ደም የፈሳሽ እና የተለያዩ የፕሮቲን እና ሴሎች ቅልቅል ነው። ቀይ የደም ሴሎች ኦክስጅን ተሸክመው ወደ ተገቢው የሰውነት አካል የሚያደርሱ ሲሆን ነጭ የደም ሴሎች በሽታ ይከላከላሉ። ፕላትሌት የሚባሉ ትናንሽ የሴል አካሎች ሰውነታችን ላይ ጉዳት ሲፈጠር ደምን በማርጋት ቁስልን ይሸፍናሉ።
እንደ ሉኪሚያ፣ ሊምፎማ እና ማይሎማ የተባሉ አንዳንድ የካንሰር አይነቶች እነዚህን ሴሎች የሚያመርቱ አካላትን ያጠቃሉ። በ2016 ዓ.ም 171,000 ሰዎች በደም ካንሰር ተይዘዋል።
ለበሽታው ማን ተጋላጭ ነው?
የደም ካንሰር መንስኤ ምን እንደሆነ በቅጡ የሚታወቅ ነገር የለም። ለበሽታው ተጋላጭ የሚያደርጉን አንዳንድ ነገሮች ግን ይታወቃሉ። በሽታው በቤተሰብ የዘር ግንድ ላይ ተከስቶ ካወቀ፣ እንደ ቤንዚን አይነት ኬሚካሎች ጋር ለረጅም ጊዜ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች እና ከፍተኛ የራዲዬሽን ጨረር ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች በበሽታው የመያዝ እድላቸው ሰፊ ነው። አንዳንድ ጊዜ ኤች.አይ.ቪ ወይም ኤድስ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ።
ሊምፎማ
ሰውነት በውስጡ ሊምፋቲክ ሲስተም የሚባል መረብ አለው። ይህ ሲስተም ኢንፌክሽን ሲያጋጥመን በመዋጋት ይረዳል። ሊምፋቲክ ሲስተም ሊምፍ ኖድ የተባሉ በሰውነታችን ባክቴሪያ እና ቫይረስ የሚያጣሩ አካላቶችን እንዲሁም ነጭ የደም ሴሎችን ያካትታል። ይህን ሲስተም የሚያጠቃ የካንሰር አይነት ሊምፎማ ይባላል። ከደም ካንሰር አይነቶች ሁሉ በቀዳሚነት የሚከሰተው የካንሰር አይነት ይህ ነው። የሊምፋቲክ ሲስተም መረብ ሙሉ የሰውነታችንን አካል ስለሚያካልል ይህ
የካንሰር አይነት በየትኛውም የሰውነት ክፍል ሊከሰት ይችላል።
የሊምፎማ አይነቶች
ሁለት አይነት የሊምፎማ አይነቶች አሉ። ሆጅኪንስ እና ነን-ሆጅኪንስ። ሁለቱም በተመሳሳይ ሁኔታ ነው የሚከሰቱት። በተለመደው መልኩ የማይሰሩ ሊምፎሳይቶችን ሰውነታችን ማመንጨት ይጀምራል። ከዛም እነዚህ ሊምፎሳይቶች ተሰብስበው ክምር በመፍጠር ወደ እጢነት ይቀየራሉ። ጤነኛ የነጭ ደም ሴሎችን በማጨናነቅ በሽታ የመከላከል አቅም ያዳክማሉ።
ሆጅኪንስ ሊምፎማ
የሁለቱ የሊምፎማ አይነቶች በሚመረተው የሊምፎሳይት አይነት ይለያያሉ። ሆጅኪንስ ሊምፎማ ሲሆን ሰውነታችን ሪድ ስተርንበርግ የሚባሉ ሴሎችን ያመርታል። ስያሜአቸውን ያገኙት ካገኛቸው ሰው ስም ነው። ሊምፎማ ካለባቸው ሰዎች ውስጥ 12 በመቶው ይህ የሊምፎማ አይነት አለባቸው። ከሁሉም የካንሰር አይነቶች ለመድሃኒት ተገዢ የሆነው የካንሰር አይነት ይህ ነው።
