ነፍሰ ገዳዩ ደፋሪ

“በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሴቶችና ልጃገረዶች የአስገድዶ መድፈር ሰለባ ሆነው ሳሉ ስለዚህ እውነት ዝም ማለት እንዴት እንችላለን?” የሚል ጥያቄ በውስጤ ይመላለሳል። በተለይ የዘንድሮው የ 16 ቀናቱ ዘመቻ መሪ ቃል “ዓለምን ብርቱካናማ እናድርግ፤ በእኩልነት የሚያምን ትውልድ አስገድዶ መድፈርን ይጠየፋል” የሚል ሲሆን በመሪ ቃሉ እንደሰፈረው ከሠብዓዊነት ውጪ የሆነውንና ሴቶች ላይ አካላዊ፣ ሥነልቦናዊ ጉዳትና የማይሽር ጠባሳ የሚያስከትለው አስገድዶ መድፈር መገታት እንዳለበት ሊታመን ይገባል።

በአብዛኛው ሴቶቹ ጥቃት የሚደርስባቸው በሚያምኗቸው ሰዎች መሆኑ ችግሩን አስከፊ ያደርገዋል። ጥቃት ከደረሰም በኋላ በቤተሰቦች በኩል ከማኅበረሰቡ መገለልን በመፍራት፣ በተጠቂዎች በኩል ደፋሪዎች በአብዛኛው የሚያምኗቸው የቤተሰብ አባላት፣ ጎረቤቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና የህክምና ባለሙያዎች በመሆናቸው ብናገር ሰው አያምነኝም በሚል ለቤተሰቦቻቸው ሳይቀር ሳይናገሩ መቅረታቸው፣ አንድም በአጥቂዎች ማስፈራሪያና ዛቻ ስለሚደርስባቸው በቀልን ፍራቻ ዝምታን መምረጣቸው ሪፖርት ለሚደረጉት ጥቃቶች ቁጥር ማነስ አስተዋጽኦ አድርጓል።

በየእለቱ በተለያየ መልኩ ይህ ጥቃት ቢፈፀምም ተመልክቶ ዝም ከማለት ያለፈ ጥቃትን ቀጥ የሚያደርግ ርምጃ አለመወሰዱ ጉዳዩን አስከፊ አደርጎታል። ስለ ጥቃት በዚህ ልክ ላነሳ የወደድኩት ከአዲስ አበባ ፖሊስ መዝገብ ያገኘሁትን እጅግ አሰቃቂ የሆነ ጥቃት ላካፍላችሁ ስለሆነ ነው። ሰው ሠብዓዊነቱን አጥቶ በደካማ በተለይም ራሷን መከላከል የማትችል አካል ጉዳተኛ ላይ ይህን ያህል ጭካኔ ለማሳደር መድፈሩ እጀግ በጣም ያሳዝናል።

ገና በአፍላ እድሜዋ ማየት የተሳናት ልጅ ለቤተሰብ ሸክም እንደሆነች እየታሰበች በማደጓ ከልክ በላይ የተከፋች ልጅ ነበረች። በእድገቷ ብዙም እንክብካቤ ያልተደረገላት ከመሆኗም ባሻገር ጠባቂ አጥታ ለተለያዩ ጥቃቶች የተዳረገች ልጅ ነበረች። ወጣቷ በተደጋጋሚ በደረሰባት ጥቃት ምክንያት የወንድ ድምፅ ስትሰማ የምትበረግግ አሳዛኝ ፍጥረት ነበረች።

ምስኪኗ ልጅ

የዛሬ ባለታሪካችን መቀጫ የሻነው ትባላለች። መቀጫ ማየት የተሰናት ወጣት ናት። መኖር ግራ የገባት ቤተሰቦቿ እንደማይፈልጓት የምታሰብ ወጣት ነበረች። ዓይኖቿ ቁልጭ ብለው ቁጭ ቁጭ ከማለታቸው የተነሳ ማየት የተሳናት አትመስልም ነበር። ጠይም የቆዳዋ ቀለም፤ እንደ በረዶ የነጡት ጥርሶቿ፤ ከርደድ ብሎ ጀርባዋ ላይ የወደቀው ጥቁር ፀጉሯ፤ ሁለ መነዋ ቆንጆ የመትባል ለጅ ነበረች። ዓይኖቿ ባለማየታቸው የተነሳ የትምህርት ቤት ደጅን ባትረግጥም ሰዎች የሚያወሩትን ማዳመጥ፤ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ መከታተል የዘወትር ተግባሯ በመሆኑ አእምሮዋ ብሩህ ነበር።

ነገሮችን በቀላሉ የምትረዳ ልጅ ከመሆኗመ በላይ በቻለችው አቅም ሰዎችን ለማስደሰት የምትጥር ተለማማጭ ልጅ ነበረች። በተሰቦቿ በርካታ ልጆች ያላቸው በኢኮኖሚ አቅማቸው ደከም ያሉ ስለነበሩ ብዙም አያስታውሷትም ነበር። ባገኘችው አጋጣሚ ለመታየት ለመስማት ብትፈልግም ነገሬ ያላት ሰውም አልነበረም።

