‹‹ጠላታችን መሃይምነት ነው›› የሚለው ቃል በደማቁ ተጽፎ በዋና ዋና አደባባዮችና ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ሁሉ መሰቀል አለበት(ለዚያውም እኮ የሚያነበው ከተገኘ ነው) የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከዜና በፊት የሚያሳዩት መሪ ቃል መሆን አለበት፤ የሬዲዮ ጣቢያዎች ከዜና በፊት የሚናገሩት መሆን አለበት ጋዜጦችና መጽሔቶች የፊት ገጻቸው ላይ በደማቁ ሊያስቀምጡት ይገባል ይህ የሚሆነው በኢትዮጵያ ነው ።
የብዙ ችግሮቻችን ምክንያት መሃይምነት ነው ኢትዮጵያ ከየትኛውም ዓለም ያላነሰ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት፣ የተስማሚ አየር ንብረት ባለቤት፤ እንደሆነች ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ የሚነገረን ነው ይህን መታደል ይዛ ግን በዓለም በድህነት ከሚጠሩ አገራት ጋር ትዘረዘራለች። (ኧረ እንዲያውም በቀዳሚነት) ምክንያት? መሃይምነት! እስኪ በቀላሉ ፅዳት እና ችግኝ ተከላን እንመልከት! (የወቅቱ አጀንዳዎች ስለሆኑ ነው)
የከተሞቻችን ወንዞች አፍንጫ ተይዞ የሚታለፍባቸው በተፈጥሮ የቆሸሸ ውሃ እያመነጩ ነው? በየመንገዱ ዳርና ዳር ጭንቅላት የሚያዞር ሽታ ያለው ቆሻሻ ከሰማይ የወረደ ነው? እንዴት እንደሚቆሽሹ ምንም ጥናትና ማብራሪያ አያስፈልገውም።
ዛፍ እየጠፋ በረሃማነት የተስፋፋው መሬቱ ዛፍ አላበቅል ብሎ ነው? ወይስ የዛፍ ዝርያ ከምድረ ገጽ ጠፍቶ ? ይሄ ሁሉ የሆነው በመሃይምነታችን ነው መሃይምነት ሲባል ፊደል አለመቁጠር እንዳልሆነ ማንም ያውቃል፤ ኧረ እንዲያውም አጉል ፊደል ቆጠርኩ ያለ መሃይም ነው አገር እያጠፋ ያለ! ፊደል ያልቆጠሩት እንዳውም ‹‹እንዲህ አታድርጉ›› ከተባሉ ይፈራሉ ሁለት ማሳያዎች ልጠቀም።
የመንግሥትም ይሁን የግል መስሪያ ቤት መጸዳጃ ውስጥ ግቡ፤ አሳፋሪ ነገር ነው የሚታየው ውሃውን እንዴት እንደሚደፉት አላውቅም! መጸዳጃ ቤቱ ባህር ይሆናል እንዲያውም ‹‹ሲንኩ›› የሚያፈስ መስሎኝ ሥራዬ ብዬ ያየሁበት አጋጣሚ አለ ምንም የማያፈስ ‹‹ሲንክ›› ሆኖ ዙሪያውን በውሃ ይጥለቀለቃል፤ ይህ የሆነው እንግዲህ ዝም ብሎ ከበሩ ላይ ሆኖ የሚደፋ መሃይም በመኖሩ ነው ይሄ ጥሬ መሃይም እንግዲህ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ በዲግሪ የተቀጠረ ነው ውሃ ሳይደፉ መሄድማ የተለመደ ሆኗል።
በአንድ ወቅት ደግሞ ያልተማሩ የሚባሉ ሰዎችን ያመሰገንኩበትን አጋጣሚ ልንገራችሁ ለአንድ የመስክ ሥራ ወደ ክልል እየሄድኩ ነው በዚህ ዕለት እንደ ሌላው ጊዜ ከጋዜጠኞችና ከሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች ጋር ሳይሆን በህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ነበር የምሄደው ከጋዜጠኞችና የመንግሥት ሠራተኞች ጋር ከአንዴም ሁለቴ ሄጄበት ስለነበር ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ አውቀዋለሁ እናም ያንን ሰዓት ነበር እየጠበቅኩ ያለሁት ሁኔታውን ሳየው ግን ቶሎ የምደርስ ሆነ፤ እንደገመትኩትም መንገዱ በእጥፍ ቀንሶ ደረስኩ ምክንያቱ እንዲህ ነበር
