በመዲናዋ 1 ሺህ 239 የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች እየተገነቡ ነው

አዲስ አበባ፡- በመዲናዋ አንድ ሺህ 239 ሁሉን አቀፍ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች እየተገነቡ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ። በተጨማሪ 113 ስብዕና መገንቢያ የወጣት ማዕከላት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አንድ ሺህ 239 ሁሉን አቀፍ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች እየተገነቡ መሆኑን ጠቁመው ወጣቱ በስፋት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን አለበት።

ሁሉን አቀፍ የስፖርት መዘውተሪያዎቹ ወጣቶች ከአልባሌ ሱሶች ተላቀው ጊዜያቸውን በተለያዩ መዝናኛዎችና የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች እንዲያሳልፉ የሚረዱ በመሆናቸው ወጣቶች በአግባቡ ሊጠቀሙባቸው እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተጨማሪ በከተማዋ በተደረገ ጥናት በመዲናዋ ከሚገኙ 113 ወጣት ስብዕና መገንቢያ ማእከላት እንደሚገኙ አስታውቀው፤ ከነዚህ ውስጥ 29 ማዕከላት ከታለመላቸው ዓላማ ውጪ የተለያዩ አገልግሎት ሲሰጡ በመገኘታቸው ችግሩን ለመቅረፍ የማስተካከያ ርምጃ እየተወሰደ ይገኛል ብለዋል።

አቶ በላይ እንደተናገሩት፤ የወጣት ስብዕና መገንቢያ ማዕከላት ወጣቶች በአካልና በአእምሮ እንዲዳብሩ፣ የተሟላ ሰብዕና እንዲኖራቸውና የራሳቸውን ሥራ እንደፈጥሩ ከማድረግ አኳያ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡

የወጣት ስብዕና መገንቢያ ማዕከላትን ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ በማስቻል መልካም ስብዕና የተላበሰ ዜጋ ለማፍራትና ወጣቱን ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

ማዕከላቱ በውስጣቸው የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት፣ የመዝናኛና የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የምክር አገልግሎት፣ የሥነ ተዋልዶ ጤና ትምህርት፣ የመረጃ ማዕከል እንዲሁም የሥልጠና አገልግሎት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

በመዲናዋ አሁን ላይ በሁሉም ክፍለ ከተማ የወጣት ማዕከላት እንደሚገኙ ገልጸው፤ ወጣቶች በተለያዩ ሥልጠናዎች እራሳቸውን በማብቃት ይኖርባቸዋል፤ ለዚህም የወጣቱን ሰብዕና ለመገንባት የሚረዳ ወቅቱን የሚመጥን የወጣት ማዕከላትን በዘላቂነት መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

በቀጣይ በተለያዩ ዘርፎች የወጣቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ብሎም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሠራም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ወጣቱ ጽዱ፣ ማራኪና ሳቢ የሆኑ ቦታዎችን ይፈልጋል ያሉት ኃላፊው፤ የጥራት ችግር ያለባቸውን ማዕከላት ማደስና ማራኪ የማድረግ ሥራ ተጀምሯል ሲሉ አስረድተዋል።

የተወሰኑ ማዕከላት በበቂ ቁሳቁስ ካለመደራጀታቸው የተነሳ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ አይደሉም ያሉ አቶ በላይ በቀጣይ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ሥራ ለመሥራት መታቀዱን አመላክተዋል።

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You