህን ቴክኖሎጂዎች ለገጠሩ ሕዝብ ለማድረስ የተለያዩ ተግባሮች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን ማውጣት፣ ቴክኖሎጂዎችን ከውጭ አምጥቶ ማላመድ ላይ በስፋት በመሥራት የገጠሩን ሕዝብ ኢነርጂ የመጠቀም ፍላጎት ለማርካት በስፋት እየተሠራ ነው።

በዚህ ሥራም እስከ አሁን ወደ 20 ነጥብ 5 ሚሊየን የተሻሻሉ የምድጃ ቴክኖሎጂዎች ተሠራጭተዋል ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ ይህንን አሃዝ እስከ 2030 ድረስ ወደ 31 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ለማሳደግ ይሠራል ሲሉ ጠቁመዋል። ዘንድሮ ወደ ሁለት ሚሊዮን የተሻሻሉና ንጹህ የኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን ለማሰራጨት እየተሠራ ነው ይላሉ።

ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በኩል በአብዛኛው የኤሌክትሪክ ምድጃዎችን ስናይ ሃይል ቆጣቢ ናቸው ተብሎ አይታሰብም ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፣ በሀገሪቱ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ብክነት እንደሚታይ ጠቁመዋል። ይህ ችግር አሁን እየጨመረ ከመጣው የኤሌክትሪክ ሃይል ዋጋ ጋር ተያይዞ በህብረተሰቡ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳርፍ ገልጸው፣ ሃይል ሊቆጥቡ የሚችሉ የምድጃ ቴክኖሎጂዎች እንደሚያስፈልጉ አጽንኦት ሰጥተው አስገንዝበዋል።

እንደ አቶ ብርሃኑ ማብራሪያ፤ የሃይል ብክነቱ ለቤተሰብ ብቻም ሳይሆን ለሀገርም ትልቅ ሸክም ነው። ብዙ ፋብሪካዎች ሊጠቀሙበት የሚገባ ኢነርጂ ቤት ውስጥ እየባከነ ነው። ይህን ችግር ለመፍታት እነዚህን ቴክኖሎጂዎች በሀገሪቱ ማስፋፋት የግድ ይሆናል።

ኢነርጂ ማመንጨቱ ብቻውን ዋጋ የለውም፤ በቁጠባ መጠቀምም ያስፈልጋል ሲሉም አስገንዝበው፣ ይህን ብክነት ለመቀነስ የቤተሰብን የንጹህ ምድጃ አጠቃቀም እንዲሁም የቴክኖሎጂዎችን ብቃት ማሻሻል ወሳኝ ይሆናል ብለዋል።

ከዚህ አኳያ ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለሥልጣን ጋር በመሆን አዳዲስ ሃይል ቆጣቢ ምድጃዎችን በማስፈተሽና የተለጣፊ ምልክት በመስጠት እነዚያ ቴክኖሎጂዎች ብቻ ገበያ ውስጥ ገብተው እንዲሠራባቸው ለማድረግ እየተሠራ ነው። ለእዚሀም የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግም ጥረት እያደረገ ይገኛል።

የሚኒስቴሩ እንዱ ሥራ ቴክኖሎጂዎችን ከውጭ በማምጣት፣ የመጡትን ቴክኖሎጂዎች በማላመድ እንዲሁም በሀገር ውስጥ በመሥራት ማህበረሰቡን የዘመናዊ ኢነርጂ ተጠቃሚ ማድረግ መሆኑን አስታውቀዋል።

አቶ ብርሃኑ ከዚሁ ጎን ለጎንም በአሁኑ ወቅት አነስተኛ ወንዞችን ጭምር ለሃይል ልማት ለማዋል እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል። በተለይ ከዋናው ግሪድ የራቁ አካባቢዎችን የኢነርጂ ተጠቃሚ ለማድረግ ይህ አንዱ አማራጭ ተደርጎ እየተሠራበት ስለመሆኑም አመልክተው፣ በዚህም የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እየተደረጉ ናቸው ይላሉ።

ባለፈው ዓመት በዚህ ላይ ወደ ሶስት ፕሮጀክቶች ሲካሄዱ እንደነበር ጠቅሰው፣ ከእነዚህ የአንዱ ግንባታና የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራ መጠናቀቁን አስታውቀዋል። በዚህም ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ አቶ ብርሃኑ ተናግረው፣ ሁለቱ ፕሮጀክቶች ደግሞ በተለያየ የግንባታ ደረጃ ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።

እሳቸው እንዳሉትም፤ ሀገሪቱ ብዙ የውሃ ሀብት አላት፤ አስራ ሁለት ተፋሰሶች አሏት። በእነዚህ ውስጥ ያሉት አነስተኛ ወንዞች ሃይል ሊያመነጩ የሚችሉ ናቸው። የሀገሪቱ የመሬት አቀማመጥ ከወንዞቹ ሃይል ለማመንጨት የተመቸ ነው። በዚህ መሠረት በተለይ ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ርቀው የሚገኙ አካባቢዎችን የሃይል ተጠቃሚ ለማድረግ እነዚህን ወንዞች ለሃይል ምንጭነት ለመጠቀም እየተሠራ ይገኛል። ይህ ሥራ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል፤ እስከ 2030 ድረስ የአነስተኛ ወንዞች ኢነርጂ ልማት ግንባታን በማከናወን በርካታ ዜጎችን የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ እናደርጋለን ሲሉም ጠቁመዋል።

ሀገሪቱ ለመስኖ ልማት ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መሆኑ ይታወቃል። የመስኖ ልማቱ ከሚካሄድባቸው መንገዶች አንዱ በነዳጅ የሚሠሩ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች /ዲዝል ፓምፓች/ በመጠቀም ነው። ለእዚህም ምናልባት በሀገሪቱ ከ500 ሺህ በላይ ሊሆኑ የሚችሉ ዲዚል ፓምፖች ለመስኖ ልማት ሥራ እያገለገሉ ናቸው።

እነዚህን በነዳጅ የሚሰሩ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን በሶላር በሚሠሩ የውሃ መሳቢያዎች ለመተካት አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ ይገኛል። እሳቸው እንዳሉትም በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ከእነዚህ ፓምፓች 50 በመቶውን በሶላር ቴክኖሎጂዎች ለመቀየር እየተሠራ ነው።

እሳቸው እንዳመለከቱት፤ ይህ እውን ሲሆን አርሶ አደሮች ነዳጅና ዘይት ፍለጋ አይንከራተቱም፤ ሶላር ቴክኖሎጂ በመጠቀም ከመሬት ውስጥም ይሁን ከመሬት ላይ ያለውን ውሃ በመጠቀም የመስኖ ልማት ሥራቸውን የሚያካሂዱበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየተሠራ ይገኛል።

ይህ ብቻም አይደለም ለግብርና ምርቶች ማቆያ ማቀዝቀዣዎች እንደሚያስፈልጉ ይታወቃል። ለእዚህም የድህረ እና ቅድመ ምርት ሶላር ቴክኖሎጂዎች የሚጠቀሙ ማቀዝቀዣዎች /ኩለር/ አርሶ አደሩ እንዲጠቀም ለማድረግ የተለያዩ የሙከራ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም አቶ ብርሃኑ ጠቁመዋል።

ኃይሉ ሣህለድንግል

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You