በክልሉ በዘጠኝ ወራት ከ26 ሚሊዮን ኩንታል በላይ አትክልትና ፍራፍሬ ተመርቷል

– በአረንጓዴ ዐሻራ ቡናንና ፍራፍሬን ጨምሮ 372 ሚሊዮን ችግኝ ይተከላል

አዲስ አበባ፡- በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ26 ሚሊዮን ኩንታል በላይ አትክልትና ፍራፍሬ ምክር መገኘቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡ በክልሉ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ቡናንና ፍራፍሬን ጨምሮ 372 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዷል።

የክልሉ የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ በግብርና ልማት በመስኖ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በበልግ እርሻ እንዲሁም በመኸር ዝግጅት አበረታች አፈጻጸም ተመዝግቧል፡፡

በመስኖ ልማት ስራ ከታቀደው በላይ 132 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን ጠቅሰው፤ በመስኖ ልማት በዘጠኝ ወራት ከ26 ሚሊዮን ኩንታል በላይ አትክልትና ፍራፍሬ ምርት መገኘቱን አስታውቀዋል። ምርቱ ገበያውን በማረጋጋት ትልቅ ሚና እንደነበረው ጠቅሰዋል፡፡

በሌማት ትሩፋት ከሁለት ሺህ 500 በላይ መንደሮችን ማደራጀት መቻሉን የተናገሩት አቶ ኃይለማሪያም፤ በዘጠኝ ወራት ከሁለት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን በላይ የዶሮ ጫጩቶችን የማሰራጨት ሥራዎች መሠራታቸውን አመልክተዋል፡፡ በተጨማሪም ከ382 ቶን በላይ የወተት ምርትም ማሰባሰብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ 752 ሺህ ሄክታር መሬት በመኸር ለማልማት ቅድመ ዝግጅት መጀመሩን የተናገሩት ኃላፊው፤ ከዚህም 52 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

በመኸር ወቅት በክልሉ በአብዛኛው ፍራፍሬ፣ እንሰት፣ እንዲሁም የድንች ምርት በብዛት ለማምረት መታቀዱን ጠቅሰዋል፡፡ ሰብሎቹ በሄክታር እስከ 350 ኪሎ ግራም የሚገኝባቸው ሰብሎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የሌማት ትሩፋት ግቦችን ለማሳካት የተጀመሩ ሥራዎችን በማስፋፋት የወተት ሀብት ልማት ላይ ዝርያ የማሻሻል ሥራና የዶሮ ሀብት ልማት ላይ በቂ ግብዓት የማቅረብ ሥራዎች እንድሚከናወኑ ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪ ሰፋፊ የንብ ርባታ ማዕከላትን በማደራጀትና ቀፎዎችን በማሰራጨት ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ሥራዎች የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።

በአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ቡናንና ፍራፍሬን ጨምሮ 372 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል መታቀዱን ገልጸው፤ የቡናና የፍራፍሬ ችግኞች ተከላ ቀደም ብሎ መጠናቀቁን ገልጸዋል። ሌሎች ችግኞች በሀገር አቀፍ ደረጃ የአረንጓዴ ዐሻራ በሚጀመርበት ወቅት እንደሚተከሉ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የበጀት ዓመቱ ሲጀመር የተቀመጡ ዋና ዋና ግቦች እንደነበሩ ያስታወሱት ኃላፊው፤ በቀጣይ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You