የመንከባከብ ዘመቻውስ?

አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ከስምንት ዓመታት በፊት ያነበብኩት አንድ የአጀንዳ ርዕስ የችግኝ ተከላ ዘመቻ በተጀመረ ቁጥር ትዝ ይለኛል፡፡ ርዕሱ ‹‹ዘቅዝቃችሁ ትከሉት በሪፖርት ይፀድቃል›› የሚል ነበር፡፡ መልዕክቱ በዘመኑ ክረምት በመጣ ቁጥር የችግኝ ተከላ ዘመቻ ቢደረግም የሚተከለው ችግኝ ክብካቤ አይደረግለትም ለማለት ነው፤ የተተከሉት ችግኞች የሚጸድቁት በውሸት ሪፖርት ነው፡፡ ስለዚህ አሰራሩ የግብር ይውጣ ስለነበር ተዘቅዝቆ ቢተከልም በውሸት ሪፖርት እንደ ጸደቀ ተደርጎ ይነገራል ለማለት ነው፡፡ የአጀንዳው ትኩረት በወቅቱ የነበረው ዓውድ ነው፡፡

ከሰኔ 2011 ዓ.ም ወዲህ ግን ችግኝ ተከላ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ነው፡፡ እነሆ ዘንድሮም ሰባት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ችግኝ እንደተዘጋጀ እና በአንድ ጀንበር 150 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ዕቅድ እንደተያዘ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤሊያስ ባለፈው አርብ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ገልጸዋል፡፡

ችግኝ ተከላው ከሰኔ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ክረምት በመጣ ቁጥር በልዩ ትኩረት እየተሰራበት ነው። በዚሁ ዘመቻ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና አግኝታበታለች፤ አየር ንብረት አያያዝም ምሳሌ ታደርጋለች፡፡

ይህን የዓለም ምሳሌነት ለማስቀጠል ግን አሁንም ያልቀረፍናቸው ችግሮች አሉ፡፡

ዛፍ እየጠፋ በረሃማነት እየተስፋፋ መሬቱ ዛፍ አላበቅል ብሎ ነው? ወይስ የዛፍ ዝርያ ከምድረ ገጽ ጠፍቶ ነው? ይሄ ሁሉ የሆነው በግዴለሽነታችን ነው፡፡

የመንግሥትም ይሁን የግል መስሪያ ቤቶች መጸዳጃ ውስጥ ግቡ፤ አሳፋሪ ነገር ነው የሚታየው፡፡ ውሃውን እንዴት እንደሚደፉት አላውቅም! መጸዳጃ ቤቱ ባህር ይሆናል፡፡ ይሄ አላዋቂነት በብዙ ነገሮች ነው፡፡ ችግሩ ጎልቶ የሚታየው ደግሞ ሀገር ይለውጣል በሚባለው የተማረው ማህበረሰብ ዘንድ መሆኑ ነው፡፡

ይህ የበርካቶቻችን አላዋቂነት፣ አርቆ ማስተዋል አለመቻላችን ለም መሬቶቻችን እንዲራቆቱ አድርጓል፡፡ ብዙ አካባቢዎች በጎርፍ እንዲጠረጉ ምክንያት ሆኗል፡፡

የክረምቱን መግባት ተከትሎ በየዓመቱ የችግኝ ተከላ ዘመቻ የተለመደ ቢሆንም ከ2011 ዓ.ም ወዲህ ያለው ግን የተለየ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ናቸው ያስጀመሩት፡፡ እርሳቸው በተከሉት ችግኝ ብቻ ሀገሪቱ አረንጓዴ በአረንጓዴ ትሆናለች ተብሎ አይደለም፤ መሪ ናቸውና አርዓያ ለመሆን ነው፡፡ ሕዝብ መሪውን ተከትሎ እንዲህ አይነት በጎ ነገሮችን ያደርጋል፡፡ መሪ ማለት እንግዲህ የሚመራ፣ የሚያሳይ ማለት ነው፡፡ እዚህ ጋ ነው አላዋቂነታችን ነጥሮ የሚታየው! በተቃዋሚዎቻቸውም በደጋፊዎቻቸውም በኩል ያለውን እንታዘብ፡፡

ተዋቃሚ ነን በሚሉት በኩል ችግኝ ሲተክሉ የሚያሳየውን ፎቶ ለምስጋና ሳይሆን ለወቀሳ ተጠቅመውታል (ለችግኝ ተከላ ተቃዋሚ የሚል ቃል መጠቀም በራሱ አስቂኝ ነው)፡፡ ‹‹ሀገሪቱ ስንት ችግር እያለባት እሱ ችግኝ ይተክላል›› ተብሏል፤ የሀገሪቱ ምድረ በዳ መሆን ችግር አይደለም ማለት ነው እንግዲህ! የጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግኝ መትከል በምን መመዘኛ ሊያስወቅስ እንደሚችል ግልጽ አይደለም! በዚህ ችግኝ ተከላ ውስጥ ምን አይነት ማጭበርበርና ሕዝብን ማታለል ይኖረዋል ተብሎ ነው? ችግኝ መትከል ምን አይነት ስውር የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ይኖረዋል? ስለተውነው ተዓምር ሆነብን እንጂ ችግኝ መትከል የዕለት ከዕለት ተግባር ነበር፤ ነውም፡፡ ይሄ የሚያሳየው እነዚህን ወገኖች ከመቃወም ውጪ ምክንያታዊ ሃሳብ እንደሌላቸው ነው። ችግኝ መትከል በራሱ የተቀደሰ ሃሳብ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ መቃወም የነበረብን ቆሻሻ የሚጥሉትን እና ችግኝ የሚያበላሹትን ነበር፡፡ ‹‹ቆዳ ፋቂ ሲደክመው ውሻ ያባርራል›› አሉ፡፡ በፖሊሲና ስትራቴጂ መሞገት ነው መቃወም ማለት።

