በአገራችን በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ሆነ ተቋማት የተለያዩ ምርምሮች ይደረጋሉ።ሆኖም እነዚህ ምርምር ሥራዎች ከመደርደሪያ ወርደው የሚተገበሩት በጣም ውስን ናቸው።ከፍተኛ ወጪና ጊዜ የፈጁት ምርምሮች ተተግብረው የህብረተሰቡን ችግር ሲፈቱ አይታይም።ይህም በአገሪቱ ዕድገት ሆነ የህብረተሰቡን ህይወት በማሻሻል ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያመጡም አይደለም ሲሉ የሚተቹ ወገኖች አሉ።
ውሃ የሚያነሱ ምርምሮች የሚሰሩት በቡድንና በተናጠል ቢሆኑም አብዛኛዎቹ ምርምሮች ወደ ተግባር የማይተረጎሙት በገንዘብ ችግር ምክንያት መሆኑን ተመራማሪዎች ያነሳሉ።የዲላ ዩኒቨርሲቲ ለዚህ ችግር መላ ዘይጃለሁ ይላል።
ዶ ክ ተ ር ሀ ብ ታ ሙ ተ መ ስ ገ ን በ ዲ ላ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዘርፍ ዳይሬክተር ናቸው። እንደ እሳቸው አገላለጽ ምርምር በዲላ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚካሄድ ተግባር ነው።ምክንያቱም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ናቸው።ዓለም አቀፋዊ ተቋም ከሚያሰኛቸውና ከሚያረጋግጡበት መካከል የምርምር ሥራዎቻቸው አንዱ ነው።
ምክንያቱም ተመራማሪዎች በምርምር ሥራዎቻቸው ችግሮችን መፍታት ከቻሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጆርናሎች ያሳትማሉ።እንዲሁም ዩኒቨርስቲ መምህራን በተመራመሩ ቁጥር ዕውቀታቸው ይጨምራል። ብቃታቸውን ያሳድጉበታል።የተቋማቸውን ተሰሜነትና ዕውቅና የሚያጎለብቱበትም ነው።በዩኒቨርሲቲዎች የውድድርን መንፈስ የሚያነሳሳ ጭምር ይሆናል ሲሉ የምርምር ጠቀሜታ ከአገር አልፎ ዓለም አቀፍ ዝናን የሚያጎናጽፍ ጭምር መሆኑን ያብራራሉ።
ብዙ ጊዜ የምርምር ሥራዎች የተማሪዎች የመመሪቂያ ጹሁፍ እንደ ምርምር ሥራዎች የሚቆጠሩበት ግንዛቤ ይታያል የሚሉት ዶክተሩ፣ እነዚህ የመመረቂያ ጹሁፎች፡ የተማሪዎቹን ብቃት ለመመዘን ነው የምንጠቀምበት እንጂ ወደ ተግባር የሚተረጎም አድርጎ መመልከት አይገባም።ምክንያቱ በእነዚህ ጽሁፎች የሚደረጉት ምርምሮች አብዛኛዎቹ በተለያዩ ውስንነቶች ጥልቀት የሌላቸውና አንድን ጉዳይ በተለያዩ አቅጣጫዎች ማየት የማይችሉ ናቸው።ዲላ ዩኒቨርሲቲ ግን ከተመራቂ ተማሪዎች ከሚጽፏቸው ውጭ መምህራንና በከፍተኛ ደረጃ ያሉ ተማሪዎችን በማወዳደር በቡድን በማደራጀት የምርምር ሥራዎችን ማካሄድ መጀመሩን ነግረውናል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ በየዓመቱ በጀቱ በአንጻራዊ በሆነ መልኩ እያደገ መጥቷል።ተማሪዎች ከዚህ የምርምር በጀት እየተጠቀሙ የምርምር ሥራቸውን እየሰሩ ይገኛሉ።አሁንም ቢሆን የሚቀሩ ነገሮች የሉም ባይባልም በምርምር ዘርፍ ረገድ ብዙ ነገሮች እየተሻሻሉ መጥተዋል። በተለይ የምርምር ፍኖተ ካርታው መሰረት በማድረግ የተለያዩ መመሪያዎችን በማዘጋጀት የምርምር ሥራን ግልጽ የማድረግ ሥራ ተሰርቷል።በዚህ መመሪያ መነሻ መሰረት ከቁጥ ቁጥ ምርምር ይልቅ የተደራጀ ምርምር እንዲካሄድ የሚያደርግ የምርምር ፖሊሲ ተዘጋጅቷል ይላሉ።