ይህችን ዓይነ ስውር ወጣት ነው እንግዲህ መኖሪያ ቤቷ በመግባት አፏን በጨርቅ ጠቅጥቆ፣ አንገቷን አንቆ በመያዝ የግብረ-ስጋ ግንኙነት በመፈፀም ሕይወቷ እንዲያልፍ ያደረገው ።

“በመጀመሪያ የቤታችንን ውስጥ ሰው ሲገባ እቃ ለመስረቅ የመጣ ሌባ ነበር የመሰለኝ። ከዛ ግን በጭካኔ ሲደፍረኝ ልጅነቴን ሊሰርቅ የመጣ ሌባ መሆኑን አወቅሁ። ከመደፈሬ በላይ ያመመኝ ግን ማየት አለመቻሌን ተገን አድርጎ ማንነቱን እንዳላውቅ ድምጹን ቀይሮ ለአንድ ሰው ብትናገሪ እገድልሻለው ማለቱ ነው።” የምትለው ምስኪን ለሁለተኛ ጊዜ የተፈፀመባት አስገድዶ የመድፈር ወንጀል ግን እስከወዲያኛው እንድታሸለብ አድርጓታል።

ቀድሞ በገጠማት መደፈር ከባድ የሥነልቦና ጉዳት የገጠማት ይህች ልጅ ቁስሏን ለማከም እየጣረች ባለችበት ሰዓት ሌላ ቁስል ተጨመረላት። የሚገርመው ከዚህ ቀደም የተደፈረችው በበተሰቧ እንደሆነ እንደታስብ ያደረጋትን ገጠመኝ ስትናገር “መድፈሩ ሳያንስ ይባስ ብሎም በዚህ እንኳን አገልግይ እንጂ አለኝ። ያኔ ለቤተሰቦቼ የማልጠቅም ሸክም የሆንኩ ስለመሰለኝ በከባድ የበታችነትና የመገፋት ስሜት ውስጥ ነው ያለሁት” ትል እነደነበረ የሚቀርቧት ሰዎች ይናገራሉ።

መጀመሪያ ገና በአስራ አንደ ዓመቷ ከተደፈረች በኋላ ወንድ ሲነካት እጀግ በጣም ትፈራ ነበር። አንድ ጊዜ አሟት ሀኪም ቤት ሄዳ ዶክተሩ ለምርመራ ቲሸርቴን ከፍ ሲያደርገው ተንቀጥቅጣ እንደነበረ አብረዋት የነበሩት በትዝታ ያወራሉ። ቁስሏ ሙሉ በሙሉ አልዳነም ነበርና እግር ከወርች ያሰራት ስጋት ሲያሰቃያት ቆይቷል። የጠሉት ይወርሳል ፤ የፈሩት ይደርሳል የሚሉት ነገር ደርሶባት ነው መሰለኝ፤ አሁን ባላሰበችው አጋጣሚ ሕይወቷን ከፍላለች።

ገና በጠዋቱ የእድሜ መጀመሪያ ላይ እሷ እንደምታሰበው በቅርብ ሰው ተደፍራ ፍዷዋን ስትበላ የቆየችው ልጅ ይባስ ብሎ ብቻዋን በተቀመጠችበት ቤት ማንነቱ ያልታወቀ ግለሰብ ገብቶ ሕይወቷን አጠፋው።

ሞገስ ደሳለኝ

ሞገስ ያደገበት ቤት ለሴት ልጅ ክብር የማይሰጥ ሴት ልጅን እንደተናቀች አድርጎ የሚያስብ ማህበረሰብ ውስጥ ነበር። እሱ እንደሚያስበው የሴት እንቢታ መግደርደር እንጂ አለመፈለግ ነው ብሎ አያስብም ነበር።

“ወንዶች ስሜታቸውን መቆጣጠር አይችሉም”፣ ሴት ልጅ እንቢ ስትልህ መግደርደር ነው” “መጠጥ ጠጥታ ነበር፣ ማን ስከሪ አላት” የሚሉ አስገድዶ መድፈርን እንደ ቀላል እና የተለመደ ነገር የሚቆጥሩ አባባሎች ሲሰማ ያደገው ወጣት ሴትን ልጅ እንደፈለገ የማድረግ መብት ያለው መሆኑን ያስባል። ማኅበረሰቡ ወንድነትን ከሃይለኛነት፣ የፈለጉትን ከማድረግ፣ ከቁጣ እና ከጉልበተኛነት ያዛመደበት የ “ወንድነት” ትርጉምም በደፋሪነት አስተሳሰብ ውስጥ ከቶ እንደልቡ እያደረገ እንዲቆይ አድርጎታል ።

ከዚህ በፊት በፈፀማቸው ጥቃቶች ሳይያዝ ቆይቷል። በሕግ አስፈፃሚዎች እና በህክምና ባለሙያዎች ሳይቀር ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶችና ልጆች በአግባቡ ባለማስተናገዳቸው የተነሳ ተጠቂዎችም የሕግ ድጋፍ ሳያገኙ እሱም በቁጥጥር ስር ሳይውል ቆይቷል።

