ከተረጂነት ለመላቀቅ እያንዳንዱ ዜጋ ቢያንስ የአንድ ሙያ ባለቤት ሊሆን ይገባል

አዲስ አበባ፡- በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተረጂነት ለመላቀቅ እያንዳንዱ ዜጋ ቢያንስ የአንድ ሙያ ባለቤት እንዲሆን መንግሥት አቅጣጫ አስቀምጦ እየሠራ መሆኑ ተገለጸ። 14ኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት የፓናል ውይይት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት አካል የሆነው የፓናል ውይይት “ቴክኒክና ሙያ ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ሃሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ትናንት አካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር)፤ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና በባህሪው የተግባር ስልጠና በመሆኑ በሥራ ቦታ መሰጠት እንዳለበትና በኢንዱስትሪ ላይ ያለውን ሥልጠናም ማጠናከር ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የቴክኒክና ሙያ ተቋማትም የሚያመርቱና የሚያሰለጥኑ መሆን አለባቸው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ከዚህ አኳያ አገልግሎትና ሥልጠናን በማስተሳሰር ለዘርፉ ምቹ ሁኔታን የመፍጠር ሥራዎች በመሠራት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ሠልጣኞች ወደ ቴክኒክና ሙያ ሲመጡ ሃሳባቸው ታይቶ ኩባንያ ሆነው ከቴክኒክና ሙያ ሥርዓት ወጥተው እንዲንቀሳቀሱ እየሠራን ነው ብለዋል።

በአዲሱ እሳቤ የመጣው ትልቁ ለውጥ እያንዳንዱ ዜጋ ቢያንስ የአንድ ሙያና ክህሎት ባለቤት መሆን መቻል አለበት የሚል አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራበት እንዳለ አስታውቀዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው፤ “ዜጎች በሚያገኙት ክህሎት ሥራና ገቢ መፍጠር ይችላሉ። እያንዳንዱ ዜጋ ሀብት የሚፈጥር ከሆነ ደግሞ ከተረጂነት መላቀቅ ሩቅ አይሆንም፤ በሚል አግባብ እየሠራን ነው” ብለዋል። በገጠርም ሆነ በከተማ ያሉት የሥራና ክህሎት ተቋማትም ይህንኑ የቤት ሥራ ወስደው ወደ ተግባር እየገቡ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት የአመራርና ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ኃላፊና የዘርፉ ባለሙያ የሆኑት አቶ አበባው ለማ ባቀረቡት ጽሑፍ፤ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ምቹ የሥራ እድልን በመፍጠር የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ትልቅ ድርሻ ያለው መሆኑን አመላክተዋል።

በዚህ መነሻነት ዘርፉ ላይ የሚሰጠው ስልጠና ውጤት ተኮር ሥራን የተከተለና ከገበያና ኢንዱስትሪ ፍላጐት የሚመነጭ ሊሆን እንደሚገባው ገልጸዋል። ለዚህ ደግሞ የግሉ ሴክተርን በስፋት ማሳተፍ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢንዱስትሪና የከተማ መሠረተ ልማት ፖሊሲ ጥናት ማዕከል ኃላፊ አማረ ማህተቡ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ቴክኖሎጂ እንዲያድግ ቴክኒክና ሙያ ላይ ተጨባጭ ሥራዎችን መሥራት ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ቴክኖሎጂ ላይ እንድትደርስ እንደ አውቶሜሽንና መሰል የክህሎት ማበልጸጊያ ሥራዎች ላይ መሥራት እንዳለባትም አሳስበዋል።

ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ አንቶኒዮስ ፍሊቼ፣ “የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ የሚጐለብተው የሰው ኃይል ልማት ላይ ከተሠራ ነው። ሠራተኛን ማልማት ካልተቻለ ኢኮኖሚን ማሰብ አስቸጋሪ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ጀርመን፣ ጃፓን እና የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት በዚህ ረገድ በዘርፉ ያላቸው ተሞክሮ አመርቂ መሆኑና ኢትዮጵያም በተለይ ኢንዱስትሪ ላይ የሚሰጡ ስልጠናዎችን በማዳበር ከቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ላይ የሚገኘውን ጥቅም ልታገኝ ይገባል ነው ያሉት።

በመድረኩ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በቂ ክህሎትና ስብእና ያለውን ባለሙያ ለማፍራት ባለፉት ዓመታት በርካታ ሥራዎች መከናወናቸው፤ የቴክኒክና ሙያ ስትራቴጂ መከለሱም ዘርፉን ብቃት ባለው የሰው ኃይል ማነቃቃት እንዳስቻለ ተገልጿል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You