የተናጠል ምርምር ጥልቀት ስለማይኖረው ለመተግበርና የምርምር ሥራውንም በተቋም ደረጃ ለመምራት አስቸጋሪ ነው።ውስብስብ የሆነ የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት አቅምም አይኖረውም።ውስን በሆነ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን በመሆኑ የማህበረሰቡንና የኢንዱስትሪ ችግሮች ለመፍታት አቅም ያጥረዋል።ስለዚህ ይህን ውጤታማ ያልሆነ የአሰራር ስርዓት ቀስ በቀስ ወደ ተቀናጀ ምርምር ማደግ አለበት የሚል ሀሳብ አላቸው።
በዩኒቨርሲቲያቸውም ከተናጠል ምርምር ሥራዎች በመተው ወደ ውስብስብ ችግሮችን በተለያዩ አቅጣጫዎች ቃኝቶ የተለያዩ ተመራማሪዎች በአንድ ቡድን አሳትፎ የሚሰራበት አሰራር እየተሸጋገረ መሆኑን አውስተዋል።ይህ አይነት አሰራር አንድም ለማስተዳደር ቀላል ነው።ምርምሩን በቀላሉ መቆጣጠርና መከታተል ይቻላል።ሁለተኛ በቡድን የሚደረግ በመሆኑ ልምድ የሌለው ተመራማሪ ልምድ ካለው እውቀትና ክህሎት እንዲቀስም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።ሶስተኛ ውስብስብ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት የተሻለ አማራጭ ይሰጣል።ከበጀትም አኳያ ወጪ ቆጣቢ ነው።
ዩኒቨርሲቲዎች ከመንግሥት የሚያገኙት ሀብት ውስን ነው።ይህም ሀብት በአግባቡ ለመጠቀምም የተቀናጀ ምርምር ተመራጭ ነው ብለዋል።ሌላው የመጻፍ ልምድ ያላቸው ተመራማሪዎች ትላልቅ ምርምሮችን በተጨባጭ መረጃና ግልጽ በሆነ መልኩ ስለሚያቀርቡ በብርም ሆነ በእውቀት የሚደግፉ ተቋማትን በማፈላለግ ምርምር ሥራው ወደ ተግባር እንዲለወጥ ይረዳል ሲሉ የተቀናጀ ምርምር በወጪ ቁጠባ፣ በተቀባይነትና ውስብስብ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው ።ስለዚህ በተደራጀና በቡድን ወደ ሚካሄዱ ምርምሮች እየተሸጋገር ነው ያሉት፡
ዩኒቨርሲቲው በተያዘው ዓመት በአንገብጋቢ አጀንዳዎች ላይ ያተኮሩ ሰባት የሚሆኑ የቡድን ምርምሮችን አሰርቷል። ምርምሮቹም የማህበረሰቡን ችግርና የመንግሥትን ክፍተት ላይ ያተኮሩ ናቸው።እነዚህ ወደ ተግባር ሲተረጎሙ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ተጨባጭ ውጤት ያስገኛሉ።ሌላው በዩኒቨርሲቲ -ኢንዱስትሪ ትስስር ማዕቀፍ ውስጥ የኢንዱስትሪ ችግሮችን የሚፈቱ ምርምሮች እየተካሄዱ ይገኛል ።
ለአብነትም ዩኒቨርሲቲው በተቀናጀ ምርምር አማካኝነት በሲዳማ፣በጊዴዮ፣በቦረና በጉጂ ዞኖች አካባቢዎች ላይ ያተኮረ የምርምር ሥራዎችን እየሰራ ነው።ከዚህ በተመሳሳይ የተሰሩ የምርምር ሥራዎችን ለማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች የሚተገበሩ መኖራቸውን አንስተዋል ። እንዲሁም ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የሚደረጉ የምርምር ሥራዎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።በተፋሰስ ልማት ዙሪያ ከጊዳቡ ግድብ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው የተፋሰስ ልማት ላይ ያተኮረ የምርምር ሥራ ወደ ተግባር ተለውጠዋል።ከዲላ ዩኒቨርሲቲ በስተምዕራብ የሚገኝ የተራቆተ መሬት ማገገሚያ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሆኖ ተጨባጭ ለውጥ ተገኝቷል።ግድቡ በደለል እንዳይሞላ የሚያደርጉ ሥራዎች ተሰርተዋል።
