የተሻሻሉ የእንስሳት ዝሪያዎችን ማባዣ ማዕከላት በስፋት መገንባት ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፦ በኢትዮጵያ በወተትና በስጋ እንዲሁም በሌሎችም በቂ ምርት እንዲገኝ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝሪያዎችን ማባዣ ማእከላት በስፋት ሊኖሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

በኢንስቲትዩቱ የእንስሳት ምርምር ዳይሬክተር ፈቀደ ፈይሳ (ዶ/ር) ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ በተለይም በወተት፣ በስጋ፣ በእንቁላልና በሌሎችም በቂ ምርት ለማግኘት እንዲቻል የተሻሻሉ የእንስሳት ዝሪያዎችን በማባዛት ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሚያደርጉ ማዕከላት በስፋት ሊቋቋሙ ይገባል፡፡

በደርግ መንግሥት ወቅት የእንስሳት ማባዣ ማእከላት የነበሩ ቢሆንም የመንግሥት ለውጥ መምጣቱን ተከትሎ ወደግሉ ዘርፍ እንዲዞሩ ተደርጓል ያሉት ፈቀደ ዶ/ር ፤ የግሉ ዘርፍ ደግሞ የብዜት ማዕከላቱን ወደሌላ አገልግሎት እንደቀየሯቸው አስታውሰዋል።

እንደ ፈቀደ ዶ/ር ከሆነ፤ በተለይም በወተት ምርት ውጤታማ ለመሆን የተሻሻሉ የእንስሳት ዝሪያዎችን በማባዛት ተደራሽ የሚያደርግ በቂ ማዕከል የለም፡፡

በተወሰኑ አርሶ አደሮች እጅ በቀን እስከ 45 ሊትር ወተት የሚሰጡ በቁጥር ውስን የሆኑ ላሞች መኖራቸውን ጠቁመው፤ እነዚህን አባዝቶ ተደራሽ ማድረግ ቢቻል ኢትዮጵያ በወተት ምርት በቀላሉ እራሷን እንድትችል ሲሉ ተናግረዋል።

እንስሳት የተሻለ ውጤት እንዲሰጡ የሚያስችል በቂ የመኖ አቅርቦት እንደሌለ አንስተው፤ በመኖ እጥረትና በሌሎችም ምክንያቶች የሀገረ ሰብ የወተት ላሞች በቀን በአማካይ አንድ ነጥብ አምስት ሊትር ይሰጣሉ፤ ይህንን ለማሳደግ በወተት ተዋጾአቸው ከታወቁ ዝሪያዎች ጋር ማዳቀል አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ወተት ምርት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች በስፋት የሉም፤ ነገር ግን የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በብዛት ያሉ ቢሆንም ጥራት ያለው ወተት በበቂ ሁኔታ የማያገኙ በመሆኑ የሚሠሩት ከአቅማቸው በታች ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ባለሀብቱ ከዚሁ ጎን ለጎን የእንስሳት ርባታው ላይ መሳተፍ እንዳለበት ዶክተር ፈቀደ አስገንዝበዋል፡፡

በዶሮ ብዜት ላይ የተወሰኑ ማዕከላት ቢኖሩም በተለይም በመንግሥት ስር ያሉት በተለያዩ ችግሮች መሥራት በሚገባቸው ደረጃ እየሠሩ እንዳልሆነ ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ የሀገር ውስጥ ዶሮች በዓመት ከ60 የማይበልጥ እንቁላል እንደሚጥሉና በምርምር እስከ 260 እንቁላል መጣል የሚችሉ መኖራቸው አንስተዋል። እነዚህን በስፋት ተደራሽ ማድረግ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።

እንደ ፈቀደ ዶ/ር ገለጻ፤ መንግሥት በእንስሳት ዘርፍ ላይ ትኩረት በማድረግ ባለሀብቶችን በማሳተፍ ኢንቨስትመንት የሚስፋፋበትን ምቹ ሁኔታ ማስፋት አለበት። የዘርፉ ኢንቨስትመንት በዋናነት ያለው በዘመናዊ ቄራዎች ላይ ቢሆንም ቄራውን መመገብ የሚያስችል ጥራት ያላቸው እንስሳት አስፈላጊ መሆናቸው የማያጠያይቅ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

መንግሥትም ይሁን የግሉ ዘርፍ ሁሉም በቅድሚያ ማምረት ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ምርት ላይ ወይም ግብዓት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሥራት ከተቻለ የተሻለ ውጤት እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You