ወጣቶች የሃሳብ ልዩነት ቢኖራቸውም የመዲናዋን ሰላም ለማረጋገጥ በአንድነት ሊሳተፉ ይገባል

አዲስ አበባ፡- የመዲናዋ ወጣቶች የሃሳብ ልዩነት ቢኖራቸውም የአዲስ አበባን ብሎም የሀገርን ሰላም ለማረጋገጥ በአንድነት መሳተፍ ይኖርባቸዋል ሲል አዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

“የሰላም፣ ባህልና አመለካከትን የመገንባትና የመምራት ክህሎት” በሚል መሪ ሃሳብ የመዲናዋን ሰላም ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ስልጠና ለአዲስ አበባ ወጣቶች ሰሞኑን ተሰጥቷል።

በአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊና የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ አለማየሁ እጅጉ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገር በሰላም ዙሪያ በርካታ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል። ወጣቶችም የከተማዋን ሰላም ለማረጋገጥ በአንድ ፓርቲ ሳይወሰኑ ሲያበረክቱ የነበረው ሚና ከፍተኛ ነው።

ወጣቶችም ትውልድ በአንድ ፓርቲ ሳይወሰን ለከተማዋ ሰላም መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ሲያበረክት መቆየቱን የገለጹት አቶ አለማየሁ፤ ይህም ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡

የመዲናዋ ወጣቶች ያሉባቸውን ፈተናዎች አልፈው አዲስ አበባ አሁን ያለችበትን ገጽታ እንድትይዝ አስችለዋታል ያሉት አቶ አለማየሁ፤ በቀጣይም ወጣቱ የሃሳብ ልዩነት ቢኖረውም በሰላም፣ በልማት እንዲሁም በበጎ ተግባራት ላይ በአንድነት መሳተፍ ይኖርበታል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ አባተ በበኩላቸው፤ ስልጠናው ወጣቶች የከተማዋን አልፎም የሀገርን ሰላም ለማረጋገጥ ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው ግንዛቤ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከለውጡ በኋላ በተለዋዋጭ የግጭት ሂደት ውስጥ ያለፈች ቢሆንም፤ መንግሥት የተለያዩ ሪፎርሞችን በማድረግ በተሠሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ያሉት አቶ መለሰ፤ የሀገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥም የወጣቶች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ይህ ስልጠና አስፈልጓል ብለዋል።

መንግሥት ሁሉንም የሃሳብ ልዩነቶች በንግግር ለመፍታትና ዜጎች ሰላም አማራጭ እንዲኖራቸው ለማድረግ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ወጣቱም ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ ለሰላም ዘብ መቆም እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2016

 

 

Recommended For You