ባህል በመለያነት የአንድ ማህበረሰብ ሊሆን ይችላል። ባህሉን የሚያንፀባርቀው የሆነ አካባቢ ማህበረሰብ ሊሆን ይችላል። የፈጠረውና ያዳበረው አንድ ማህበረሰብ ሊሆን ይችላል። ይህ ማህበረሰብ ምናልባትም ‹‹የባህሉ ባለቤት›› ሊባል ይችላል፤ ምናልባትም በተለየ መንገድ ሊኮራበትም ይችላል።
አንድን ባህልና ሥርዓተ ክዋኔ ግን ‹‹የእገሌ ብቻ ነው›› ማለት እልም ያለ ኋላቀርነት ነው። በዚህ ዓለም አንድ በሆነበት ዘመን፣ በአንድ አካባቢ የሚከወን ሥርዓተ ክዋኔ ብዙዎች ጋ የመድረስ ዕድል አለው። በብዙዎች የመታየት ዕድል አለው። ስለዚህ ብዙ ሰው ይጋራዋል፤ ብዙ ሰው ሊወደው ይችላል ማለት ነው።
በነገራችን ላይ ‹‹ዓለም አንድ ሆናለች፣ ዘመኑ የሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ነው›› ሲባል የግድ በቴክኖሎጂ ውጤቶች ብቻ አይደለም። ዓለም አንድ ሆናለች ሲባል በአመለካከት ጭምር ነው። ከሰፈርና ከመንደር አጥር በመውጣት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ሰው ሩቅ ምሥራቅም ሆነ ሩቅ ምዕራብ ያለ ነገር የራሱ መንደር ጭምር ነው። ከመልከዓ ምድራዊ መንደርነት መውጣት አለበት። በዚህ ዘመን የትኛውም የዓለም ጫፍ ላይ የሚደረግ ነገር ጠቃሚ ሆኖ ካገኘው የትኛውም የዓለም ጫፍ ላይ የሚኖር ሰው ይጠቀመዋል። ‹‹ይህ የኔ አይደለም፣ እኔ የፈጠርኩት አይደለም፣ የኔ ወገኖች የፈጠሩት አይደለም…›› ብሎ አይተወውም፤ ምክንያቱም ቴክኖሎጂው ብቻ ሳይሆን አመለካከታችንም አንድ እየሆነ ነው። በአጭሩ የማንም ነገር የሁሉም ነው።
ሰሞኑን የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላት በኢትዮጵያ ይከበራሉ። በተለይም ኢሬቻ ደግሞ በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ በልዩ ሁኔታ ይከበራል። የመስቀል በዓል ደግሞ በሰሜን እና በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በአዲስ አበባ፣ በልዩ ሁኔታ ይከበራል። በልዩ ሁኔታ የሚከበሩበትን ማለታችን እንጂ ሁለቱም ከተጠቀሱት ቦታዎች ውጭም ይከበራሉ። የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱ የሚጎላ ቢሆንም በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ግን መልከ ብዙ በዓል ነው።
ኢሬቻም ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት ሃይማኖታዊ መልክ ያለው ቢሆንም የኦሮሞ ባህልና እሴት የሚንፀባረቅበት በዓል ነው። በተለይም ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት በአዲስ አበባና ቢሾፍቱ በልዩ ሁኔታ እየተከበረ ነው።
የአጀንዳችን ዋና ጉዳይ ግን የእነዚህን በዓላት ምንነትና አከባበር ማብራራት አይደለም። እነዚህ በዓላት አጀንዳ በሆኑ ቁጥር በአንዳንድ ወገኖች ብሽሽቅ የሚኖረው ለምንድነው? ‹‹የኛ ነው አትንኩብን!››፣ ‹‹የእናንተ ነው አይመለከተንም!›› የሚባለው ለምንድነው?
ዓለም አንድ ሆናለች ስንል በአመለካከት ጭምር ነው ብለናል። ስለዚህ በአንድ ትንሽዬ መንደር ውስጥ የምትደረግ ነገር ዓለምን ልታዳርስ ትችላለች። ይህ የሚሆነው ነገርየውን ለማዳረስ የሚያስችል ፈጣሪን የቴክኖሎጂ ግብዓት ስላለ አይደለም፤ ይልቁንም የጋራ ፍላጎት፣ የጋራ ስሜት፣ የጋራ ደስታና ኀዘን ስለሚፈጠር ነው።
የሰሞኑ አጀንዳ ኢሬቻ ነውና ኢሬቻን ምሳሌ እናድርግ። በኢሬቻ ሥርዓተ ክዋኔ ውስጥ የሚደረጉ ነገሮችን ስናይ ሥርዓተ ክዋኔውን ከሚፈጽሙ ሰዎች እኩል እንደሰታለን፤ በሚደረጉ ነገሮች እንደመማለን። ለዚህ ዝግጅት በተዋቡ ቆነጃጂት እንማረካለን፤ ይህ ተፈጥሯዊ ግዴታ ነው። ባህላዊ ጭፈራዎችም ሆኑ ትውፊታዊ ክንውኖች ያስደስቱናል።
ይህን ስል ግን ሁሉም ሰው ይደሰታል ማለት አይደለም። የማይደሰት ይኖራል፤ ጭራሽ ይባስ ብሎ የሚናደድም ይኖራል። ‹‹ለምን?›› እና ‹‹ማን?›› የሚሉ ጥያቄዎችን እንያቸው።