በደጋፊዎቻቸው በኩል ያለውንም እንታዘብ፤ ይሄ እንግዲህ በብዛት የሚታየው በመንግሥት ተቋማት ላይ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ላይ ተቃዋሚዎች ‹‹ማሽቃበጥ›› የሚሉትን ቃል እጋራዋለሁ፡፡ አንዳንዶቹ ነገሩ ገብቷቸውና አምነውበት አይደለም የሚያደርጉት፤ ሲደረግ ስላዩ ብቻ ወይም አድርጉ ስለተባሉ ነው፡፡

በዚያው ዓመት (2011ዓ.ም) በአንድ የመንግሥት ተቋም አማካኝነት ለመስክ ሥራ ከአዲስ አበባ ወጣ ብዬ ነበር፡፡ የወጣንበት ሥራ ሌላ ቢሆንም ችግኝ ተከላ እንደ አንድ ፕሮግራም ተይዟል፡፡ ነገሩን ላሳጥረውና ችግኙ የሚተከልበት ቦታ ስንደርስ እየታዘብንም እየሳቅንም ነበር፡፡ ለችግኝ ተከላ በተዘጋጁ ጉድጓዶች ዙሪያ፤ የጠወለጉ፣ ጭራሹንም የደረቁ፣ የተገነጣጠሉ… የዕፅዋት አይነቶች አሉ፡፡ እነዚህ ዕፅዋት የደረቁትና የተገነጣጠሉት በእርግማን አይደለም፤ እንክብካቤ አጥተው ነው፡፡ እንኳን እንክብካቤ ማድረግ እንዲያውም በተቃራኒው የደረሰባቸው ጥፋት ነው፤ ለዚያውም የእንስሳት ሳይሆን የሰው ጥፋት! እነዚህ ዕፅዋት ጋ ነው ችግኝ የሚተከለው! በወቅቱ ‹‹አሁን የሚተከሉ ችግኞችም ነገ ይደርቃሉ›› እያልን ነበር፡፡

አንዳንድ ሰዎች የመንግሥት ተቋማት ይህን የሚያደርጉት በቀጥታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ታዝዘው ይመስላቸው ይሆናል፤ ግን አይሆንም፡፡ የራሳቸው አስመሳይነት ነው፡፡ ማስመሰል የምንልበት ምክንያት ደግሞ ቀደም ሲል የጠቀስኩት አይነት አተካከል ነው፡፡ ለምን እንደሚተከል፣ የት እንደሚተከል፣ እንዴት እንደሚተከል ካልታወቀበት ማስመሰል ነው፡፡ አልኩ ለማለት ብቻ የሚደረግ ማለት ነው፡፡

የሚተከልበት ቦታ እና ሁኔታ ካልተጠና እኮ ችግኝ መትከል ግዴታ አይደለም፤ ነው እንዴ? አልኩ ለማለት ብቻ ለምን ወጪ ይወጣል? ችግኙ የሚተከለው የሚፈለገውን ጥቅም እንዲያስገኝ ነው፡፡ አውቀን እና አምነንበት ከሆነ የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ነው ማስመስከር! አለበለዚያ አስመሳይነት ነው፡፡

ላለፉት አምስት ዓመታት ትኩረት በተሰጠው የችግኝ ተከላ ላይ በወቅቱ ከተሞች ላይ ብቻ ማተኮር የለበትም የሚል ትዝብት ነበረኝ፡፡ ሁለት ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ግን ወደ ገጠራማ አካባቢዎች መሄድ ችሏል፡፡ አሁን ችግር የሆነው ገጠራማ አካባቢዎች በቂ ግንዛቤ የመስጠት ጉዳይ ነው፡፡ አሁንም በከተሞች ብቻ ሳይሆን ትኩረቱ በገጠራማና ተራራማ አካባቢዎች መሆን አለበት፤ ምክንያቱም በከፍተኛ ሁኔታ የተራቆቱት እነዚያ አካባቢዎች ስለሆኑ፡፡ የመንግሥት አካላት በገጠራማ አካባቢዎች ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል፡፡

ዋናው ትዝብታችን ግን ገጠርም ሆነ ከተማ የሚተከሉ ችግኞች ክብካቤ አይዘንጋ የሚለው ነው፡፡ ችግኝ ለመትከል የሚደረገውን ዘመቻ ያህል የመንከባከቡ ዘመቻም ይታሰብበት፡፡ ለመትከል የሚደረገውን ዘመቻ ያህል ለመንከባከብ ሲደረግ አይታይም፡፡ ብዙዎች መንከባከብ ሲባል ውሃ ማጠጣት ብቻ ይመስላቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ‹‹ደግሞ በክረምት ዝናብ አለ ምን መንከባከብ ያስፈልጋል?›› ሊባል ይችላል፡፡ መንከባከብ ማለት ግን ውሃ ማጠጣት ብቻ ሳይሆን እንስሳትም ሆነ ሰዎች በችግኞች ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ማድረግ ነው፡፡ በበጋ ውሃ ማጠጣት፣ በክረምት ደግሞ ሰዎችና እንስሳት እንዳያበላሹት መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡

ይህንን ስል ከግለሰቦችና እንደ አንዳንድ አካባቢዎች ይዞታ አኳያ ነው፤ እንደ ሀገር ከተመለከትነው መትከልና ማፅደቅ ላይ ከፍተኛ ለውጦችና መሻሻሎች እንዳሉ አጥቼው አይደለምና ዘመቻው ለመትከል ብቻ ሳይሆን ለመንከባከብም ይሁን! እላለሁ።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You