የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጦራቸው ከሔዝቦላሕ ጋር በሙሉ ኃይሉ እንዲዋጋ አሳሰቡ

አዲስ አበባ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከአሜሪካና ሌሎች አጋሮቻቸው በኩል ተኩስ እንዲያቆሙ ቢጠየቁም ወታደሮቻቸው ሔዝቦላሕን በሙሉ ኃይል እንዲፋለሙ አሳስበዋል።

የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር ሐሙስ ብቻ በአየር ጥቃት 92 ሰዎች መገደላቸውን ይፋ አድርጓል። ሔዝቦላሕ በበኩሉ በደቡባዊ ቤይሩት እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት የቡድኑ የድሮን ክፍል ኃላፊ መሐመድ ሱሩር መገደሉን ይፋ አድርጓል።

በሔዝቦላሕ እና እስራኤል መካከል የሚደረገው ውጊያ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ ስጋት አለ። እስራኤል ከሰኞ ጀምሮ በሊባኖስ ጥቃት እያደረሰች ትገኛለች። በተባበሩት መንግሥታት የእስራኤል አምባሳደር ዳኒ ዳነን ሀገራቸው ለውይይት በሯ ክፍት ነው ማለታቸውን ተከትሎ የተኩስ አቁም ተስፋ ተደርጎ ነበር።

ሆኖም ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ሃሳቡ በእስራኤል ፖለቲከኞች ሙሉ በሙሉ ውድቅ ተደርጎ ጦርነቱ ቀጥሏል። ለተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ኒው ዮርክ የሚገኙት ኔታንያሁ ሀገራቸው እስራኤል ‘’ግቧን እስክትመታ’’ ጦርነቱን እንደማታቆም ዝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግብ አድርገው ካስቀመጧቸው ነገሮች አንዱ በሰሜን እስራኤል የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ማስቻል ነው።

‘ኋይት ሐውስ’ በበኩሉ ኔታንያሁ ይህን ይበሉ እንጂ የተኩስ አቁሙ በመልካም ሁኔታ እየተሳለጠ ነው ብሏል። የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪየር ስታርመር በሊባኖስ ያለውን ችግር ለመቅረፍ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀዋል።

የእርሳቸው ስጋት ይህ ጦርነት ገደቡን ጥሶ ከወጣ ማንም የሚቆጣጠረው አይሆንም የሚል ነው። እስራኤል በጋዛ የከፈተችውን ዘመቻ ተከትሎ በጦርነት ስጋት 70ሺህ የእስራኤል ዜጎች ከሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ ወደ ሌላ ሥፍራ እንዲሄዱ ተደርጓል። ይህም ሔዝቦላሕ ሊያደርስ የሚችለውን ስጋት በመፍራት የተካሄደ ነው።

በሊባኖስ በኩል ደግሞ ባለፉት አራት ቀናት ብቻ 90 ሺህ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ከዚህ ቀደም ብሎ ደግሞ ጦርነቱን በመፍራት 110 ሺህ ነዋሪዎች ከቤታቸው ሸሽተዋል ይላል የተባበሩት መንግሥታት።

እስራኤል ከሰሞኑ በፈጸመችው ጥቃት ሔዝቦላሕ የስንቅና ትጥቅ ማስተላለፊያ ይሆኑታል የተባሉ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል። ይህም በሶሪያና ሊባኖስ ድንበር የሚገኝ ነበር።

ሔዝቦላሕ በበኩሉ 50 ሮኬቶችን ወደ ኪርያት አታ ከተማ እንዲሁም 80 ሚሳኤሎችን ወደ ሳፌድ ከተማ ተኩሻለሁ ብሏል። ሁለቱም የሰሜን እስራኤል ከተሞች ላይ የደረሰው ጉዳት በውል አይታወቅም። እስራኤል ከየመን የተተኮሰ ሚሳኤል አከሸፍኩ ብላለች።

የእስራኤል አየር ኃይል ኮማንደር ጄኔራል ቶመር ባር ሐሙስ ለወታደሮቻቸው ሲናገሩ አሁን እየተካሄደ ያለው ኦፕሬሽን ወደ ሊባኖስ እግረኛ ለማስገባት የሚያዘጋጅ ነው ብለዋል።

ይህ በእንዲህ ሳለ የኳታር መንግሥት ቃል አቀባይ ማጂድ አል አንሳሪ ሀገራቸው በሊባኖስ አሰቃቂ የቤተሰብ እልቂት ዜናዎች እየደረሷት እንደሆነ ተናግረዋል። የንጹሃን ሰቆቃው የጋዛን የሚመስል እንደሆነም ተናግረዋል።

የዩኬና የአውስትራሊያ አቻዎቻቸው ጋር የተነጋገሩት የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን ሁለቱ ተዋጊዎች ወደለየለት ጦርነት እንዳይገቡ ብቸኛው መንገድ ዲፕሎማሲ ነው ብለዋል።

ሐሙስ ምሸት የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር 8 ነጥብ 7 ቢሊዯን ዶላር የሚገመት እገዛ ከአሜሪካ ማግኘቱን ይፋ አድርጓል ሲል የዘገበው ቢቢሲነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You