በእንዲህ አይነት ሥርዓተ ክዋኔዎች የማይደሰት ይባስ ብሎም የሚናደድ ውስጡ ነፃ ያልሆነ ሰው ነው። ነፃ ያልሆነው ደግሞ በጥላቻ ነው። ይህ ማንንም ሳይሆን የሚጎዳው ራሱን ነው። ‹‹አለመውደድ፣ አለማድነቅ…. መብት ነው›› ሊባል ይችላል። አዎ! መብት ነው! በግድ ውደድ ሊባል አይችልም። ሲጀመር ይህ ስሜት እንጂ በትዕዛዝ የሚሆንም አይደለም። በዚህ ዘመን መብትን ማክበር መሠልጠን ነው። ልብ ማለት ያለብን ግን ያልወደደበት ምክንያት ከመብት አንፃር ብቻ አይደለም። ከጥላቻ ነው፤ ውስጣዊ ነፃነት ከማጣት ነው። በፖለቲካዊ መንገድ የሚባሉ ነገሮች ተፅዕኖ ስለሚያደርጉበት ነው። ለሆነ አካል ስለሰጠው ነው። ‹‹አለመውደድ መብት ነው›› ብለን ማለፍ እንችል ነበር፤ ችግሩ ግን ይባስ ብሎ እንደ ጭቆና የሚያየውም አለ። መከናወኑን የሚቃወም አለ። ንቆ መተው ይቻላል፤ ዳሩ ግን እንዲህ አይነት ትንንሽ ነገሮች ሲደማመሩ የትርክት ተፅዕኖ ይፈጥራሉ። የምርም ሰዎችን ለመጉዳት የሚደረግ ሥርዓተ ክዋኔ ነው ብሎ የሚያምን ይኖራል። ልብ መባል ያለበት ነገር ግን በዚህ ዘመን የትኛውንም ባህልና ሥርዓተ ክዋኔ አለማክበር ኋላቀርነት መሆኑን ነው።
እዚህ ላይ ግን አንድ ልብ መባልና ደፈር ብሎ በግልጽ መነገር ያለበት ነገር የመንግሥት አካላት ቱባ የሆኑ የማህበረሰብ መገለጫዎችን ከፖለቲካ ጋር መቀላቀላቸውን ነው። ይህን እየተሸፋፈኑ ማለፍ ራስን መሸወድ ነው። ዜጎችን የበለጠ ወደ እልህና ጥላቻ እንዲገቡ ማድረግ ነው። ዜጎች በፍርሃት ዝም ቢሉ እንኳን በውስጣቸው ግን ማማረራቸው አይቀርም። እንዲህ አይነት የማህበረሰብን መገለጫ ባህል ሰዎች በንጹህ ልባቸው እንዲወዱት ማድረግ እንጂ በብሽሽቅ እና በእልህ መጫን አይቻልም። አሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ኢሬቻ… በመሳሰሉት ባህላዊ በዓላት ላይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የሚያደርጓቸው ንግግሮች ብሽሽቅ የተጫናቸው ናቸው። ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በፖለቲካዊ መድረኮች መናገር ሲገባቸው በእንዲህ አይነት የባህል ጨዋታ መድረኮች ላይም ይናገራሉ። ከብዙ ዘመናት በፊት የነበረ ነገር እያመጡ ‹‹ድሮ እንዲህ ይደረግ ነበርና…›› ይላሉ። በቃ! እሱ የተደረገው ድሮ ነው!
በተቃውሞ ጎራ ያሉት ደግሞ በፖለቲካ ትግል አልሳካላቸው ሲል እንዲህ አይነት ባህላዊ ነገሮችን እንደ አጀንዳ ይጠቀሟቸዋል። እንቶኔ በእንቶኔ ላይ የጫነው ነው ይላላሉ። ወይም ፀጉር በመሰንጠቅ ይህ የተደረገው እንዲህ ለማድረግ ተፈልጎ ነው በማለት ሰው ያላሰበውን ያሳስባሉ፤ ያልታሰበና ያልተቀኜ ቅኔ ካልፈታነው ይላሉ። ደግነቱ ግን ሁለቱንም ሕዝብ እየነቃባቸው ነው። ያም ሆኖ ግን ተፅዕኖ መፍጠሩ አይቀርም።
ስለዚህ የሁላችንም አመለካከት የዘመኑነን ሰዋዊ ነፃነት የሚመጥን መሆን አለበት። የአንዱ አካባቢ ውብ ባህል ለሌላውም ውብ የሚሆነው በንፁህ ልቦና ሲታይ ነው፣ በንጹህ ልቦና ሲከበር ነው። በአንዲት የዓለም ዳርቻ የተደረገ ነገር ሰፍ ብለን የምናየው ነገርየው በራሱ እንድንወደው ስላደረገን እንጂ ሰው አስገድዶን አይደለም። አሸንዳንም ሆነ ኢሬቻን የምንወደው ውብ ባህሉን እንጂ የሕወሓት ወይም የብልጽግና ካድሬ አስገድዶን አይደለም። በመንግሥት በኩል ይህ ልብ መባል አለበት።
አንዳንድ ወገኖች ደግሞ ነገርየውን መንግሥት የፈጠረው የሚመስላቸው አሉ። እንዲህ አይነት ባህሎችና ትውፊቶች ለሺህ ዘመናት በውርርስ የመጡ እንጂ መንግሥት የፈጠራቸው አይደለም፤ የሕዝብ ናቸው። እንዲህ አይነት ባህሎች እንዲከበሩ መንግሥት ደግሞ ማመቻቸት አለበት፣ ኃላፊነቱም ነው። በአንድ በኩል የራሳችን ለሆኑ ነገሮች ትኩረት ይሰጥ እያልን በሌላ በኩል ደግሞ መበሻሸቅ አያዋጣም። ሲጠቃለል፤ በዚህ ዘመን የማንም ባህል የሁሉም ነው!
ሚሊዮን ሺበሺ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም