በጢያ ትክል ድንጋይ አካባቢ ሎጅ ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ፡- ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በጢያ ትክል ድንጋይ አካባቢ ሎጅ ለመገንባት እየተሠራ ነው ሲል ክልሉ አስታወቀ፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በጢያ ትክል ድንጋይ ሎጅ ለመገንባት እየተሠራ ነው፡፡

ክልሉን የቱሪዝም መዳረሻና ተመራጭ ለማድረግ ከጢያ ትክል ድንጋይ እስከ አምበርቾ 77 ተራራ ድረስ ያለውን የቱሪዝም ሀብት ሎጅና የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን የመገንባትና የማሟላት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የጢያ ትክል ድንጋይን ለቱሪዝም ክፍት ለማድረግ ቦታውን የሚመጥን ሎጅ መገንባት ያስፈልጋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ እስካሁን ድረስ የፕሮጀክት የዲዛይን ሥራ ተጠናቋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቱሪዝም መስህብ ከሆኑት ጥንታዊ ቦታዎች ውስጥ አንዱ የጢያ ትክል ድንጋይ ነው ያሉት አቶ እንዳሻው፤ የጢያ ትክል ድንጋይን የሚመጥን ሎጅ ለመገንባት ፕሮጀክት ተቀርፆ በትኩረት እየተሠራበት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ክልሉ ጢያ ትክል ድንጋይን፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን ማለትም የተለያዩ ሀይቆች፣ ተራራዎችና ሌሎች የተፈጥሮ ፀጋዎችን የታደለ ቢሆንም፤ የታደለውን የተፈጥሮ ሀብትና ታሪካዊ ቦታዎችን ተጠቅሞ ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆኑ በማድረግ በኩል የተሠራ ሥራ አለመኖሩን ጠቁመው፤ አሁን ክልሉን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ያለውን የቱሪዝም ሀብት አሟጦ በመጠቀም ለዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠርና ክልሉ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንዲያገኝ ለማድረግ እየተሠራ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ክልሉ የጢያ ትክል ድንጋይ፣ የተፈጥሮ ሀብቶች በተጨማሪም የማይዳሰሱ የቱሪዝም መስህቦች ማለትም የሀዲያ፣ የጉራጌ፣ የከምባታና የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ባህል፣ እሴት፣ የመስቀል በዓል የመሳሰሉ አሉ ያሉት አቶ እንዳሻው፤ ክልሉ ያሉትን የማይዳሰሱ የቱሪስት መስህብ ለሕዝብ ክፍት እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ እየሠራ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቱሪዝም መዳረሻ ለጎብኚዎች ምቹና ብቁ በማድረግ የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አቅም ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ክልሉ ከአዲስ አበባ ከተማ ያለው ርቀት ቅርብ በመሆኑ የመጎብኘት እድሉ ሰፊ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ያልተነካ የቱሪዝም ዘርፉን በመንካት ለማሳደግ እየተደረገ ያለው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2016

 

Recommended For You