ነን–ሆጅኪንስ ሊምፎማ
የሚመረቱት ሴሎች አይነታቸው የሪድ- ስተርንበርግ ካልሆነ የካንሰሩ አይነት ነን- ሆጅኪንስ ሊምፎማ ይባላል። ከሁሉም የሊምፎማ አይነቶች በቀዳሚነት የሚከሰተው ይህ አይነት ነው። 30 አይነት የካንሰር አይነቶች በዚህ የካንሰር አይነት ስር ይጠቃለላሉ። አንዳንድ የካንሰር አይነቶች እድገታቸው ለዘብተኛ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በፍጥነት ተንሰራፍተው ሌላ የሰውነት ክፍል ማጥቃት ይጀምራሉ። እነዚህ የካንሰር አይነቶች በፍጥነት ህክምና ያስፈልጋቸዋል። ለማጥፋትም ከባድ ናቸው።
የሊምፎማ ምልክቶች
በተደጋጋሚ የሚታዩት ምልክቶች የሊምፍ ኖዶች ማበጥ፣ ትኩሳት፣ ምክንያት የሌለው ክብደት መቀነስ እና የድካም ስሜት ናቸው። የሚከተሉት ምልክቶችም ሊታዩ ይችላሉ።
• ምሽት ላይ የሚከሰት የሰውነት ላብ
• ማሳል
• ደረት ወይም ሆድ ላይ ህመም
• የረሃብ ስሜት መጥፋት
• የጉበት ወይም ጣፊያ እብጠት
ምርመራ የሚያካሂደው ዶክተር ሊምፎማን ከጠረጠረ ከአንዱ ሊምፍ ኖድ ሳምፕል መውሰድ ይፈልጋል። ከተወሰድው ሳምፕል ካንሰር መፈጠሩን፣ ከተፈጠረም አይነቱን ማወቅ ይችላል።
ሉኪሚያ
ይህ የካንሰር አይነት ደምን ወይም የአጥንት መቅኔ (አጥንት ውስጥ ያለ የደም ሴሎች የሚመረቱበት ለስላሳ አካል) የሚያጠቃ የካንሰር አይነት ነው። ልክ እንደ ሊምፎማ ሰውነታችን በትክክል የማይሰሩ የነጭ ደም ሴሎች እንዲያመርት በማድረግ ጤነኞቹ ነጭ ደም ሴሎች በሽታ እንዳይከላከሉ ያደርጋል። በተጨማሪም ሉኪሚያ የአጥንት መቅኔ በአግባቡ ቀይ የደም ሴሎችን እና ፕላትሌቶችን እንዳያመርት ይዳርጋል። በልጆች ላይ አብዝቶ የሚከሰት የካንሰር አይነት ቢሆንም ትልልቅ ሰዎችንም ሊያጠቃ ይችላል።
የሉኪሚያ ምልክቶች
ይህ የደም ካንሰር አይነት በምልክቶቹ ምክንያት ከጉንፋን ጋር ይምታታል። ትኩሳት፣ የድካም ስሜት፣ ላብ እና መገጣጠሚያ ላይ የሚከሰት ህመም ያመጣል። የሚከተሉት ምልክቶችም አብረው ሊታዩ ይችላሉ።
• ያበጡ ሊምፍ ኖዶች
• ያለ ምክንያት ክብደት መቀነስ
• የድድ መድማት ወይም ማበጥ
አዘውትሮ በኢንፌክሽን መያዝ፣ በቀላሉ መቁሰል እና የደም ማነስ ሌሎች ምልክቶቹ ናቸው።
ሉኪሚያ መፈጠሩን እንዴት ይታወቃል