በውስጡ የነበሩ ሰዎች አብዛኞቹ የገጠር ሰዎችና እኛ ‹‹ያልተማሩ›› የምንላቸው ናቸው። (ያልተማርንስ እኛ) ለቁርስም ሆነ ለምሳ የሚጠቀሙት ሾፌሩ የፈቀደውን ደቂቃ ብቻ ነው አየር ለመውሰድ ቆሞ ከሆነ ወዲያውኑ ይገባሉ።
ይሄን ነገር የተማሩ የሚባሉ ሰዎች ከሚያደርጉት ጋር አነጻጸርኩት ልዩነቱ ሰማይና ምድር ነው ምናልባት የተማሩት የሚሄዱት ለመስክ ሥራ ስለሆነ ረጋ ቢሉም ችግር የለውም ትሉኝ ይሆናል፤ አያሳምነኝም
የምንሄድበት ቦታ ርቀቱ እየታወቀ፣ ሰዓት እላፊ እንደምንገባ እየታወቀ፣ በዚህ በመዝረክረክ ምክንያት ያላሰብንበት ቦታ እንድናድር እያስገደደ፤ ይሄ ነው ታዲያ ረጋ ማለት? ሁሉም ሰው ገብቶ መነሳት ከጀመረ በኋላ ትቶት የቆየውን ዕቃ ተመልሶ ሊገዛ ወይም ምግብ ሊያዝ የሚሄድ አለ፤ ታዲያ ይሄ መሃይምነት አይደለም?
ወደ ጽዳትና ችግኝ ተከላ እንመለስ!
የክረምቱን መግባት ተከትሎ በየዓመቱ የችግኝ ተከላ ወሬ ይወራል(ለእኔ ወሬ ነው) ከችግኝ ተከላ ወሬዎች ሁሉ ግን የ2000 ዓ.ም(ሚሊኒየም) እና የዘንድሮው ይለያል የሚሊኒያሙ ያው ሚሊኒየም ስለሆነ ነው የዘንድሮው ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለውጥ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህን የተቀደሰ ሃሳብ ለማጠናከርና አርዓያ ለመሆን በብዙ ቦታዎች ችግኝ ሲተክሉ አይተናል እርሳቸው በተከሉት ችግኝ ብቻ አገሪቱ አረንጓዴ በአረንጓዴ ትሆናለች ተብሎ አይደለም፤ መሪ ናቸውና አርዓያ ለመሆን ነው ህዝብ መሪውን ተከትሎ እንዲህ ዓይነት በጎ ነገሮችን ያደርጋል መሪ ማለት እንግዲህ የሚመራ፣ የሚያሳይ ማለት ነው መሪው ይህን ሲያደርጉ እኛ ግን መሃይምነታችን ነጥሮ ታይቷል።
በተቃዋሚዎቻቸውም በደጋፊዎቻውም በኩል ያለውን እንየው
«ተዋቃሚ» ነን በሚሉት በኩል ችግኝ ሲተክሉ የሚያሳየውን ፎቶ ለምስጋና ሳይሆን ለወቀሳ ተጠቅመውታል። (ለችግኝ ተከላ ተቃዋሚ የሚል ቃል መጠቀም በራሱ አሳፋሪ ነው እኮ) ‹‹አገሪቱ ስንት ችግር እያለባት እሱ ችግኝ ይተክላል›› ተብሏል፤ የአገሪቱ ምድረበዳ መሆን ችግር አይደለም ማለት ነው። እንግዲህ! የጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግኝ መትከል በምን መመዘኛ ሊያስወቅስ እንደሚችል አይገባኝም።
በዚህ ችግኝ ተከላ ውስጥ ምን ዓይነት ማጭበርበርና ህዝብን ማታለል ይኖር ይሆን? ችግኝ መትከል ምን ዓይነት ስውር የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ይሆን? እንዲያው ስለተውነው ተዓምር ሆነብን እንጂ ችግኝ መትከል የዕለት ከዕለት ተግባር ነው ይሄ የሚያሳየው እነዚህ ወገኖች ከመቃወም ውጪ ምክንያታዊ ሃሳብ እንደሌላቸው ነው፤ ችግኝ መትከል በራሱ የተቀደሰ ሃሳብ ነው ከዚህ ይልቅ መቃወም የነበረብን ቆሻሻ የሚጥሉትን እና ችግኝ የሚያበላሹትን ነበር(ቆዳ ፋቂ ሲደክመው ውሻ ያባርራል አሉ)
