በኢትዮጵያ ሰፊ የቱሪስት መዳረሻና መስህብ ቦታዎች የሚገኙ በመሆኑ ከቱሪዝም መስክ ሊገኝ የሚችለው ጠቀሜታ ግልጽ ነው። ሆኖም በየዓመቱ የጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም የቱሪዝም ዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ጥቅም እያስገኘ አለመሆኑ ይነገራል። በመሆኑም አገሪቷ ያላትን ያልተነካ የቱሪዝም ሀብት ትጠቀምበት ዘንድ፣ ይህንን ሀብት በመጠቀምም በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገቢ ታስገባ ዘንድ እየታዩ ያሉትን ክፍተቶች በፍጥነት ትኩረት በመስጠት መቅረፍ እንደሚገባ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው እንደሚናገሩት፤ ቱሪዝም ጠንካራ የሆነ የኢኮኖሚ ምንጭ ነው። የሥራ ዕድልን ይፈጥራል። የውጭ ምንዛሬን ያስገኛል። አማራጭ የታክስ ማስገኛ ሆኖ ያገለግላል። የቱሪዝም ገበያ የሚያመለክተው ደንበኞች ሰፊ የሆነ የጉዞ የእንግድት መስተንግዶ የሚጠይቁበት ዘርፍ መሆኑን ነው። ይህንን መስተንግዶ ለማግኘት ከፍተኛ ገንዘብ ያፈሳሉ። አገሮችም ከዚህ ገንዘብ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ቀላል የማይባል ገቢንም ለአገራቸው ያስገኛሉ። በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ወገኖች ዓለም አቀፍ ትብብር ያደርጋሉ። መረጃን ይለዋወጣሉ። በጋራ ሠርተው በጋራ ያተርፋሉ።
በአንድ ወቅት አይደረስባቸውም ከዓለም የራቁ ናቸው የሚባሉ ሥፍራዎች አሁን የዓለም ህዝብ ትኩረት ያገኙ ሆነዋል የሚሉት ሚኒስትሯ፤ አገሮች ከመቼውም በላይ በኢኮኖሚ የተሳሰሩ መሆናቸውን፤ መልከዓምድራዊ፣ ባህላዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ የሆኑ ጉዳዮች አገሮች እርስ በእርስ እንዳይገናኙ እንዳላገዷቸውና፤ በርካታ የዓለም ህዝብ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የህዝቦችን ማንነት እንዲያጠና፣ ቀደምት ሥልጣኔን እንዲያደንቅ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል። ትቬት በአንድ ወቅት ከዓለም እጅግ ሩቅ ስፍራ ተደርጎ ይቆጠር እንደነበርና አዲሱ የቻይና የባቡር መንገድ ከተከፈተ በኋላ ቁጥሩ ቀላል የማይባል በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ሂማሊያን የሚጎበኝ ስፍራ መሆን እንደቻለም ታሪክ ጠቅሰው ያስገነዝባሉ።
እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ የ13 ወራ ጸጋ የታደለች አገር፣ የብዝኃ ባህል፣ ብዝኃ ቋንቋ አገር፣ ድንቅና ውብ የሆኑ የተፈጥሮ መስህብ ያሏት አገር ሆና ሳለ ከቱሪዝም መጠቀም የሚገባትን ያህል አልተጠቀመችም። በዘመናችን ጠንካራና ቀጣይነት ያለው የቱሪዝም ዕድገት ተመዝግቧል። ከውጭ ወደ አገሪቷ የሚገቡ ቱሪስቶች ቁጥር ጨምሯል። በዓለማችንም ሆነ በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው እጅግ ፈጣን በሆነ መልኩ እያደገ ሳለ በአገሪቷ ኢኮኖሚ መጫወት የሚገባውን ሚና ግን እየተወጣ አይደለም።