ዶክተር የደም ምርመራ በማድረግ የነጭ ደም ሴሎች ከተገቢው መጠን በላይ ወይም ቀይ ደም ሴሎች እና ፕላትሌቶች ከተገቢው መጠን በታች መሆናቸውን በማስተዋል ሉኪሚያ መፈጠሩን መመርመር ይጀምራል። ከአጥንት መቅኒ ውስጥ ትንሽ ሳምፕል በመውሰድ የካንሰር ሴሎች እንደሚገኙ ይመረመራል።
ማይሎማ
ይህ የደም ካንሰር አይነት ፕላዝማ ሴል ተብለው የሚታወቁ የነጭ ደም ሴሎችን ያጠቃል። ፕላዝማ ሴሎች ባክቴሪያ እና ቫይረስ የሚያጠቁ አንቲቦዲ የሚባሉ ፕሮቲኖችን ያመርታሉ። ማይሎማ ካለብዎ ሰውነትዎ ስራቸውን በተገቢ ሁኔታ የማይሰሩ ፕላዝማ ሴሎችን በከፍተኛ ደረጃ ያመርታል። እነዚህ ፕሮቲኖች በአጥነት መቅኒ ውስጥ በመከማቸት ኩላሊት ላይ ጉዳት ሊፈጥሩ ይችላሉ። አጥንትንም ሊያዳክሙ ይችላሉ።
የማይሎማ ምልክቶች እና ምርመራ
የማይሎማ ምልክቶችን በጊዜ ማየት ሊጀምሩ ይችላሉ። ብዙ ጊዜ የመጀመሪያው ምልክት የአጥንት ህመም ሲሆን በተለምዶ የጀርባ እና የደረት አጥንቶች ይጠቃሉ። የድካም ስሜት፣ አዘውትሮ የሚከሰት ኢንፌክሽን፣ ጥማት፣ የሽንት መፈራረቅ፣ የሆድ ድርቀት እና የእጅ እና እግር መደንዘዝ የህመሙ ምልክቶች ናቸው። ዶክተሩ ማይሎማን ከጠረጠረ የደም ምርመራ እና የአጥንት መቅኒ ምርመራ ያካሂዳል። አጥንት ላይ ጉዳት መፈጠሩንም ይመረምራል።
ህክምና፡ ራዲዬሽን እና ኪሞቴራፒ
ለደም ካንሰር የተለመደው ህክምና ኪሞቴራፒ ወይም ራዲዬሽን ወይንም የሁለቱ ቅልቅል ነው። ኪሞቴራፒ ከባድ ኬሚካሎችን በመጠቀም የካንሰር ሴሎችን ለመግደል የሚሞከርበት ህክምና ሲሆን የራዲዬሽን (ጨረር) ህክምና ከባድ ሃይል ያያዙ ጨረሮችን በመጠቀም የካንሰር ሴሎችን ለመግደል ይሞክራል። ነገር ግን እነዚህ ህክምናዎች ጤነኛ ሴሎችን አብረው ስለሚገድሉ የጸጉር መነቃቀል እና የማቅለሽለሽ ስሜት አብረው ይፈጥራሉ።
ህክምና፡ ስቴም ሴል ትራንስፕላንት
ሌሎች ህክምናዎች ካልሰሩ ወይም ዶክተሩ ካንሰሩ ተመልሶ ይመጣል ብሎ ካሰበ ይህንን የህክምና አይነት ሊመክር ይችላል። ስቴም ሴሎች ወደ ማንኛውም የሴል አይነት ሊቀየሩ ይችላሉ። ሃሳቡ ችግር ያለባቸውን ሴሎች በጤነኛ ስቴም ሴሎች ለመተካት መሞከር ነው። በኪሞቴራፒ እና ሬዲዮቴራፒ ህመምተኛ ሴሎቹ እየተገደሉ በስቴም ሴል ዝውውር አዲስ ጤነኛ ሴሎች የምንቀበልበት ህክምና ነው።
ወደፊት
የደም ካንሰርን የምናሸንፍበትን እድል የምንጨምርባቸው ህክምናዎች ላይ ምርምር እየተደረገ ነው።
ምንጭ፡– ጤነኛ ድረ ገፅ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 15/2011