ምርምሮች ችግር ፈች እንዲሆኑ ለማድረግ በቂ አቅምና በጀት ሊኖር ይገባል።በምርምሩ ዘርፍ የተሻሉና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ሊኖሩ ይገባል።ሆኖም ዩኒቨርሲቲዎች ገና አቅማቸውን በመገንባት ሂደት ላይ በመሆናቸው የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ምርምሮች እየተካሄዱ ነው ማለት አያስደፍርም የሚሉት ዶክተር ሀብታሙ፣ ችግሩን ለመፍታት ሁለንተናዊ ጥረትና ስልታዊ አሰራር መከተል ይኖርባቸዋል ሲሉ ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚ ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶክተር ዳዊት ሀይሶ የምርምር ሥራዎች ወደ መሬት ወርደው የሚጨበጥ ውጤት አምጥተዋል ለማለት አይቻልም። ሆኖም በዩኒቨርሲቲያቸው በተማሪዎችና በመምህራን የምርምር ሥራዎች የሚካሄዱ መሆኑን ይጠቅሳሉ።እነዚህ የምርምር ሥራዎችን ወደ መሬት ለማውረድ ግን የፋይናንስና የምርምሮቹ ሥራዎች ውስንነት የሚታይባቸው መሆኑን አልሸሸጉም።
ስለዚህ በየትኛውም ተቋማት የሚካሄዱ የምርምር ሥራዎች ተተግብረው የህብረተሰቡን ችግር መፍታት አለባቸው።ይህን ለማድረግ ደግሞ የተመረጡ ጉዳዮችና የተቀናጁ ጥልቀት ያላቸው ምርምሮች መካሄድ ይጠበቅባቸዋል።ለዚህ ነው ዩኒቨርሲቲው በውስን ሀብት የተመረጡ ምርምሮችን በተቀናጀና በቡድን እንዲካሄድ የሚያደርገው። በዚህም ጅምር ሥራ ቢሆንም ወደ መሬት በማውረድ ረገድ ጥሩ ለውጦች መታየታቸውን ነው የሚናገሩት።
በኢትዮጵያ ብዙ ምርምሮች የሚደረጉ ቢሆንም ወደ ህብረተሰቡ ወርደው ተጨባጭ ለውጥ ሲያመጡ አልታየም።ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ ብዙ ገንዘብ የወጣባቸውና ወደ ተግባር የተተረጎሙት የጎንዮሽ ጎዳት በማስከተላቸው ህብረተሰቡ እርም ይቅርብኝ ያላቸውም አሉ።ስለዚህ ውስን የአገር ሀብትን በምርምር ሥራዎች በማዋል ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት እንደ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በተወሰኑ ርዕሰ ጉዳዮችና በቡድን የተደራጁ ማድረግ ወጪ ቆጣቢና ለውጤታማነታቸው ጉልህ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
ስለዚህ ዩኒቨርሲቲዎች የቁጥር ጋጋታን ትተው ማህበረሰባችን ከችግር የሚያላቅቅና የተሻለ ህይወት እንዲመራ የሚያደርጉ ውጤታማ ምርምሮች በተቀናጀና በቡድን ቢ ያ ደ ር ጉ ተ መ ራ ጭ ይ ሆ ና ል ። አ ገ ሪ ቱ ከፍተኛ ወጪ አውጥታ የምታስተምራቸው ተመራማሪዎች ገንዘብ ለመሰብሰብ ሳይሆን የአርሶ አደሩን፣የነጋዴውን፤የኢንዱስትሪ ባለቤቶችን ህይወት፣ንግድና ምርታማነት የሚያሳድጉ ምርምሮችን ማድረግ ሞራላዊ ሀላፊነት አለባቸው።ለዚህ ተግባራዊነት ደግሞ በቁርጠኝነትና በሃላፊነት መንፈስ ሊሰሩ ይገባል። ምክንያቱም ይች አገር ከዜጎቿ ቆንጥራ በምታገኘው ሀብት ነው የተማራችሁት።
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2011
ጌትነት ምህረቴ