ሆቴልና ሪዞርቶች ለኢሬቻ በዓል ቅናሽ እያደረጉ ነው

አዲስ አበባ፡- ሆቴልና ሪዞርቶች ለዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ቅናሽ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ቱሪዝምና ሆቴል ማርኬት ማህበር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ቱሪዝምና ሆቴል ማርኬት ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታሁን አለሙ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ለኢሬቻ በዓል ታዳሚዎች ሆቴልና ሪዞርቶች ከ30 በመቶ ጀምሮ ቅናሾችን አድርገዋል። በተያዘው ወር ለኢሬቻ በዓል ሆቴሎች የራሳቸውን ቅድመ ዝግጅት አድርገዋል ያሉት አቶ ጌታሁን፣ ለኢሬቻ በዓል ታዳሚዎች ሆቴልና ሪዞርቶች ከ30 በመቶ ጀምሮ ቅናሾችን አድርገዋል ብለዋል።

በዓሉን ለመታደም ለሚመጡ እንግዶች በወንጪ ሪዞርትና በሸራተን ሆቴል የቅናሽ አገልግሎት እንደሚያገኙ ጠቅሰው፣ ሌሎች ሆቴሎችም በኢሬቻና በመስቀል በዓል ላይ የተለያዩ ጥቅሎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በአደባባይ በዓላቱ የዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች እንደሚሳተፉ በመግለጽ፣ በዓላቱን ተከትሎ ሆቴሎች ገቢአቸውን ለመጨመር የራሳቸውን ጥቅሎች እንደሚያዘጋጁ ጠቁመዋል።

ለኢሬቻ በዓል የተለያዩ የኦሮሞ የባህል ምግቦችን የሚያዘጋጁ ሆቴሎች መኖራቸውንም ጠቅሰው፣ የአደባባይ በዓላት ለሆቴሉ ዘርፍ ገቢን በማሳደግ ከፍተኛ መነቃቃት እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል።

የስካይላይት ሆቴል የሽያጭ ክፍል ኃላፊ አቶ አየሁ ገሰሰ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚያስተዳድረው የወንጪ ሪዞርት ላይ ለኢሬቻ በዓል ከ35 እስከ 45 በመቶ ቅናሽ ተደርጓል።

ለኢሬቻ በዓል በወንጪ ሪዞርት መኝታ ቀድመው መያዝ እንደሚችሉ ጠቅሰው፣ በሪዞርቱ በሚሰጡ የመኝታ፣ ምግብና መጠጥ አገልግሎቶች ላይ ከመደበኛ ዋጋ ከ35 እስከ 45 በመቶ ቅናሽ መደረጉን ገልጸዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች የቅናሽ አገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን ቀድመው መመዝገብ እንደሚጠይቅ በመግለጽ፣ የዋጋ ቅናሹ ከመስከረም 13 ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን እስከ በዓሉ ዕለት ድረስ እንደሚቆይ ጠቁመዋል።

ለኢሬቻ በዓል በስካይላይት ሆቴል ባህላዊ ሬስቶራንቶች ላይ በዓሉን የሚገልጹ ምግብና መጠጥ አገልግሎቶች እንደሚቀርቡ የገለጹት ኃላፊው፣ በዓሉ ባህላዊ ሬስቶራንቶች ላይ የተለያዩ ዝግጀት የተደረገ ሲሆን አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ብለዋል።

በደቡብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሚከበሩትንም የዘመን መለወጫ በዓላት ላይም የተለያዩ ልዩ መርሃግብሮች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው፣ የመስከረም ወር በርካታ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች፣ የአደባባይ በዓላት የሚካሄዱበት በመሆኑ በሆቴል ገበያው ላይ መነቃቃት መፍጠሩን ገልጸዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You