ሚኒስትሯ ‹‹እንደ አገር የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማዘመን የሆቴሎችን ቁጥር ለማብዛት በዓለም ላይ ተወዳዳሪና ገበያ የሚስቡ እንዲሆኑ ብዙ ሥራዎች ይጠበቃሉ። ገበያ የማጥናት፣ የአድቮኬሲ ሥራ ከሚሠሩ አካላት ጋር በትብብር የመሥራት የሆቴል ኢንዱስትሪዎችን አዳዲሶችን የመገንባት የተገነቡትን የማስፋፋትና ደረጃቸውን የመጠበቅ ብሎም የማሳደግ ሥራ ያስፈልጋል። በዚህ መሠረት በጥንቃቄ ከተሠራ የማህበረሰቡን ህይወት ትርጉም ባለው መንገድ በመቀየሩ ረገድ ከቱሪዝም የሚጠበቀው ብዙ ነው። ቱሪዝም ፈርጀ ብዙ በመሆኑ። ኮንፈረንስ ቱሪዝም፣ ሆቴል ቱሪዝም፣ ስፖርት ቱሪዝም፣ ፓርኪንግ ቱሪዝምና ገበያ ቱሪዝም የመሳሰሉት ሀብቶች ላይ በስፋትና በትጋት መሥራት ይጠበቃል። የቱሪስት መዳረሻዎችን የመለየት፣ የማልማት፣ ሎጅ የመሥራት፣ የማደራጀት፣ ለጎብኚዎች ክፍት የማድረግ፣ የማስተዋወቅና ተዛማጅ ሥራችን መከናውን ቀጣይ የቤት ሥራ ነው›› ይላሉ አመላካች የመፍትሔ አቅጣጫን በመጠቆም የዘርፉን ቀሪ የቤት ሥራዎችን በመጥቀስ።
በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂና ቱሪዝም ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ ተክለብርሃን ለገሠ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቁ የቱሪዝም ጥቅም የሚገኘው በቱሪስት ብዛትና በጉብኝት የቆይታ ጊዜ ነው። በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አገሪቷ ካላት እምቅ ሀብት አንጻር ሲታይ ሁለቱም ጥቂት በሚባል ደረጃ ላይ ነው። በኢትዮጵያ የውጭ ጎብኚዎች በአማካኝ ለ16 ቀን ነው ቆይታ የሚያደርጉት። ይህ እንደ አገር የሚታየው ችግር በሁሉም መዳረሻ አካባቢዎች ነው። በመሆኑም አሁን በአገሪቱ ያለውን ሀብት ከግምት ያስገባ የቱሪስት ቆይታ ጊዜን ማራዘም ይገባል ይላሉ የአክሱምና አካባቢዋን ጅምር ልምድ እንደማሳያ በማንሳት።
አቶ ተክለብርሃን እንደሚናገሩት፤በተለይ በአክሱም አካባቢ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች ቢኖሩም የማስተዋወቅ ሥራዎች በአግባቡ አልተከናወኑም። እንደ አገር ያለውን ችግር ለመፍታት ጭምር በአክሱምና አካባቢዋ ያሉትንና እስከአሁን ያልታወቁትን የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች በማስተዋወቅ የቱሪስቱን የጉብኝት የቆይታ ጊዜ ከፍ ለማድረግ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ እየሠራ ይገኛል። በአብዛኛው የትግራይ ክልል በሚገኙ የነባርና የአዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት ተሞክሮዎችን እንዲሁም በልማቱ ዙሪያ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች፣ መልካም አጋጣሚዎች እና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማሳየት የሞክሩ ጥናቶችም እየተደረጉ ይገኛሉ።
‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ በቅርስነት ተመዝግቦ ካለው የአክሱም ሀውልት በተጨማሪ ሌሎች የመዳረሻ ስፍራዎች በብዛት ቢገኙም በቱሪስቶች የመጎብኘት ዕድል የላቸውም። በመሆኑም ቱሪስቶች የአክሱምን ሀውልት ለመጎብኘት የሁለት ቀናት ብቻ የጊዜ ቆይታ ይኖራቸዋል። ይህ የጉብኝት ጊዜ ቆይታ ማነስ ደግሞ ከቱሪዝም በሚገኘው ገቢ ላይ ተጽእኖ ያሳድራል። በአካባቢው ያለው ሀብት ከሁለት ቀናት በላይ የሚያስጎበኝ በመሆኑ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመውሰድ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ማስፋት በሚያስችል ሁኔታ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ሌሎች የመዳረሻ ስፍራዎችን በማስተዋወቅ የቱሪስት የጉብኝት የቆይታ ጊዜን ከሁለት ቀናት በአማካኝ ወደ አምስት ቀናት ለማሳደግ ከክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር እየሠራ ነው›› ብለዋል አቶ ተክለብርሃን።