በደጋፊዎቻቸው በኩል ያለውን እንይ፤ ይሄ እንግዲህ በብዛት የሚታየው በመንግሥት ተቋማት ላይ ነው እነዚህ ወገኖች ላይ ተቃዋሚዎች ‹‹ማሽቃበጥ›› የሚሉትን ቃል እጋራዋለሁ አንዳንዶቹ ነገሩ ገብቷቸውና አምነውበት አይደለም የሚያደርጉት፤ ሲደረግ ስላዩ ብቻ ወይም አድርጉ ስለተባሉ ነው።
ሰሞኑን በአንድ የመንግሥት ተቋም አማካኝነት ለመስክ ሥራ ከአዲስ አበባ ወጣ ብዬ ነበር የወጣንበት ሥራ ሌላ ቢሆንም ችግኝ ተከላ እንደ አንድ መርሐግብር ተይዟል ነገሩን ላሳጥረውና ችግኙ የሚተከልበት ቦታ ስንደርስ እየታዘብንም እየሳቅንም ነበር ለችግኝ ተከላ በተዘጋጁ ጉድጓዶች ዙሪያ፤ የጠወለጉ፣ ጭራሹንም የደረቁ፣ የተገነጣጠሉ… የዕፅዋት ዓይነቶች አሉ እነዚህ ዕፅዋት የደረቁትና የተገነጣጠሉት በእርግማን አይደለም፤ እንክብካቤ አጥተው እንጂ እንኳን እንክብካቤ ማድረግ እንዲያውም በተቃራኒው የደረሰባቸው ጥፋት ነው፤ ለዚያውም የእንስሳት ሳይሆን የሰው ጥፋት! እነዚህ ዕፅዋት አካባቢ ነው ችግኝ የሚተከለው! ከዚህ ተነስቶ አሁን የሚተከሉ ችግኞችም ነገ እንደሚደርቁ እርግጠኛ መሆን ይቻላል።
በዚያው በጨዋታችን ውስጥ ችግኞች በውድ ዋጋ እንደሚገዙ ሰማሁ።(እንዴት እንደሚመጡ አላውቅም ነበር) እንግዲህ ይሄ በየክፍለ ከተማውና በየወረዳው የሚደረገው የችግኝ ተከላ ዘመቻ ወጪ ወጥቶበታል ማለት ነው።
አንዳንድ ሰዎች የመንግስት ተቋማት ይህን የሚያደርጉ በቀጥታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ታዝዘው ነው ሲሉ ይሰማል፤ ግን አይሆንም የራሳቸው አስመሳይነት ነው ማስመሰል የምንልበት ምክንያት ደግሞ ቀደም ሲል የጠቀስኩት ዓይነት አተካከል ነው ለምን እንደሚተከል፣ የት እንደሚተከል፣ እንዴት እንደሚተከል ካልታወቀበት ማስመሰል ነው ተከልኩ ለማለት ብቻ የሚደረግ የሚተከልበት ቦታ እና ሁኔታ ካልተጠና እኮ ችግኝ መትከል ግዴታ አይደለም አይደል? አልኩ ለማለት ብቻ ለምን ወጪ ይወጣል? አውቀውትና አስበውት ቢሆን ኖሮ ምነው እስከዛሬ በዘመቻ አልተከሉም ነበር? የዛፍ ጥቅም ዘንድሮ ነው በጥናት የተረጋገጠው? አውቀን እና አምነንበት ከሆነ የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ነው ማስመስከር! እነዚህ ተቋማት የተከሏቸውን ችግኞች ከጎበኙና ከተንከባከቡ ደጋግሜ ለማመስገን ቃል እገባለሁ!
ከላይ እስከታች እንዲህ ነን እንግዲህ! አንዱ ያጸዳል፤ ሌላው ያቆሽሻል! አንዱ ችግኝ ይተክላል ሌላው ይነቅላል! ነገራችን ሁሉ የተበለሻሸው እንዲህ ተካይ እና ነቃይ ሆነን ነው!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22/2011
ዋለልኝ አየለ