ባህላዊ ምግቦችን በሆቴሎች የምግብ ዝርዝር ለማካተት የሚሠራው ሥራ የቱሪዝም ፍሰቱን የሚያሳድግ ነው

አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሚመገቧቸው ባህላዊ ምግቦች በሆቴሎች የምግብ ዝርዝር ውስጥ ተካተው ለአገልግሎት እንዲውሉ እየተሠራ ያለው ሥራ የቱሪዝም ፍሰቱን የሚያሳድግ ነው ሲል የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ስዩም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሚመገቧቸው ባህላዊ ምግቦች በሆቴሎች የምግብ ዝርዝር ተካተው ለአገልግሎት እንዲውሉ እየተሠራ ያለው ሥራ የቱሪዝም ፍሰቱን የሚያሳድግ ነው፡፡

“በሀገሪቱ ከሰማንያ በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ይገኛሉ፤ እያንዳንዳቸው የየራሳቸው የአመጋገብ ሥርዓት አላቸው፤ የአመጋገብ ሥርዓታቸውን የሚገልጹ ባህላዊ ምግቦች አሠራራቸውን በጥናት አስደግፎ በሆቴሎች የምግብ ዝርዝር ውስጥ እንዲካተቱ ለማድረግ እየተሠራ ያለው ሥራ የቱሪዝም ፍሰቱን ይበልጥ እንዲያድግ ያደርገዋል” ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ቱሪስቶች የኢትዮጵያን የተለያዩ ባህላዊ ምግቦች የመጠቀም ፍላጎት እያደገ ነው ያሉት አቶ ይታሰብ፤ የቱሪስቶችን ባህላዊ ምግብ የመጠቀም ፍላጎት አሁን ካለው ይበልጥ ለማሳደግ በሆቴሎች የምግብ ዝርዝር ውስጥ እንዲካተቱ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አንድ ባህላዊ ምግብ ለቱሪስቶች በተዋወቀ ቁጥር፤ ጎብኚዎች ምግቡ የመጣበትን አካባቢ የመጎብኘት ፍላጎት እንዲያሳዩ ያደርጋል ያሉት አቶ ይታሰብ፤ በአካባቢው የቱሪዝም ፍሰት ተፈጠረ ማለት የቱሪዝም ፍሰቱን ይበልጥ ከማሳደግ በተጨማሪ ለሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ እድል ይፈጥራል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ባህላዊ ምግቦችን አሠራርና አዘገጃጀት በሰነድ ሰንዶ በሆቴሎች የምግብ ዝርዝር ውስጥ ለማካተት እየተሠራ ያለው ሥራ በትኩረት እየተሰራበት ቢሆንም፤ ሁሉንም ባህላዊ ምግቦች አጥንቶ በምግብ ዝርዝር ውስጥ ለማስገባት እንዳይቻል የሚያደርግ የበጀት ውስንነት መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

“ዜጎች ያገኙትን ምግብ ብቻ የሚመገቡበት ሳይሆን ለጤናቸው ተስማሚ የሆኑ ምግቦችን መርጠው የሚመገቡበት ጊዜ ላይ ተደርሷል፤ ባህላዊ ምግቦች ለጤንነት ተስማሚና ተመራጭ በመሆናቸው በማህበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ፍላጎት እየታየ ነው” ብለዋል፡፡

በሀገር ውስጥ የሚገኙ ሆቴሎች የምግብ ዝርዝር ውስጥ የህንድና የቻይና ምግቦች ይገኛሉ፤ የሀገሪቱ አንዳንድ ባህላዊ ምግቦች አይገኙም፤ እንዲገኙና ለዓለም እንዲተዋወቁ እየተሠራ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አንዳንድ ሆቴሎች ባህላዊ ምግቦችን በምግብ ዝርዝራቸው ውስጥ እንዲካተቱ የማድረግ ሥራ ሠርተዋል፤ ቀሪዎችም በምግብ ዝርዝራቸው ውስጥ እንዲያካትቱ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የሚታወቁ ባህላዊ ምግቦች ይበልጥ እንዲታወቁ፣ የማይታወቁት ታውቀው ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ከክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ጋር የማጥናትና በሰነድ የመሰነድ ሥራ እየተሠራ ነው፤ ተጠናክሮም ይቀጥላል ሲሉ ም/ዋና ዳይሬክተሩ አመላክተዋል፡፡

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2016

 

Recommended For You