ከሦስት ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች በከንቲባ ችሎት ምላሽ አግኝተዋል

– ችሎቱ ሕዝብና መንግሥትን ለማቀራረብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል

አዲስ አበባ፡- የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ጥያቄ ያላቸው ከሦስት ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች በከንቲባ ችሎት ምላሽ አግኝተዋል ሲሉ የደሴ ከተማ ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ገለጹ። ችሎቱ ሕዝብና መንግሥትን ለማቀራረብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ገልጸዋል።

የደሴ ከተማ ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በከተማዋ የከንቲባ ችሎት ከተጀመረ ጀምሮ በሳምንት ሁለት ቀን ከ94 በላይ መድረኮችን በማካሄድ የሕዝቡን አቤቱታ በተጨባጭ መፍታት ተችሏል።

የተለያየ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ጥያቄ ያላቸው ከሦስት ሺህ በላይ ዜጎች በከንቲባ ችሎት መልስ ማግኘታቸውን ገልጸው፤ ምላሽ ከተሰጣቸው ቅሬታዎች መካከል 80 በመቶ የሚሆነው ከስድስት ዓመታት በላይ ሳይፈቱ የቆዩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በሀሰተኛ መረጃ በፍርድ ቤት ውሳኔ ተሰጥቶባቸው መሬታቸውንና ሕንፃቸውን የተቀሙ ግለሰቦች መረጃውን በማጣራትና ለጸረ ሙስና በማሳየት መልስ እንዲያገኙ መደረጉንም ጨምረው ገልጸዋል።

ችሎቱ የሕዝቡን እንባ በማበስ ሕዝቡን ከመሪው ጋር እንዲቀራረብ ከማድረጉም ባለፈ በከተማዋ ሕገወጥ ደላላና ሌባ እንዳይኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ከንቲባው ገለጻ፤ በሕገወጥ መንገድ መሬትን አስፋፍተው የያዙ ግለሰቦች ላይ የካዳስተር ሥራ በመሥራት ከ17 ሄክታር መሬት በላይ በማስመለስ ወደ መንግሥት መሬት ባንክ ማስገባት ተችሏል። ይህንንም መሬት ለልማት ተነሺዎች ምትክ በመስጠት የልማት ሥራዎችን በቀላሉ ለማከናወን አስችሏል ብለዋል።

በከንቲባ ችሎት የሕዝቡ እርካታና አመኔታ ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ ሳሙኤል፤ አቤቱታቸውን ከማእከል እስከ ቀበሌ ድረስ በተዘረጉት መድረኮች በማቅረብ በተጨባጭ መልስ እያገኙ ነው። በዚህም ደሴን የሰላምና የልማት ከተማ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።

“ከተማዋ ሰላም የሆነችው ሕዝቡ ቀና ትብብር በማድረጉና ሰላም ወዳድ በመሆኑ ነው። የደሴ ከተማ ሕዝቦች ለሰላም ቅድሚያ ሲሰጡ ጥያቄ የሌላቸው ሆኖ አይደለም። ስለ ጦርነት አስከፊነት ጠንቅቀው ስለሚያውቁና ችግሮችን በውይይት መፍታት የተሻለ አማራጭ መሆኑን ስለሚያምኑ ነው” ሲሉም አስታውቀዋል።

ደሴ ከተማ እንደሚወራው አሉባልታ ሳትሆን የልማትና የንግድ ማዕከል እንዲሁም የሰላም አምባሳደርና የልማት አርበኛ ሕዝብ ያለባት መሆኗንም ተናግረዋል።

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመፍታት በተጨማሪም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የኅብረተሰቡን የልማት ጥያቄ የሚፈቱ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑንም አመላክተዋል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You