ቱሪስቶችን እስከ አምስት ቀን ድረስ ማቆየት የሚቻለው የቱሪዝም መስህብ አገልግሎት ላይ ከዋለ የአገርን ገጽታ ይበልጥ ለማስተዋወቅም ሆነ ኢኮኖሚውን ለማሳለጥ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ የሌሎች ባለ ድርሻ አካላት እገዛ ታክሎበት ልምዱን ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ማስፋፋት እንደሚቻል ጠቁመዋል።
የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ምክትል የቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ዘነቡ ሓለፎም፤ እንደ አገር የቱሪዝም ዘርፉ በአግባቡ ጥቅም እየሰጠ አይደለም ብቻ ሳይሆን ትኩረትም አልተሰጠውም። ተረስቶ የነበረና አሁን ላይ በተነጻጻሪነት በጥቂቱም ቢሆን እየተሠራበት ይገኛል። ሴክተሩ በኤጀንሲ ይመራ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በቢሮ ደረጃ እስከ ወረዳ ድረስ መዋቅር ተሠርቶለት ራሱን ችሎ እንዲንቀሳቀስ እየተደረገ መሆኑ ማሳያ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለሴክተሩ በቂ ነው ባይባልም በበጀት የመደጎም ሥራውም ዘርፉን እንዲበረታታ ያደርገዋል።
እንደ ወይዘሮ ዘነቡ ማብራሪያ፤ የሴክተሩን ውጤታማነትና ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ሊኖረው የሚችለውን አስተዋጽኦ የሴክተሩ አስፈላጊነት ለፖሊሲ አውጪዎች ማሳየት አልተቻለም። ይህ መሆን ካልቻለ ወደ ፊትም ትኩረት ሊነፈገው ይችላል። በመሆኑም ሴክተሩን በሁሉም ደረጃ በአቅም የማደረጃት ጉዳይ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል። ሴክተሩን በጥናትና ምርምር የመደገፍ ሥራም መዘንጋት የለበትም። ሥራዎች በግምት መከናወን የለባቸውም። በዘርፉ የሚያጋጥሙ ማነቆዎች በጥናትና ምርምር እየተፈቱ ከመጡ ቱሪዝም ለኢትዮጵያ ትልቅ የኢኮኖሚ ምንጩ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል።
ከግብርናው የማይተናነስ ሀብት እያለ የቱሪዝም ዘርፉን የኢኮኖሚ ሴክተር ነው ብሎ አመኔታ አለመጣል ዘርፉን ካዳከሙት ምክንያቶች ውስጥ ተጠቃሹ ነው። ለቱሪዝም ግብዓት መሆን የሚችሉ በርካታ የተፈጥሮና የታሪክ ብዝኃ ሀብቶች መኖራቸው ሥራውን ለማስፋት ምቹ ነው። ያሉትን የቅርብ ዕድሎች ወደ ጥቅም አለመቀየር በአመራር ደረጃ ሴክተሩን በሚገባው ደረጃ ካለመረዳት የሚመነጭ ነው። ቱሪዝም የጎንዮሽ ጉዳትም ስለሌውና በትንሽ ካፒታል ተጀምሮ ብዙ መዋዕለ ነዋይ የሚገኝበት እንደመሆኑ በቁርጠኝነት መሠራት አለበት።
‹‹ቱሪዝሙ አገሪቷን በሚመጥን ደረጃ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ለነገ የሚተው ሥራ ባለመሆኑ አሁን ላይ ያሉትን ውስን የመረዳት ምልክቶች በማሳደግ በኢኮኖሚ የሚበለጽግበትን ዕድል ልንጠቀምበት ይገባል›› ሲሉ ወይዘሮ ዘነቡ ይመክራሉ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2011
አዲሱ ገረመው