በአሁኑ ግን ድምፁን አጥፍቶ መኖሪያዋ ቤት ገብቶ አለማየቷን በመጠቀም ሊደፍራት የሞከረው ወጣት ያላሰበው ተከሰቶበታል። ወጣቱ እንደለመደው አድብቶ ከሟች መኖሪያ ቤት በመግባት አፏን በጨርቅ ጠቅጥቆ፣ አንገቷን አንቆ በመያዝ የግብረ-ስጋ ግንኙነት ሲፈፅምባት በመታፈናና በመታነቋ የተነሷ ሕይወቷ ሊያልፍ ችሏል።

ሕይወቷ ማለፉን የተረዳው ልማደኛ ደፋሪ በድንጋጤ ሲደነባበር ነበር ወደ መኖሪያ ቤቱ ከመጡ የጎረቤት ሰው ጋር የተገናኙት። ቤት ወስጥ የተገኘው ሰው ሁኔታው ያላማራቸው ሰው ግራ የተጋባውን ጎረምሳ ጮኸው በአካባቢው ሰዎች በማሲያዝ ወደ መኖሪያ ቤቱ ሲመለከቱ ዓይነ ስውሯ ወጣት እርቃኗን ተዘርግታ ይመለከታሉ። ያኔ ፖሊስ ተጠርቶ በቁጥጥር ስር እንዲውል አደረጉት።

የፖሊስ ምርመራ

ፖሊስ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ የጀርባ ታሪኩን ማጥናት ጀመረ። መሬት ላይ ወድቃ ያገኛትን ወጣት አንስቶ ሆስፒታል ቢያደርሳትም በሕይወት ሊያቆያት አልቻለም። ወጣቷ በአሳዛኝ ሁኔታ ሕይወቷ ማለፉን ከተረዳ በኋላ የተለያዩ ምርመራዎችን ማድረግ ጀመረ።

ወጣቷ በመታፈኗ ምከንያት ህይወቷ ከማለፉም በተጨማሪ ተገዳ መደፈራንም የሚያመለክት ምርመራ ወጤት ተገኘ። የምርመራ ውጤቱን የያዘው ፖሊስ የዓይን እማኝ ባለማግኘቱ የተነሳ ከተጠርጣሪው የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ወደ ማረሚያ ቤት ተመለሰ።

በምርመራ ክፍሉ ውስጥ የተፋጠጡት ፖሊስና ተጠርጣሪው አተካራ ገጥመዋል። ተጠርጣሪው ምንም አላደረኩም ቢሊም ፖሊስ የአንተ ዐሻራና የዘር ፍሬ በሰውነቷ ላይ ተገኝተዋል፤ ብታምን ይሻላል በሚል ብዙ ከተከራከሩ በኋላ ነበር የእምነት ክህደት ቃሉን የሰጠው።

ከዚህ በፊት በርካታ ሴቶችን እንዲህ ማደረጉን ማስረጃም ስላልተገኘበት ሳይከሰስ መቅረቱን ፖሊስ በምርመራው አገኘ። ይህን የለመደ ወንጀለኛ በአግባቡ ቅጣቱን ያገኝ ዘንድ በቂ ምርመራ በማድረግ ማስረጃውን አጠናቅሮ በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ቀረበ።

የአቃቤ ህግ ክስ ዝርዝር

ጉዳዩ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ተጣርቶ በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወ/ሕ/አ/620/2/ሀ/ እና /3/ መሠረት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 11ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡

በአቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር እንደቀረበው ሞገስ ደሳለኝ የተባለ ተከሳሽ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ከጠዋቱ በግምት 1፡30 ሲሆን በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ሽሮ ሜዳ አዲስ ተስፋ ትምህርት ቤት አካባቢ የ 14 ዓመት የሆነችውን የግል ተበዳይ የምትኖርበት መኖሪያ ቤት በመግባት በጥፊ በመምታት፣ እንዳትጮህ አፏ ውስጥ ጨርቅ በመጠቅጠቅ እና አንገቷን በሁለት እጁ አንቆ በመያዝ በኃይል የግብረ-ስጋ ግንኙነት የፈጸመባትና አፏ ውስጥ ጨርቅ በመጠቅጠቁ እና አንገቷን በማነቁ ምክንያት ትንፋሽ አጥሯት ሕይወቷ እንዲያልፍ በማድረጉ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ተመልክቷል።

በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ተጣርቶ በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወ/ሕ/አ/620/2/ሀ/ እና /3/ መሰረት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 11ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡

በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ የመከላከያ ምስክሮችን ያሰማ ቢሆንም የቀረበበትን ክስ ሊከላከል ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ ሰጥቷል።

ውሳኔ

ተከሳሹ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 11ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ የቆየ ሲሆን በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ የመከላከያ ምስክሮችን ያሰማ ቢሆንም የቀረበበትን ክስ ሊከላከል ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት በ19 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2016 ዓ.ም

Recommended For You